የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ

0
347

ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አንድ እንግዳ ሰው ብቅ አለ፡፡ ይህ ሰው በአለም ውስጥ የተወለደ ቢሆንም፣ ልክ እንደማንኛውም ሰው ሰብአዊ ማንነት ቢኖረውም ተራ ሰው አልነበረም። እንደ ክርስትና እምነት እየሱስ ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ ወደ ምድር የመጣው፣ በሰው አምሳል የተገለጠው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ገና ከዘመናት በፊት እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ምድር ልኮ እንደ ሰው ስጋ ለብሶ የሰው ልጅን ከኃጢያት ሞት ለማዳን ያለውን ሀሳብ በነብያት በኩል አስቀድሞ ገልጦት ነበር። እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ድንግል ፈፅሞ ወንድ በማታውቀው በንፅህት ሴት ማርያም ማህፀን በመንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ፣ ተወልዶ፣ አድጎ የአባቱን ዘላለማዊ እቅድ በምድር ላይ ፈፅሞ ከዚያ ተሰቅሎ እንደሚሞት፣ በሦስተኛውም ቀን ተመልሶ እንደሚነሳ የተለያዩ ነብያት የሰጡት የትምቢት ቃል እስኪፈፀም በአማኞች ዘንድ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ ዘልቋል።።

እየሱስ ክርስቶስ  በተለይ ለሺዎቹ ዓመታት በስደት እና በባርነት ይማቅ ለነበሩት እስራኤላውያን የትንቢቱ መፈፀም በጉጉት የሚጠበቅ የመከራ እና የባርነት ማብቂያ ማብሰሪያ የሚሆን ትልቅ መለኮታዊ ተስፋ ነበር። መሲሁ እየሱስ ክርስቶስ።

መጽሐፍ ቅዱስ እየሱስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ መሲሕ ወይም ክርስቶስ አድርጎ ስለሚልከው ልጁ ተንብዮ ነበር። “መሲሕ” ከዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ አዳኝ ማለት ነው፤ “ክርስቶስ” የሚለው ቃል ደግሞ ከግሪክኛ ቃል የተወሰደ  ሲሆን “የተቀባ” የሚል ትርጉም አላቸው።

ከእየሱስ ዘመን በፊት የኖሩት የአምላክ ነቢያት ስለ መሲሑ በተናገሩት ትንቢት ላይ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠቅሰዋል።በመጀመሪያ ከ700 የሚበልጡ ዓመታት አስቀድሞ ነቢዩ ሚክያስ መሲሑ በይሁዳ ምድር በምትገኘው ቤተ ልሔም የተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ እንደሚወለድ ተንብዮ ነበር። በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ ላይ እየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላ ነገር ተፈጽሟል። ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ለመጠመቅ ወደ አጥማቂው ዮሐንስ የሄደው በዚህ ዓመት ነበር።

እግዚአብሔር፣ ዮሐንስ መሲሑን ለይቶ ማወቅ እንዲችል ምልክት እንደሚያሳየው ቃል ገብቶለት ነበር። እየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ዮሐንስ ይህን ምልክት ተመልክቷል። መጽሐፍ ቅዱስ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። እነሆ፣ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።” እየሱስ በዚያ ዕለት የአምላክ መንፈስ ወይም ኃይል በላዩ ሲወርድበት መሪና ንጉሥ እንዲሆን የተሾመ መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ አወቀ።

በሰማይ የነበረውን የበኩር ልጁን ሕይወት ማርያም ወደምትባል አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ማኅፀን አዛወረው። ይህን ለማድረግ ሰብዓዊ አባት አላስፈለገም። በዚህ መንገድ ማርያም ፍጹም ልጅ የወለደች ሲሆን ስሙንም እየሱስ ብላ ጠራችው።

እየሱስ ማን ነው ቢባል በአጭሩ ለማስረዳት ያህል እየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው በብሉይ ኪዳን ስለሚመጣው መሢህ (ክርስቶስ) ሲተነበይ ከመጠሪያዎቹ አንዱ አማኑኤል እግዚአብሔር ከኛ ጋራ ማለት ነው። ምድር የእግዚአብሔር መረገጫ እንደ ተባለች (ኢሳይያስ 66:1 እና ማቴ.5:35) ወደፊት «ከወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ» ለዘላለም የሚነግስ ብለው የተነበዩለት አምላክ የሚሉት እግዚአብሔር ነው። የሰውን ልጅ ከጠፋበት መንገድ ሊመልስ፣ ከጨለማ ስልጣን ሊያድነን፣ ነፍሱን ለሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ፣ ደሙን ከፍሎ ሊዋጅ፣ የሰይጣንን ሥራ ሊያፈርስ፣ የዘላለም ሕይወት ሊሰጥ ከሰማይ የተላከ መሲህ ሆኖ እንደተገለጠ የክርስትና እምነት ታሪክ ያስረዳል፡፡

የተነገረው የትንቢት ቃል መፈፀሚያው ወቅት ሲደርስ እየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማሪያም እንደሚወለድ በመልአኩ ገብርኤል አማካይነት ተበሰረ። በአለማዊው እውቀት መሰረት የሚታመን የማይመስለው ተዓምር ተፈፅሞ ድንግል ማርያም ያለወንድ ሕፃን መፀነሷ ታወቀ። ይህ እያነጋገረ ሳለ በትንቢት እንደተነገረው በቤተልሔም በበጎች ግርግም ውስጥ ብላቴናው እየሱስ ተወለደ።

እንደ ክርስትና እምነትና ወንጌሎች ኢየሱስ ከድንግል ማርያም እና ከመንፈስ ቅዱስ በቤተ ልሔም፣ ይሁዳ ተወለደ። ድንግሏ ማርያምና እጮኛዋ ዮሴፍ ለሕዝብ ቆጠራ በይሁዳ ስለ ተገኙ የቤት መጻተኞች ሆነው በጋጣ ተኝተው ነበር፤ ኢየሱስም በግርግም እንደተኛ ተደረገ እንጂ አልጋ አልነበረም። ።

የልጅነት ዘመን እና አስተማሪነት

ብላቴናው እየሱስ እንደማንኛውም ሕፃን ወላጆቹን እያገለገለ፣ እየታዘዘ ያድግ እንደነበር የክርስቶስ ታሪክ ፀሀፊዎች አስፍረውታል። እየሱስ እንደ ጨዋ ልጅ ወላጆቹን ከማገዝ ባለፈ ገና በብላቴንነቱ ትላልቆች አፋቸውን ከፍተው የሚሰሙት የልጅ አዋቂ ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ አስደናቂ እውቀት እየተመላ ያድግ የነበረው እየሱስ እግዚአብሔር መንግሥት ማስተማርን እንደዋና ተግባሩ አድርጎ በመላ እስራኤል እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። በተጨማሪም እየሱስ የታመሙትን ይፈውስ ነበር፣ አስደናቂ ተዓምራትንም ይሰራ ነበር። ሲያስተምር ከነበራቸው ብዙ ጥቅሶች መካከል ለአብነት፣ “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም…” (ማቴ 20፡25)

በዚሁ ጥቅስ ኢየሱስ ዓለሙን እንደ ገለበጠ ተብሏል። በዚያን ጊዜ ይሁዳ በባዕድ አረመኔ ሕዝብ ከባድ ገዥነት ሥር ነበረችና፣ የአይሁዶች ሊቃውንት ከትንቢት የተነሣ ከሮሜ ዕጅ የሚያድናቸውን መሢሕ ይጠብቁ ነበር። ይህ አይነት ትንቢት ቢገኝም ኢየሱስ ያንጊዜ ጦርነት ስላላነሣ የአይሁድ መሪዎች ሊቀበሉት ፈቃደኛ አልነበሩም።

ለሚሰሙት ተከታዮቹ ደግሞ አዲስ ጥያቄ ጠየቃቸው፣ እንዲህ ሲል፦ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?”። እነዚህ  እየሱስ ካስተማራቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

ይሁን እንጂ እየሱስ ያስተምር በነበረው መለኮታዊ እውቀት የብዙዎችን ቀልብ ገዝቶ ስለነበር እጅግ ብዙ ተከታዮችን ማፍራት እየቻለ ትምህርቱም እየተዛመተ ሄደ። ነገር ግን ይህ ተቀባይነቱ እና ዝናው መናኘት ከትላልቅ የአይሁድ ካህናት እና ፈሪሳውያን ተቃውሞ እየገጠመው መጣ። በመላ እስራኤል በትምህርቱ አስደናቂነት፣ በሚሰራቸው ተዓምራቶች መነጋገሪያ እየሆነ የመጣው እየሱስ ክርስቶስ ሊገድሉት የሚያሴሩ ሰዎች እንዳሉ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ለደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጣው ሁሉ እየነገራቸው እንዲበረቱ ያስተምራቸው ያዘጋጃቸውም ነበር።

እየሱስ በሕዝቡ ተቀባይነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ያልተደሰቱት ፈሪሳውያን የሀሰት ክስ ይጎነጉኑበት ያዙ። በዘመኑ እስራኤል በሮማውያን ስለምትተዳደር ለሮሙ ንጉሥ ሄሮድስ እኔ የእስራኤል ንጉሥ ነኝ እያለ ሕዝቡን ያስታል ብለው ወነጀሉት። በስልጣኑ የመጡበት የሮማው ገዢም እንዲገርፉት እንዲለቁት ቢወስንም  ፈሪሳውያኑ ግን እንዲሰቅልላቸው ስለጠየቁት ወሰነላቸው፣ እርሱ ግን እጁን ታጥቦ ከደሙ ንፁህነቱን ገለፀ። እናም ክርስቶስ በመጨረሻ ይሆናል ተብሎ በተነገረው ትንቢት መሰረት በብዙ መከራ ግርፋት እና እንግልት ወደ መስቀል ተወሰደ፤ ሰቀሉት። ከእርሱ ጋር ሁለት ሰዎች በግራ እና በቀኝ አብረው ተሰቅለው ነበር።

ስቅለት

እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ‹‹ሁሉ ተፈጸመ›› አለ፡፡ ያን ጊዜም   ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡ አይሁድም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ ብለው ጭን ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ጭፍሮቹም የሁለቱን ወንበዴዎች ጭናቸውን ሰብረው አወረዷቸው፡፡ ወደ እየሱስ ሲቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ‹‹ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንቱንም አትስበሩ›› ተብሎ የተነገረው ምሳሌያዊ ትንቢት ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ተብሎ የተፃፈው የመፅሀፍ ቅዱስ የትንቢት ቃል ተፈፀመ።

ጁሊየስ አፍሪካነስ የተባለ እውቅ የጥንት ታሪክ ፀሀፊ የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ አስደናቂ እውነታዎችን ፅፏል። በስቅለቱ እለት ምድሪቱን የሸፈነውን ድቅድቅ ጨለማን በመረጃ አጣቅሶ ስገልፀው…መላው ዓለም በአስፈሪ ጨለማ ተውጦ ነበር፤ እንዲሁም ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ የምድርን መሰረቶች ንጠውት ነበር። ይሁዳ እና ሌሎች አውራጃዎች ፈራረሱ…።”በማለት የስቅለቱን እለት አስፈሪ የተፈጥሮ መናወጥን በታሪክ ውስጥ ከትቦታል።

ወደ መቃብር መውረዱ

እየሱስ ክርስቶስ የተቀበረበት ሥፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ሲመሽ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ወደ ጲላጦስ ሄደው የጌታን ሥጋ አውርደው ይቀብሩ ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ከዚያም ከመስቀል አውርደው  ዮሴፍ ለራሱ ብሎ ባሳነጸው በአዲስ መቃብር ለመቅበር በኀዘንና በልቅሶ በአዲስ በፍታ ጠቅልለው ቀበሩት። ትልቅ ድንጋይም አምጥተው በመቃብሩ ላይ  ገጠሙት፡፡ አንዳንድ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት በመቃብሩ ላይ የተገጠመው ድንጋይ እስከ 2000 ፓውንድ ክብደት ያለው በሰው ጉልበት የማይንቀሳቀስ ግዙፍ ድንጋይ ነበር።

ትንሳኤ

የአይሁድ አለቆች ግን ‹‹ክርስቶስ እነሣለሁ ብሏል፤ ስለዚህ ሐዋርያት ሰርቀው ተነሥቷል እንዳይሉን መቃብሩን እናስጠብቅ›› ብለው ጠባቂዎችን ቀጠሩለት፡፡ እጅግ የሰለጠኑ ንቁ ወታደሮች ነበሩ። መቃብሩ እንደተዘጋ፣ ወታደሮቹም በንቃት እየጠበቁ ሦስት ቀን ደፈነ፤ በሁለቱ ቀን ምንም አዲስ ነገር አልነበረም። በሦስተኛው ቀን ማለዳ ላይ የሆነው ክስተት ግን እጅግ አስገራሚ ነበር። እየሱስ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ለደቀመዛሙርቱ የነገራቸው አፅናኝ ቃል ይፈፀም ዘንድ መቃብሩን የፈነቃቀለ ይትንሳኤው ጉልበት ከሰማይ ወረደ። መቃብሩን ፈነቃቅሎ እየሱስን ከሙታን አለም ሕያው አድርጎ ከተዘጋው መቃብር ውስጥ አስነሳው። አንዳንድ የስነ መለኮት ዘርፍ ተመራማሪዎች ሲገልፁት እየሱስን ከመቃብር ያስነሳው ኃይል ምድሪቱን ከዳር እስከዳር ንጧት ነበር ያለፈው። ይህን መሬትን ያስጨነቀውን የመሬት መናጥ ያልተሰማው የምድር ክፍል አልነበረም ሲሉ ያስረዳሉ። ትንሳኤ ሆነ።

እሁድ ሌሊት፣ ምናልባትም እርሱ ከተሰቀለ፣ ከሞተና ከተቀበረ ከ36 ሰዓታት በኋላ ከሙታን እንደ ተነሣና አስከሬኑ የነበረበት መቃብር ባዶ እንደሆነ፣ እንዲሁም በአዲስ መልክ እና ባልተለመደ ሁኔታ ኢየሱስ በሚታይ አካላዊ ማንነት ሕያው መሆኑን የዐይን ምስክሮች መሰከሩ። እነዚህ የአይን ምስክሮች የትንሣኤ አካል ይዞ ከተነሣውና ኢየሱስ እንደሆነ ከመሰከሩት አካል ጋር መነጋገራቸውናን የተቀበረበት መቃብር ባዶ መሆኑን መመልከታቸውን መመስከር ችለዋል።

ብሮተን ኖክስ እንደተባለው ጸሐፊ ትንሣኤ የክርስቶስ ስቅላትና ሞት ውጤት ነው። በመሆኑም፣ የክርስቶስ ትንሣኤ እውንነት እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ወደ ፍጻሜና ግብ በማምጣት በጥልቅና በማይናወጥ መሠረት ላይ ለማኖር ያለውን ጥልቅ መሻት በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሙታን በማሥነሣት የሁሉ ፈራጅ አድርጎ በመሾሙ ምክንያት፣ በመጨረሻው ሁሉም አማኝ ከሞት ተነሥቶ የትንሣኤ አካል በማግኘት በክርስቶስ ፍርድ ፊት ይቀርባል የሚል ሀሳብ  ፅፏል። እኛም አበቃን፤ ለመላው የክርስትና አማኞች መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን ተመኘን።

(መሠት ቸኮል)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here