ወደ ሙዚቃው ዓለም ትገባለች ብሎ የሚጠብቅ ሰው አልነበረም፤ ነገር ግን እጣ ፋንታዋ ሆኖ ገብታለች:: ከስሟ በኋላ ያባቷ ስም ሳይሆን የሙዚቃዋ መጠሪያን አስከትሎ ነው ብዙ ሰው የሚጠራት:: ይህ ሙዚቃዋም ጉም ጉም ይሰኛል:: ደርባባዋ፣ ጨዋታ አዋቂዋ፣ ሳቂታዋ እና ድምጸ መረዋዋ ድምጻዊት መሠረት በለጠ (ጉም ጉም)ን የበኩር እንግዳ አድርገናታል፤
መልካም ንባብ!
የልጅነት ጊዜሽን እና ወደ ሙዚቃው የገባሽበትን አጋጣሚ ብታጫውቺን?
የተወለድኩት መራ ቤቴ ነው:: አባቴ ቄስ ነበረ:: ነብሱን ይማረው እና አሁን በሕይወት የለም:: እኛ (ልጆቹ) በቤተክርስቲያን አካሄድ ታንጸን እንድናድግ ይፈልጋል፤ በዛም ሁኔታ ነው ያደግነው:: ዘማሪ ነበርን፤ የሰንበት ተማሪዎች ነበርን:: አንዳንዴ ከቤተሰብ ተለይተህ ፈትለክ የምትለው ነገር አለ:: እኔም ከወንድሞቼ እህቶቼ ተለይቼ ወደ ስፖርቱ አመዝን ነበር:: ትንሽ ቆይቼ በስፖርት ወረዳችንን ወክዬ ወደ ተለያዩ ከተሞች መሄድ ጀመርኩ:: በዚህም ሳደንቃቸው የነበሩ ትልልቅ ድምጻዊያንን ማግኘት ጀመርኩ:: ውይ እንደዚህ በሆንኩ የሚል ፍላጎት መፈጠር ጀመረ:: ፈጣሪም ፍላጎቴን አይቶ “ያሰብሽው ይሁንልሽ” ብሎ ፈቀደልኝ፤ ወደ ሙዚቃ ገባሁ::
እናቴ የቤት እመቤት ነበረች:: በጣም በሥራ አግዛት ነበር፤ ውኃ ልቀዳ ቦኖ ወይም ወንዝ እወርዳለሁ:: እንዳሁኑ ቧንቧ ውኃ በየቤቱ አልነበረም:: ውኃ ከሚቀዳበት ፊት ለፊት ሙዚቃ ቤት አለ፤ እናም ውኃ ልቀዳ ቦኖ ተራ ስሄድ ጀሪካኔን ተራ አስይዤ ከሙዚቃ ቤቱ ቆሜ ሙዚቃ አዳምጥ ነበር፤ እስክስታ እወርድ ነበር:: ልጅ ስለነበርኩ ማፈር የሚባል ነገርም አላውቅም:: ተራዬ ሁሉ አልፎኝ ያውቃል:: በልጅነቴ ሰው በጣም ነበር የሚወደኝ:: የዘፈን ምርጫ እና ህብረ ትርኢት ከሰው ቤት እየሄድኩ አይ ነበር:: ከቤቴ በሬዲዮ ሙዚቃዎችን አዳምጥ ነበር:: እንደዛ እያዳመጥኩ እንዴት ጥሩ ሙዚቀኛ መሆን እችላለሁ ብየ አስብ ነበር:: በኋላ የታዳጊ ኪነት ተጀመረ:: አንደኛ ሆኜ ተመረጥኩ:: ቀጥሎ ደግሞ የወጣቶች ኪነት ገባሁ::
በሙዚቃ እንደዛ እየተሳተፍኩ ስፖርቱንም ጎን ለጎን አስኬድ ነበር:: እንደ መስከረም ሁለት እና የመሳሰሉ በዓላት ሲመጡ በውድድሮች ወረዳየን ወክየ እሳተፍ ነበር:: የኋላ ኋላ ልቤ ወደ ሙዚቃው ሙሉ ለሙሉ አደላ:: የወንድ፣ የሴት፣ የፍቅር፣ የሀገር የሚል አላውቅም፤ ሁሉን የተመቸኝን ዘፈን እዘፍን ነበር:: በስፖርቱም ደግሞ በሩጫ፣ መረብ፣ ቅርጫት እና ሌሎችን አስኬድ ነበር::
የከተማችን መብራት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ብቻ ነው የሚቆየው፤ ከዛ በኋላ ይጠፋል:: ስለዚህ ትምህርት ቤታችን ውስጥ መብራት ስለማይጠፋ “እዛ ሄደን እናጥና!” ብለን ወላጆቻችንን እናሳምናለን:: ትምህርት ቤት ሆነን ጓደኞቼ ደብተር እና መጽሐፋቸውን ሲያጠኑ እኔ የዘፈን ግጥሞችን ጽፌ ድምጼን ዝቅ አድርጌ እያንጎራጎርኩ ዘፈኑን አጠና ነበር:: ይህን የሙዚቃ ፍቅሬን የሚያውቅ ወታደር የነበረ አሁን በሕይወት የሌለ ወንድም ነበረኝ፣ የምድር ጦር አባል ነው:: እሱ “ምስራቅ እዝ ሙዚቀኛ ይቀጥራል፤ ሞክሪው” አለኝ:: ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ጠፍተን ወደ ሀረር በመሄድ ተቀጠርን::
ወደ ሀረር ስትገቡ ግር አልተሰኛችሁም?
ሦስታችንም በስፖርቱም ሆነ በኪነቱ ውስጥ የነበርን ልጆች ነን:: በስፖርቱ ውስጥ ዝዋይ፣ ደብረ ዘይት፣ ናዝሬት እና ሌሎች ከተሞች እንሄድ ነበር:: ስለሆነም የከተማውን ግርግር አስቀድመን ስለምናውቀው ግርታ አልተሰማንም:: እኔም ደግሞ አዲስ አበባ እማር ስለነበር የአዲስ አበባን ግርግር እንኳ በደንብ አውቀዋለሁ:: ሀረር ትንሽ ቸግሮን የነበረው ማረፊያ ነው:: የማታውቀው ሰው ጋር መቆየት ትንሽ ይከብዳል::
ምሥራቅ እዝ ሄደን ካምፕ ስንጠይቅ “ገና ቅጥር አልጀመርንም፤ እንቆያለን” አሉን:: አማራጭ ምን አለ? ብለን ስንጠይቅ:: ኦጋዴን አንበሳ ስፖርት ክለብን ተጠቆምን:: ሄደን ተፈተን፤ መረብ ኳስ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ እና ሌሎችን ነው የተፈተነው:: ልምድ ስለነበረን አለፍን:: ወዲያው ካምፕ ሰጡን:: ስድስት ወር ወታደራዊ ስልጠና እና የሙዚቃ ትምህርት ወሰድን:: ከስልጠናው በኋላ ፈተና ተፈተን:: እኔ የንግሥት አበበን ነበር የዘፈንኩት:: በሁሉም ፈተናዎች አንደኛ ወጥቼ ብዙ ነገር ተሸለምኩ፤ የሀረር ሙዚቀኛ ለመሆንም በቃሁ::
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መድረክ ላይ የዘፈንሽው ሙዚቃ ምን የሚል ነበር?
የካቲት 1980 ዓ.ም ቅጥር አድረገን በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ሁለት የወታደራዊ ኪነቶች ውድድር ይካሄድ ነበር፤ የጎሃ፣ ፖሊስ እና የምሥራቅ እዝ ነበር በውድድሩ የሚሳተፉት:: በዚያ መድረክ የራሴን ዘፈን አጥንቼ ወደ መድረክ ወጣሁ:: የዛን ጊዜ ፍቅር አልያዘኝም፤ ግን ያቀረብኩት የፍቅር ዘፈን ነው:: “ፍቅር ዓለም ገና” የሚል ነበር::
ሙዚቃው እንዴት ቀጠለ?
ከውድድሩ በኋላ ለካ ጥሩ ዘፋኝ መሆን እችላለሁ የሚለው ነገር ውስጤ ሰረፀ:: የኋላ ኋላ የመንግሥት ለውጥ መጣ:: ካምፑም ባዶ ሆነ:: እኛም ወደ አዲስ አበባ መጣን:: በብሔራዊ ትያትር ቤት ተቀጠርን፤ ከዚያ በኋላ በምሽት ክለቦች መዝፈን ተጀመረ:: በብዛት የሌሎች ሙዚቀኞችን ዜማዎች ነበር የማቀነቅነው::
የመጀመሪያው አልበምሽ እንዴት ተወጠነ? ለሕዝብስ እንዴት ደረሰ? ተቀባይነቱስ?
ከሀረር እንደመጣሁ ብሔራዊ ትያትር ነው የተቀጠርኩት:: እንደገና ቦሌ ካራማራ የሚባል የባሕል ቤት ነበር:: እዛም በትርፍ ጊዜ እሠራለሁ:: አረጓዴው ጎርፍ የሚባል ቤትም እንደዚሁ እሠራለሁ:: በዚያም የማዕከላዊ እዝ ሙዚቀኞች አብረው ይሠራሉ:: የሂሩትን ጉም ጉም እወደው ነበር፤ እንደሷ መዝፈን ባልችልም ለራሴ ብየ አንጎራጉረው ነበር:: እናም የማዕከላዊ እዝ ትልልቅ ሙዚቀኞች ሰምተውት፤ “እስኪ በይው?” ይሉኛል፤ ከሰሙ በኋላም ይደነቃሉ::
ከዚያ ለአዲስ ዓመት ከራስ ትያትር ባንድ ጋር ግሎባል ሆቴል አቀረብኩ:: በቴሌቪዢን ተላልፏል:: እነ ሙሉቀን እና ሂሩት ዘፍነውት በእኔ ድምጽ እጅግ ውጤታማ ይሆናል ብየ አላሰብኩም፤ እንደ ነገሩ ነው የዘፈንኩት:: የነበረው መልስ ግን በጣም ልዩ ነበር:: ካሴት አላወጣሁም፤ አልታወቅሁም:: ነገር ግን ከብዙ ሰው አድናቆት እና ሽልማት አገኘሁ:: ከእኔ ጋር ካሴት ሥሪ የሚል ጥያቄ መምጣት ጀመረ::
የሚገርመው ነገር ጉም ጉምን ሦስት ጊዜ ሠርቸዋለሁ:: የመጀመሪያው እንዲያው ጉም ጉም የሚለው ነው የነበረው:: በኋላ እናና ዘመዴ የሚል ቅኝት ተጨመረበት፤ ሁለተኛው ማለት ነው:: መጨረሻ ላይ የሠራሁት ደግሞ በመውደድ ጉም ጉም ብሎ እንጉርጉሮው ረዘም ተደርጎ ነው የተሠራው::
ከጉም ጉም በኋላ የነበሩት ሥራዎች እና ተቀባይነታቸው ምን ይመስላል?
ከሌሎች ጋር ሦስት የጋራ ሥራዎች አሉኝ:: ከሰማሃኝ በለው፣ ከግዛቸው ተሾመ፣ ከተስፋየ ውቤ፣ ከተስፋየ እሪኩም፣ ከዙሪያሽ አብዩ፣ ከታደሰ መከተ እና ሌሎች ጋር ሦስት ካሴት አለኝ:: ለብቻ ደግሞ ወደ አራት አሉኝ:: አራት ደግሞ ነጠላ ዜማዎች አሉ:: ተቀባይነታቸውም እጅግ ጥሩ ነው::
የሙዚቃ ሥራዎች ሲሠሩ ከባለሙያዎች ጋር ያለሽ መስተጋብር፣ ባሕል እና ወጉን ይዞ እንዲሠራ የምታደርጊው ጥረት ምን ይመስላል?
ስሠራ ባለኝ አቅም ከግጥም ደራሲዎች ጀምሮ እስከ አቀናባሪዎች ጥሩ ጥሩ ሃሳቦችን አቀርባለሁ:: ግጥሞቹ እንዲህ ቢሆኑ በሚል የሚሰማኝን ሃሳብ እናገራለሁ:: ግጥሞቹን አጥንቼ ራሴ ቀርጬ አመጣና አዳምጣለሁ፤ ጥሩ ስሜት ካልተሰማኝ አልሠራውም:: ምክንያቱም እኔን ያላስደሰተኝ አድማጭን አያስደስትም ብየ ስለማምን ነው:: ከዚያ ባሻገር በመነጋገር እና በመደማመጥ ሥራዎችን ለመሥራት እሞክራለሁ:: አስተያየት ስሰጥም ጠንከር ብየ ሳይሆን በትህትና ቀረብ ብየ ነው:: በአብዛኛው ሃሳቤንም ባለሙያዎች ይቀበሉኛል:: ለዚህም ነው የተሳኩ አልበሞችን ማውጣት የቻልነው::
እዚህ ለመድረስ የቤተሰቦችሽ እገዛ ምን ይመስላል?
ከመራ ቤቴ ጠፍቼ አዲስ አበባ ከዛ ሀረር ስሄድ የቄስ ልጅ አዝማሪ ሆነች ተብሎ ጉድ ተባለ:: አባቴንም ሰዎች እየሄዱ ይወቅሱት ነበር:: አባቴ ግን “ለልጄ እግዚአብሄር ሙዚቃን እንጀራዋ ካደረገው ከልክየ አላስቀራትም” ብሎ እንድቀጥል ወሰነ፤ ስለዚህ የመጀመሪያ ደጋፊዎቼ እናት እና አባቴ ናቸው:: እኔም ጎበዝ ነበርኩ እና ሠርቼ ጥሩ ደረጃ ላይ ስደርስ “እሰይ ልጄ ብዙ ሰው ያለአግባብ ተቃውሞሽ ነበር፤ እንኳንም ጆሮ አልሰጠሸው፤ አሁን ደግሞ መዝሙር ዘምሪ እና እግዚአብሔርን አስደስቺ” ብሎኛል:: እኔም ተሳክቶልኝ አባቴን አስደስቼው ብሞት ደስ ይለኝ ነበር፤ አልሆነልኝም (ሳግ ያለው ለቅሶ) አሁንም አምላክ ከፈቀደ አባቴ የፈለገውን የጠየቀኝን አደርግለታለሁ ብየ አስባለለሁ::
ባለቤቴ በሥራየ እጅግ ያግዘኛል፤ ሙዚቃዎቼን በጣም ነው የሚወዳቸው፤ በተለይ ዋለኔ የሚለውን ዘፈን በጣም ነው የሚወደው፤ ከዚህ የበለጠ እንድሠራም ያበረታታኛል፤ ብዙ ሥራ እንድሠራም ይፈልጋል:: ያው በቤተሰብ ጉዳይ እንዲሁም ለልጆቼ ጊዜ ለመስጠት ትንሽ ከሥራው ርቄያለሁ::
ስለ ልጆችሽ እና ቤት አያያዝ ንገሪን?
ልጆቼን ራሴ ነኝ የማሳድጋቸው:: ትልቋ ትምህርት ጨርሳለች፤ ትንንሾቹ አምስት እና ስምንት ዓመት ናቸው፤ ስለዚህ ለልጆቼ ጥሩ ጊዜ ሰጥቻለሁ፤ እኔ ነኝ ትምህርት ቤት ማደርሳቸው፤ ከሙዚቃውም ትንሽ የራኩት ለዚህ ነው:: ቤት አመራርም ጎበዝ ነኝ:: ጠጅ እና ጠላ እንኳ እራሴ ነኝ የምጠምቀው:: ባለቤቴ “በሰው እናሠራው፤ ለምን ትደክሚያለሽ?” ይላል፤ እኔ የት ሄጄ? እለዋለሁ::
ለሀገር ጥሪ የነበረሽ ምላሽ ምን ይመስላል?
በሀገሬ አልደራደርም፤ በፊትም “ሀ” ብየ የጀመርኩት ጦሩን በማዝናናት፣ በመቀስቀስ እና በመሳሰሉት ነው:: በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ከእነ ጋሽ ጥላሁን፣ ታምራት ሞላ እና ሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረን ጦሩን አበረታተናል፣ አዝናንተነዋል፤ ያውም እርጉዝ ሆኜ ሁሉ ነው የሄድኩት:: በቅርቡ በተከሰተው የህልውና ዘመቻም በቀረበልኝ ጥሪ መሰረት ጦሩን የማዝናናት እና የማነሳሳት ሥራ ሠርቻለሁ::
የባህል ሙዚቃ መበረዝ እያጋጠመ እንደሆነ ሙያተኞች ይናገራሉ፤ አንቺ ምን ትያለሽ?
ባህል ከዘመናዊ ሲበረዝ አልወድም፤ ባህላችን ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳውቀን:: ልብሳችን በዓለም ላይ ሲታይ ጌጥ ነው፤ ግርማ ሞገስ አለው:: እሴታችን ውበታችን ነው:: ይህ ተፍቆ ሲቀየጥ በጣም ያመኛል:: ዘፈኑ ጥሩ ባሕላዊ ዘፈን ሆኖ ክሊፑ የተቀየጠ ይሆናል፤ መሠራት ያለበት ባሕላዊው እንደ እንደ ባሕሉ፣ ዘመናዊውን እንደ ራሱ ነው፤ ድብልቅልቅ ያለ ነገር ቢደመጥ እንኳ ዘመን ተሻጋሪ አይሆንም::
በመጨረሻ የምታስተላልፊው ምልዕክት ካለ?
ለዚህ ክብር እና እውቅና ያደረሰኝን ፈጣሪን አመሰግናለሁ፤ ከዛ በመቀጠል ጎበዝ፣ በርቺ ጠንክሪ የሚለኝን የኢትዮጵያ ሕዝብ አመሰግናለሁ፤ የትም ብሔድ አድናቆት አይለየኝም:: ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አመሰግናለሁ፤ ጥሩ ሥራ ይዤ እንደምመጣ ቃል እገባለሁ:: ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን፣ ልጆቼን አመሰግናለሁ:: እናንተም (አሚኮ) ከረጅም ጊዜ በኋላ ፈልጋችሁ ስላገኛችሁኝ አመሰግናለሁ::
እንግዳችን ስለሆንሽ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም