ጥላሁን ገሠሠ በሌላ መልኩ

0
273

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ ነው። ብዙዎች ተስማምተው ይህንን ክብር ሰጥተውታል። ሙዚቃን ከ50 ዓመታት በላይ ነግሦባት አልፏል። ሙዚቃ ለጥላሁን ከዘፈን እና ከገንዘብ ማግኛነት ያለፈ ትርጉም ነበረው።  ሙዚቃ ለጥላሁን እስትንፋስ ነበር። ዛሬ ጥላሁንን ከዘፈኖቹ በስተጀርባ ባለው ሕይወቱ እንመለከተዋለን። ዘከሪያ መሐመድ “ጥላሁን ገሠሠ የህይወቱ ታሪክና ምሥጢር” በሚል የጻፈውን መጽሐፍ ዋቢ በማድረግ ቀጣዩን ጽሑፍ አጋራችኋለሁ።

የኢትዮጽያ ደራሲያን ማሕበር በ2004 ዓ.ም የጥላሁንን ሕይወት የሚመለከት መጽሐፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ዘከሪያ መሐመድ ደግሞ ሌላ መጽሐፍ በጥላሁን ሕይወት ላይ ሲጽፍ የቀድሞ ታሪኩን የሚያፈርሱ፣ የተደበቁትን እውነቶች ያወጡ፣ እንቆቅልሹን ጥላሁንን አሳይቶናል። የዝነኞች ሕይወትም እንደ ሌላው ሰው ደስታ እና ኀዘን የሚፈራርቁበት መሆኑን ያሳያል። ከዚህም በላይ ጥላሁን በልጅነት ሕይወቱ የገጠመው ቤተሰባዊ መናጋት የሕይወቱን ጉዞ በሙሉ ሲከተለው እንደኖረ ያሳያል። ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ጥላሁንን የበለጠ በሰው ስሜት እንድንረዳው፣ ከመጠቋቆም ይልቅ ሰው በመሆኑ በችግሮች ውስጥ ማለፉን እንድንገነዘብ በማሰብ ነው። ምናልባትም ሌሎች ሰዎች ከዚህ የሕይወት ልምድ አንዳች ቁም ነገር ይወስዳሉ በሚል ነው። መልካም ንባብ።

በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ፤  በየቦታው ያለው የሀገሬ ሕዝብ ወራሪው ጠላት ሀገሩን ተቆጣጥሮ ተረጋግቶ እንዲቀመጥ አላደረገውም። በተለያዩ ቦታዎች ለወራሪ አልገዛም ያለው ሕዝብ በዱር በገደል መሽጎ እያደፈጠ በማጥቃት ጠላትን እረፍት አሳጥቶት ነበር። በአርበኝነት ዱር ካልገባው ሕዝብ አንዳንዱ ለጠላት ተቀጥሮ ሢሠራ፤አቅሙ የቻለ ደግሞ የጠላት አገልጋይ ከመሆን በማለት በጠላት ወዳልተያዙ አካባቢዎች ይሰደድ ነበር።

በዚህ ጊዜ አንድ ዕድሜው በወጣትነት  ላይ የሚገኝ ሰው የትውልድ አካባቢው ቡልጋ  በጠላት  እጅ ሲወድቅ በየረር እና ከረዩ አውራጃ አሳብሮ ወደ ጨቦ እና ጉራጌ አውራጃ፣ ጎሮ/ሶየማ ይሰደዳል። ይህ ቁመናው ዘለግ ያለ ፣መልከ መልካም ወጣት ጎሮ/ሶየማ አካባቢ ሲኖር በአጋጣሚ ከአንዲት የአካባቢው ነዋሪ ኮረዳ ጋር ይተያያል። መተያየት ወደ ትውውቅ፣ ትውውቅ ወደ መግባባት፣ መግባባቱ ወደ ቅርርብ፣ ቅርርቡ ወደ ምስጢራዊ የፍቅር ግንኙነት ያድጋል። ይህ የቡልጋ ወጣት ገሠሠ ወልደ ኪዳን ይባላል። የጎሮ/ሶየማዋ ኮረዳ ደግሞ ደግሞ ጌጤነሽ ኢተአ ትባላለች።

ዕለቱ ዓርብ መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የወደፊቱን ኮከብ ታሪክ በጻፉት ፈይሳ ኀይሌ ሐሰና አያት እልፍኝ (በአቶ ሐሰን ቤኛ ማለት ነው) ውስጥ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ ነበር። ከእኩለ ቀን በኋላ ጌጤነሽ ምጥ ተያዘች።ምጧም ረጅም ሰዓት ወሰደ። ከሰዓታት በኋላ ጌጤነሽ ወንድ ልጅ ተገላገለች። የጌጤነሽ እናት ነገዬ አብደላ ለተወለደው ሕጻን ደገፋ ሲሉ ስም አወጡለት።

በወሊሶ ከተማ ተወልደው የጎለመሱት ስመጥር ሰው ቀኛዝማች መኮንን መሸሻ፣ በመስከረም ወር 1934 ደገፋ አንድ ዓመት ሲሞላው “ይህንን ልጅ ክርስትና ላንሳው” ሲሉ ሐሳብ አቀረቡ። ምንም እንኳን የወይዘሮ ጌጤነሽ ወላጆች እና ቤተሰቦቿ እምነት እስልምና ቢሆንም፣ የቀኛዝማች መኮንን ጥያቄ ይሁንታን አገኘ። ደገፋ በተወለደ በአንድ ዓመቱ መስከረም ወር 1934 ዓ.ም ወሊሶ  ከተማ ውስጥ በሚገኘው የቤተሳይዳ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን በቀኛዝማች መኮንን የክርስትና አባትነት ተጠመቀ። በዚህ ጊዜም የክርስትና አባቱ ጥላሁን የሚል ስም አወጡለት። ይህ ስም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ በማይደበዝዝ ቀለም ተጻፈ።

በ1938 አንድ ዕለት የጥላሁን እናት ጌጤነሽ ከምትኖርባት አመያ ቀበሌ (ከወሊሶ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች) ድንገት መጥፋቷ  ተነገረ። ከአቶ ገሠሠ ወልደ ኪዳን ጋር መኖር በጀመረች በአምስተኛው ዓመት የሄደችበት ሳይታወቅ መጥፋቷ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጠረ። ሕጻን ልጇን ጥላ ለምን፣ የት ሄደች የሚለው በጥላሁን አያት ወ/ሮ ነገዬ ላይ ረብሻን ጫረባቸው። ቀደም ብሎ  ጌጤነሽ እና ገሠሠ ቤተሰቡ ያልፈቀደውን እና ያላቀደውን የፍቅር ግንኙነት በምስጢር አድርገው  ልጅ መውለዳቸው ቅሬታን በመፍጠሩ፣ እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር ደግሞ ይበልጥ ያስደነግጣል።   ምናልባትም ሚስቱ በሌለችበት የአማቱ ርስት ላይ መኖሩ ጫና ፈጥሮበት ይሆናል። ጥላሁን በአያቱ እጅ ላይ አረፈ።

በ1939 መስከረም ወር በስድስት ዓመቱ ጥላሁን ከአያቱ ወ/ሮ ነገዬ አብደላ ጋር በመሆን ያደገበትን አመያን ትቶ ወደ ወሊሶ  ተጓዘ። በራስ ጎበና ዳጨው ትምህርት ቤትም ተመዘገበ። የክርስትና አባቱ ቀኛዝማች መኮንን በሰጧቸው ቤት ሆኖ ከአያቱ ጋር መማር ቀጠለ። በትምህርት ቤት ቆይታው ለመዝሙር እንጂ ለሌላ ትምህርት ግድ አልነበረውም። በዚያው ትምህርት ቤት ያገኛቸው አስተማሪዎች  እና ርእሰ መምህሩ ጥላሁን ዘፈን ላይ ያለውን ፍላጎት የበለጠ እንዲያጠነክር አገዙት።

“ዘፈን የጀመርሁት የስምንት ዓመት ልጅ ሆኜ ሆይ ሆያ  የሚሉትን በማየት እና ከዚያም በትምህርት ቤት በመዝሙር ነው። ከዚያ ‘ጠላታችን ወደቀ፣ፍጹም ጠፋ ሞሶሎኒ’ የምትለዋን መዝሙር በማዳመጥ ብቻ እየዘመርኩ፣ ከዚያም ‘መንግሥትን ለዳዊት ቡራኬን ለሴም’ ስል የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር የነበሩት ሱዳናዊ ሚስተር ሸዳድ ያበረታቱኝ ጀመር። ከዚያ የሚስተር ሸዳድ ወንድም ማህሙድ ሳንሁሪ ወንድሙ ቤት እየወሰደኝ የሱዳንን ሸክላ መስማት፣ ኮፒ ማድረግ ሆነ።ሚስተር ሸዳድ ዘወትር ከወንድማቸው ጋር ሥራችን ዘፈን ብቻ መሆኑን ሲያዩ ዘፋኝ እንድሆን ገፋፉኝ”  ጥላሁን ስለ ሙዚቃ አጀማመሩ ያወራው ነበር።

በወላጆቹ ናፍቆት ውስጥ ሲብሰለሰል  የነበረው ጥላሁን በ1940 ክፉኛ ታመመ። በወቅቱ የሰባት ዓመት ልጅ ነበር። እናቱ ድንገት ከቤተሰቡ መሐል ጥላው በጠፋች በ2ኛ ዓመት ነበር።ዕለቱ ፋሲካ ነበር። በፀና ታሞ በቤተሰቡ ብርቱ ጸሎትና ልመና ከሞት ተርፏል። ጥላሁን አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየው በ1943 ከአያቱ ነገዬ አብደላ ጋር ነበር። የጥላሁን አያት ከወሊሶ አዲስ አበባ ከዚያም ደብረ ብርሀን ጥላሁንን ይዘውት የሄዱት ከወዳጃቸው አቶ ፈይሳ ኀይሌ ሐሰን ዘንድ ወስደው ለማስመከር ነበር። በወቅቱ ጥላሁን ትምህርቱን ችላ  ብሎ መዝሙር እና ጨዋታ ላይ አተኩሮ ነበር። እንዲያጠና ተመክሮ ወደ ወሊሶ ተመለሰ። ቀኛዝማች መኮንን መሸሻም ኑሯቸው አዲስ አበባ ነበርና ወደ ወሊሶ ሄደው ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር መክረውታል።

ጥላሁን ገሠሠ የህይወቱ ታሪክና ምሥጢር በሚል መጽሐፉ ላይ ዘከሪያ መሐመድ ጥላሁን የደረሰበትን የቤተሰብ ታሪክ ኀዘን እና ስብራት ፣የተስፋ አንገቱን ቀና ያደረገበት መሣሪያው ሙዚቃው ነው ይላል። “ሙዚቃ ለጥላሁን ካስማ እና ማገር ነች፣ እሱ በሙዚቃ ዳግም ተወልዷል፣ በሙዚቃ አዲስ ሕልውና አግኝቷል፣ መራራ ሕይወቱ በሙዚቃ ጣፍጧል። አሮጌው እውነት… ያ አሳማሚ እና መራራ እውነት ከነምሬቱ በአእምሮው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተከርችሟል።” በማለት ዘከሪያ ጽፏል።

ከአመያ ድንገት ከጠፋች  ከአምስት ዓመታት በኋላ የጥላሁን እናት፤ ጌጤነሽ ኢተአ በአዲስ አበባ ከተማ ጨርቆስ መገኘቷ ተሰማ። ጊዜውም ታህሳስ 19 ቀን 1944 ነበር። ዘከሪያ መሐመድ እንደ ምንጭነት የተጠቀመበት የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ጽሐፊ ፈይሳ ኀይሌ ሐሰና “ያጋጠማት ችግር ካለ መፍትሔ ለመሻት አስቀድሞ ችግርን መስማት እና መረዳት ያስፈልግ ነበር እና ተነስታ የጠፋችበትን ምክንያት እንድትነግረኝ ጠየቅኋት። ምንም ነገር ለመናገር አልፈቀደችም። ወደ ቤተሰቦች አመያ የመመለስ ጉዳይም ቀረ። በአዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ በስተጀርባ የሚገኝ ሰፈር መጣን። እናቷ ወይዘሮ ነገዬ ከልጇ፣ ጥላሁንም ከእናቱ ጋር ተገናኙ” በማለት መዝግበዋል።

ጥላሁን እናቱን ሲያገኝ የመረጋጋት ስሜት አልነበረውም። ወደ ወሊሶ ተመልሶ ትምህርቱን እንዲከታተል ተደረገ። እናቱ እዚሁ አዲስ አበባ ጠጅ መነገድ ጀመረች። አቶ ፈይሳ አራት የጠጅ በርሜል ገዙላት፣ ሌሎች ነገሮችንም ሰጧት። እናቷ ወይዘሮ ነገዬ ለጌጤነሽ ለጊዜው ብለው 600 ብር ሰጧት።

በ1946  ጥላሁን ገሠሠ ከወሊሶ ጠፍቶ አዲስ አበባ ወላጅ እናቱ ዘንድ ሄደ። እንዲመለስ ሲነገረውም ፈቃደኛ አልነበረም የክርስትና አባቱ ቀኛዝማች መኮንን ወደ ወሊሶ  በትሬንታ ኳትሮ መኪናቸው ጭነው ወሰዱት። ከወራት በኋላ በዚህችው ትሬንታ ኳትሮ ሳያዩት እንደ እቃ ተጭኖ አዲስ አበባ ገባ። በ1946 ጥላሁን ገሠሠ ሀገር ፍቅር ቴያትር ተቀጠረ። ብርቱካኔ፣ጥላ ከለላዬ እና አልማዝ ነች የጠራችን በመዝፈን የሕዝብ ልብ ውስጥ መግባት ጀመረ።ያን ጊዜ ጥላሁን የጋዜጠኞችን ቀልብ እና ትኩረት ሳበ። የማን ነህ፣ የት ነህ፣ ውልደት እና እድገትህ የት ነው የሚሉ ጥያቄዎች ያሳድዱት ጀመር።

ዘከሪያ ጥላሁን በአምስት ዓመቱ የተፈጠረበትን የቤተሰቡን ስብራት ታሪክ በመሸሽ ነበር የኖረው ይላል “አሳማሚው  እውነት የሚፈጥርበትን መረበሽ መቋቋም ይችል ዘንድ አዕምሮው መከላከያ አድርጎ የተጠቀመው እውነቱን የመካድ፣ የማዳፈን፣ ብሎም የመቀየር አማራጭን ነው” ይላል። ለማሳያነትም ጥላሁን ጋዜጠኞች ሲጠይቁት ያቀርብ የነበረውን የፈጠራ እና የሽሽት ቃል እንመልከት “አዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ ሰፈር ተወልጄ ስድስት ወሬ  አያቴ ወደ ወሊሶ  ይዘውኝ ሄዱ። ከዚያም በትምህርት ቤት ስዘምር የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ዘፋኝ እንድሆን አበረታቱኝ። ከዚያም አዲስ አበባ መጭቼ በሀገር ፍቅር ቴያትር ማህበር ተቀጠርሁ” የሚል ነው። ጥላሁን በሕይወት ዘመኑ “አዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ ሰፈር ተወልጄ በስድስት ወሬ አያቴ ወደ ወሊሶ ይዘውኝ ሄዱ” የሚለውን ሐሳብ ሲደጋግመው ኖሯል። ይሁን እንጂ ይሕ ሐሳብ ዘከሪያ እንደሚለው ትክክል አይደለም።

በዚህ አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ያለፈው ጥላሁን በ14 ዓመቱ ሀገር ፍቅር ትያትር ማኅበር፣ ቀጥሎም በ18 ዓመቱ ክብር ዘበኛን ተቀላቅሎ በፍጥነት ያልጠበቀው ዝና ውስጥ ገብቷል። ታሪኩ የብዙዎችን ትኩረት እንዲስብም አድርጎታል። ዝናን እንዴት ማስተናገድ እንዳለበት እንኳን ባልተረዳበት ዘመን የአደባባይ ሰው ሆኗል።

ይቀጥላል!

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here