“ወሳኝ” ማለት አስፈላጊ “ኩነት” ደግሞ ክስተት ወይም ድርጊት ማለት ነው:: ተጠቃሎ ሲነበብ እጅግ አስፈላጊ ድርጊት ወይም ክስተት ማለት እንደሆነ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት የመረጃ ቅበላ እና ጥራት ግምገማ ባለሙያ አቶ ዘመኑ ወርቁ ይገልፃሉ::
ልደትና ሞት እንዲሁም ጋብቻና ፍቺ የሰው ልጅ ህይወት የሚጀመርባቸው፣ የሚጠናቀቅባቸው እና የሚያልፍባቸው የህይወት ኩነቶች ናቸው:: እንግዲህ “ወሣኝ ኩነት” በመባል የሚታወቁት የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ክስተቶች ናቸው::
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥራ በአንድ ሀገር ዜጎች ላይ ከልደት እስከ ህልፈተ ህይወት የሚከሰቱ ወሳኝ ኩነቶችን በዋነኛነት የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ክስተቶችን በቀጣይነት፣ በቋሚነትና በአስገዳጅነት፣ የመመዝገብና የማከማቸት እንዲሁም በዋነኛነት ለሕግ፣ ለአስተዳደርና ለስታትስቲክስ ሥራ መረጃ ፍላጎት የማቅረብ ተግባራትን የሚያከናውን ነው::
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የዛሬውን ቅርጽና ይዘት ለመያዝ በሰው ልጅ ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ በርካታ ዘመናትን አስቆጥሯል:፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በተለይም ከሲቪል መብቶች ጋር በመያያዝ በመንግሥት ሕግ የተካተተው እ.አ.አ በ1804 በወጣው በፈረንሳይ ሲቪል ሕግ/civil code/ ውስጥ የወሳኝ ኩነቶች (ልደት ፣ ሞት ፣ ጋብቻና ፍቺ) ምዝገባ አሠራር እንዲካተት በተደረገበት ወቅት ነው ::
ወሣኝ ኩነቶች የተባሉበት ዋናው ምክንያት በሀገራት ሕገ – መንግሥትና በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የታወቁ የሰብዓዊ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ መብቶችን ተፈጻሚ ለማድረግና ለመጠበቅ ወሳኝ የሆኑ ሕጋዊ የግለሰብ ማንነት መረጃዎች ምንጭ በመሆናቸው ነው::
ከዚህ ባሻገር ኩነቶቹ የአንድን ሀገር ሕዝብ ብዛትና ዕድገትን በትክክል ስለሚያሳዩ፣ ለኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለሚዘጋጁ ዕቅዶች ዝግጅትና አፈጻጸም እስከ ዝቅተኛው አስተዳደር ክፍል አልፎም በግለሰቦች ደረጃ ተፈላጊና ወሳኝ መረጃዎች በመሆናቸው ወሳኝ ኩነት ተብለዋል::
እንደ ሀገር በአዋጅ ቁጥር 260 መሠረት ግዴታ ከሆኑት አራቱ ማለትም የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ክስተቶች በተጨማሪ ጉዲፈቻ፣ ልጅነት መቀበልን፣ አባትነት በፍርድ ቤት ማወቅን ከሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በማድረግ በጠቅላላው ሰባት ሁነቶችን እየመዘገበ ይገኛል::
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማካሄድ ለአስተዳደራዊ አገልግሎት (ለነዋሪ መታወቂያ ለመስጠት፣ ለፓስፖርት አገልግሎት፣ ጋብቻን ለሚመሠርቱ የጋብቻ ዕድሜ ደርሰዋል ወይ ለሚለው ጥያቄ፣ ከቅጥር ጋር ተያይዞ የጡረታ ዕድሜ፣ የመኪና ማሽከርከር ዕድሜ የመሳሰሉ ከዕድሜ ጋር ማጣራት ለሚፈልጉት ጉዳይ) በማስረጃነት ይቀርባል::
ለአካለ መጠን ዕድሜያቸው ያልደረሱ ሕፃናት ለዕድሜያቸው የሚመጥን ተግባር ላይ ብቻ እንዲታቀቡ ለማድረግ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ትልቅ ፋይዳ አለው::
ከዚህ በተጨማሪም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለብሔራዊ ደህንነት እና ወንጀል ጉዳዮች የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው::
ከቤተሰብ ሕጉ ጋርም ተያይዞ እናትነትን፣ አባትነትን ስለማወቅ፣ ልጅነትን ስለመቀጠል፣ ስለ ጉዲፈቻ፣ አካለ መጠን ስላልደረሡ ልጆች፣ ከጋብቻ እና ከጋብቻ ውጭ ስለተወለዱ ልጆች እና መሰል ውሳኔዎችን ለመወሰን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደ ዋና ማስረጃ ያገለግላል::
ሞትን እና የሞትን ምክንያት በማረጋገጥ ከመድን ከ(ኢንሹራንስ) ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመሳሳይ የምንዳኝበት ሁነኛ የመረጃ ሥርዓት በመሆን እንደሚያገለግልም ባለሙያው ዘመኑ ወርቁ ይገልፃሉ::
ከጋብቻ ምዝገባ እና ፍቺ ምዝገባ ጋር ተያይዞ የጋብቻ መኖር እና መፍረስ ማረጋገጫም ይሆናል::
ከወንጀል ሕግ ጋር ተያይዞ ወንጀለኛ ሆነው ሲቀርቡ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ዓመት በታች አሊያም ከዘጠኝ እስከ 12 ዓመት ዕድሜ መካከል የሚከሰቱ ጉዳዮችን ለመዳኘት እንደ ሁነኛ መረጃ ሆኖ ያገለግላል::
ለአካለ መጠን ያልደረሰች ልጅ መጠለፍን በሕጉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሰዎች ላይ ለተፈፀመ ድርጊት ቅጣት ማረጋገጫ ነው:: ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ ስለሚፈፀም የመደፈር ወንጀል ለተደፋሪዋ መረጃ ለመውሰድም ገለግላል::
በሌላ በኩል የሕዝብ ቁጥር ስሌት (ስታትስቲክሳዊ) መረጃ ለመሰብሰብ ሀገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው:: ባለሙያው እንዳብራሩት የሕዝብ ብዛት ስርጭት እና ለውጦች ክትትል ለማድረግ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ወሳኝ ነው፤ የሞት መረጃ የሞተውን (የተቀነሰውን)፣ ሲወለድ ደግሞ የሚወለደውን በመመዝገብ የተጨመረውን፣ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ አዲስ የገባውን፣ ከሀገር ሲወጣ ደግሞ (ሲሰደድ) በመቀነስ በሀገር ደረጃ ያለው የሕዝብ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በቀላሉ ማወቅ የሚያስችል ሥርዓት ነው::
በቀበሌ ደረጃ ውልደት ሲመዘገብ መረጃው ተሰብስቦ ቀጣይ ምን ያህል ትምህርት ቤቶች መገንባት ያፈልጋል የሚለውን ጥምርታ እንደ ሀገር ለመሥራት ትልቅ ማረጋገጫ በመሆን የሚያገለግል የመረጃ ምንጭ ነው:: የሴቶችን እና ሕፃናት መብቶችን ለማስከበርም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው::
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መቶ በመቶ ደርሶ መንግሥት እነዚህን መረጃዎች ባልያዘበት ሁኔታ ዘመናዊ ከተማና ዘመናዊ ሀገር መገንባት አይቻልም:: በአንድ ሀገር ውስጥ ምን ያህል ሰው ተወለደ፣ ሞተ፣ ተጋባ፣ ተፋታ፣ … የሚለው መረጃ እስከሌለ ድረስ የሀገሪቱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለመምራት ያስቸግራል::
ታዲያ ይህ ሁሉ ጠቀሜታ ያለው የወሳኝ ኩነት ምዝገባን የጠቀሜታውን ያህል መዝኖ ለእኔም ለሀገርም ጠቃሚ ነው ብሎ በማስመዝገብ በኩል ብዙ ሥራ እንደሚቀር ነው ባለሙያው አቶ ዘመኑ የሚገልፁት::
ሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም የተጀመረው እና ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚሰጥ አሠራር ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ የአግልግሎቱን አስፈላጊነት ተረድቶ በመጠቀም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ነው ያሉት::
በአጠቃላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በአግባቡ በመረዳት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል::
የህግ አንቀጽ
ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 7/2010 የወል የሆኑትን ድንጋጌ የምዝገባ አፈጻጸምና መረጃ አያያዝ መርሆዎች፡-
- በዚህ መመሪያ ተለይተው ከተመላከቱት መረጃዎች በስተቀር ሌላ ማንኛውንም ቃል በክብር መዝገብ ቅጾች እና ቅጂዎች ላይ መጻፍ የተከለከለ ነው፡፡
- ችሎታ የሌላቸው ግለሰቦች ላይ የሚከሰት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በተንከባከቢዎቻቸው ወይም በአሳዳሪዎቻቸው አማካኝነት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግለሰቡ ችሎታ የሌለው መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ከፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፡፡
- ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ ዜጎች ምዝገባ ቦታ በሁሉም ክልል በሚገኙ ዝቅተኛው የአስተዳደር ምዝገባ ጽህፈት ቤቶች ምዝገባው ይከናወናል፡፡
- መረጃዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ መያዝ አለባቸው፡፡
- ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኩነት ምዝገባ ደጋፊ ሰነዶች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካልተረጋገጠ እና በኢትዮጵያ የሰነዶች ማረጋገጠና ምዝገባ ኤጀንሲ ካልተመዘገበ በስተቀር ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
- ክብር መዝገብ ሹሙ ምዝገባን ካጠናቀቀ በኋላ የአስተዳደር ጽህፈት ቤቱን ማህተም ማሳረፍ ያለበት ሲሆን የወሳኝ ኩነት መዋቅር በተዘረጋባቸው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት የራሱን ማህትም መጠቀም አለበት፡፡
- ኩነቱ የተከሰተው በክብር መዝገብ ሹሙ/ሟወይም በሚስቱ/በባሏ ወይም በወላጆቹ ወይም በተወላጆቹ ላይ ከሆነ ምዝገባው በተተኪየክብር መዝገብ ሹም ይከናወናል፡፡
- የክብር መዝገብ ሹሙ በሃላፊነት የተረከባቸውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የክብር መዝገብ፣ የምስክር ወረቀትና ሌሎች ቁሳቁሶች ያለ በቂ ምክንያት ቢያጎድል አግባብ ባለው ህግ መሰረት ይጠየቃል፡፡
- በምስክር ወረቀት ህትመት ወቅት ሴሪ /ተከታታይ/ ቁጥር ተካቶ መታተም አለበት፡፡
- በወሳኝ ኩነት ምዝገባ አዋጅ 760/2004 እና 1049/2009 እንዲሁም በሌሎች ሕግች ላይ ያሉ ድንጋጌዎች በዚህ መመሪያ ውስጥ የሌሉ በመሆናቸው በምዝገባ ወቅት አዋጁንና ሌሎች ሕጎችን በማገናዘብ ምዝገባው የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ምንጭ፡- የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም