ፍልስጤም በጥንታዊ እና በዘመናዊው የመካከለኛው ምስራቅ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና ያለው አንድ አነስተኛ ክልል ነው። ለበርካታ የዓለማችን ዋና ዋና እምነቶች ካለው ጠቀሜታ እና በአፍሪካ እና እስያ መካከል ጠቃሚ የሆነ አገናኝ ድልድይ የሆነ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው በመሆኑ የፍልስጤም ታሪክ ተደጋጋሚ በሆነ ፖለቲካዊ ግጭት እና በአደገኛ የመሬት ወረራ የተሞላ ነው። በአሁኑ ጊዜ ይህን ስፍራ እንደ ርስታቸው የሚጠሩት የአረብ ሕዝብ ፍልስጤማውያን ይባላሉ።
ታዲያ ፍልስጤም ማለት ምንድነው? ከሚል ጥያቄ ብንጀምር ፍልስጤም የሚለው ቃል፣ ፊሊስቲያ ከሚል ጥንታዊ የግሪክ ቃል የተወሰደ ነው ነገር ግን የጥንት ግብፃዊያን፣ አሶራውያን እና እብራዉያን ቋንቋዎች ተመሳሳይ ቅላፄ የሚሰጡ ቃላትን አካተው እናገኛለን። ይሁዳዊነት፣ ክርስትና እና እስልምና ሁሉም ከአካባቢው ጋር ያላቸውን ጠንካራ ቁርኝት እና የታሪካቸው መነሻ ያያይዙታል።
ሙሁራን እንደሚያምኑት “ፍልስጤም” የሚለው ቃል አመጣጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ12ኛው ክፍለ ዘመን በአካባቢው ከሰፈሩት ፍልስጤማውያን ከሚለው የሕዝቡ መጠሪያ የተወሰደ ነው። አካባቢው ባቢሎናውያንን፣ ፋርሶችን እና ሮማውያንን ጨምሮ በአያሌ ኢምፓየሮች ወረራ ተፈፅሞበት ነበር። መጀመሪያ በሙስሊሞች ስር የገባች ሲሆን ይህም እየሩሳሌም በ629 ላይ በራሽዱን ካሊፌት እጅ በወደቀችበት ጊዜ ነበር። ነብዩ ሙሃመድ ከሞቱ አራት ዓመታት ካነሰ ጊዜ በኋላ መሆኑ ነው።
በመስቀሉ ጦርነቱ ወቅት ከምእራብ አውሮፓ የመጡ ክርስቲያን ወታደራዊ ኃይሎች፣ ሙስሊሞችን እና የአካባቢውን ክርስቲያኖች የሀይማኖቶቻቸውን ቅዱስ ስፍራዎች ለመቆጣጠር ወጓቸው። ከ1508 እስከ 1908 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት በኦቶማን ቱርኮች አካባቢውን እንዳስተዳደሩት ሂስትሪ ዶት ኮም ላይ ሰፍሯል።
አረቦቹ ‘ፊልስቲን’፣ አይሁዶች ‘እስራኤል’፣ በውክልና ያስተዳደሩት እንግሊዞች ደግሞ ‘ፓልስታይን’ ይሉታል። የፍልስጥኤም ምድር የቁርሿቸው ማጠንጠኛ ነው። ሁለቱም ለቦታው ያላቸው ስያሜ እንደመለያየቱ፣ ለአካባቢው ትናንት፣ ዛሬ እና መፃኢ እድሉ ያላቸው አመለካከትም ፍፁም ለየቅል መሆኑን ይጠቁማል። ስለሆነም ለአረቦች ፍልስጤም ማለት፣ ለዘመናት አፈሩን ሲያለሙት የኖረ የአያት የቅድመ አያቶቻቸው ርስት፣ የአረብ ምድር በመሆኑ እንደማንኛውም የአረብ አገር ሉዐላዊ ነፃነቱ ሊከበርለት ይገባል ባይ ነበሩ።
ሁለቱ ወገኖች አሁን የሚጋጩበት መሬት የኦቶማን ቱርክ ግዛት አካል የሆኑ የኢየሩሳሌም ሳንጃክ እና የቤሩቱ ቪላየት የሚባሉ ሁለት አስተዳደራዊ አውራጃዎችን የያዘ ነበር። በ1870ዎቹ ፍልስጤምም ሆነ እስራኤል የሚባል ሀገር አልነበረም። ምንም እንኳ በቱርኮች የህዝብ ቆጠራ ባይደረግም ከ600 ሺህ በላይ ሕዝብ ይኖር እንደነበር ይገመታል። ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት አረቦች ነበሩ። ከዚህም ውስጥ በአብዛኛው የሱኒ ሙስሊም ሀይማኖት ተከታይ ቢሆንም ቅሉ ቀላል የማይባል አናሳ ክርስቲያኖች ይገኙበት ነበር።
ከ1509 ዓ.ም ጀምሮ በምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን እና በግብፅ ያሉ የአረብ መሬቶች የኦቶማን ቱርክ ግዛት አካል ነበሩ። ኦቶማኖች በኃያልነት ዘመናቸው በመካከለኛው ምስራቅ አረብ፣ በሰሜን አፍሪካ እና በአብዛኛው የባልካን አካባቢዎች፣ በግዛቱ ስር ተጠቃለው ነበር፣ ግዛቱም ልዩ ልዩ የተሰባጠረ ማህበረሰብ እና እንደ አይሁድ እና ክርስትና የመሳሰሉ ሀይማኖታዊ ስብስቦች ታቅፈው ነበር። በአብዛኛው የግዛታቸው ክፍል ያደርጉ እንደነበሩት ብልጠት በተሞላበት እና በሰለጠነ ሁኔታ በመምራት የቱርኮቹ አስተዳደር ለአካባቢው መረጋጋት እና ሕብረት እንዲኖር አድርገዋል።
ነገር ግን በ1675 ዓ.ም ከቪየና ከተማ መከበብ በኋላ የኦቶማን ቱርኮች ግዛት በማፈግፈግ ውስጥ ነበር። በመጀመሪያ በሀብስበርጎች እንደገና መነሳት፣ ቀጥሎም በባልካን ብሔርተኞች አመፅ መቀጣጠል፣ እና በመጨረሻ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ተስፋፊነት የግዛት አድማሱ መመናመን ይዞ ነበር። ሆኖም እንኳ ኦቶማን ቱርክ በአብዛኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓውያን አስተዳደር ውስጥ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ነበረው። በመሆኑም የተማሩ አረቦች በዚህ ወቅት መላውን አውሮፓ በተቆጣጠረው የብሔርተኝነት መንፈስ መነካታቸው እርግጥ ነበር፣ ከቱርክ አገዛዝ ወጥተው ነፃ የአረብ ሀገር እንዲኖራቸው ይመኙ ነበር። እናም የአረብ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ መጀመሩን ታሪክ ያስረዳል።
‘እናንት አረቦች ተነሱ እና ንቁ’
በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የአረቡ ዓለም ጥልቅ በሆነ የለውጥ ምእራፍ ውስጥ አልፏል፤ ይህም በአንድ በኩል፣ የሚያኮራ ያለፈ ጊዜያቸውን ከመናፈቅ እና የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የፖለቲካዊ ውድቀት ምንጭ የሆነው የኦቶማን ቱርኮች ቅኝ አገዛዝ ለማስወገድ ትእግስታቸው ከመሟጠጡ እንዲሁም የምእራባውያን ህሳቤዎች ወረራ፣ በተለይ ከፈረንሳይ አብዮት፤ በሌላ በኩል በሚነሳ ግጭት ነው። የእነዚህ እውነታዎች መጣመር ወደ አንድ ከፍተኛ ተቀጣጣይ ብሔርተኝነት አድገዋል።
በ1906 ዓ.ም ከአረብ ብሔርተኝነት መቀጣጠል በፊት ቀደም ብሎ የተለያዩ ፖለቲካዊ ቡድኖች ተፈጥረው ነበር። በ20ኛው ክፍለዘመን በቱርክ የቱርክ ሞንጎል ወገን የሆኑ የቱርክ፣ ኢራን እና ሶቭየት ኅብረት የቱርክ ሞንጎል ማንነቶችን እንደ ገና በማሰባሰብ አንድ ቱራኒያን ሀገር ለመፍጠር የተጀመረ ብሔራዊ ንቅናቄ ነበር። በዚህ ንቅናቄ ውስጥ የአረብ አውራጃዎች እንዲካተቱ የኢስታንቡል ጌቶችን ስብከት ለመቃወም ነበር የአረብ በርከት ያሉ ፖለቲካዊ ቡድኖች የተመሰረቱት። እነዚህ ቡድኖች አንዳንዴ በባህል ውይም በማህበራዊ መሰረት ላይ የቆሙ ሲሆን፤ ነገር ግን በአብዛኛው ግልፅ በሆነ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ላይ የቆሙ ነበሩ።
የእንዲህ አይነት ቡድኖች መሪዎች፣ ግላድስቶን የተባለውን የወቅቱን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ግላድስቶንን ነፃነት፣ እኩልነት እና ብሔራዊ ሉዓላዊነት የሚሉ የፖለቲካ ፈለግ የተከተሉ ኃያል መርሆዎች ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ሊብራሎች ነበሩ። የሕዝቦችን ራስን በራስ በአግባቡ የማደራጀት እና ማህበራዊ ፍትህን እና የአረብ ትውፊቶችን በሚያጎላ አግባብ በመመስረት ዲሞክራሲን የመመኘት መብት አውጀው ነበር።
የአረብ ብሔራዊ ንቅናቄ ታሪክ የተከናወነው በ1839 ዓ.ም በሶሪያ ሲሆን በአሜሪካ ድጋፍ ስር አንድ ቀለም ቀመስ ማህበረሰብ ቤሩት ውስጥ በመመስረት ነበር። የዚህ ንቅናቄ ናሲፍ ያዚጂ እና ቡትሩስ ቦስታኒ የተባሉ ሁለት ግንባር ቀደም ሌባኖሳዊ አረብ ክርስቲያኖች ነበሩ።
በ1852 ዓ.ም ቦስታኒ ቤሩት ውስጥ በበቂ ሁኔታ አላማውን ገላጭ የሆነ፣ ክላሪዮን ኦፍ ፒየር፣ የተሰኘ ጋዜጣ መሰረተ። በሀገሪቱ ሲታተም ለመጀመሪያው ጊዜ የሚባልለት የፖለቲካ ጋዜጣ ነበር። በ1862 ዓ.ም ደግሞ ‘አልጀኒን’ የተሰኘ በየአራት ቀኑ የሚታተም ጋዜጣ መሰረተ፤ “አርበኝነት የእምነት አንዱ ምእራፍ ነው” የሚል መሪ መፈክር ሰጥቶት ነበር። ይህ በአረቡ ዓለም እስከዚያ ድረስ የማይታወቅ አመለካከት ነበር።
ከአሜሪካ ሚሲዮን ጋር ኅብረት በነበራቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት፤ ያዚጂ እና ቡስታኒ አንድ የተማረ ማኅበረሰብ የማቋቋም ምክረ ሀሳብ በመያዝ ወደፊት ተራመዱ። ፕሮጀክቱ “የሶሪያውያን ሳይንቲፊክ ሶሳይቲ” ህልው በሆነበት ጊዜ በ1849 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ብስለት አሳየ። ይህም የመጀመሪያው የአረብ ፖለቲካዊ መርሀ ግብር መሆኑን የሚገልፅ ነው። በሀገሪቱ እድገት የማየት ፍላጎት አላማቸው ነበር፤ ማህበራቸው በአረብ ቅርስ መኩራት ነበር። በዚህ መልኩ፤ ከዚህ ማህበረሰብ መመስረት ጋር ተያይዞ፤ የጋራ ብሔራዊ ሀሳብ ድምፅ የተስተስተጋባበት የመጀመሪያው ግልፅ ማሳያ ሆነ።
የትልቁ ናሲፍ ያዚጂ ልጅ፣ ኢብራሂም ያዚጂ የተባለው አንዱ የማኅበረሰቡ አባል በአርበኝነት ላይ ያተኮረ አንድ ግጥም ፃፈ፦”እናንት አረቦች ተነሱ እና ንቁ” የሚል። የግጥሙ ዋና ጭብጥ ለአረብ ዋስትና የሆነ ግልፅ ማነሳሻ ነበር።
በዚህ ደረጃ ላይ የአረብ ብሔራዊ ህሳቤ ገና በፅንስ ደረጃ መሆኑን እና “የሶሪያውያን ሳይንቲፊክ ሶሳይቲ” ራስን መቻል ዋነኛ ትኩረት እንዳልነበረ ማጤን ወሳኝ ነው። ይልቁንም አላማው የተወሰነ የነፃነት እመርታዎችን ማሳካት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መለሳለስ ጥቂት እንደቆየ በ1896ዓ.ም ፓሪስ ውስጥ ‘የአረብ ሀገር ሊግ’ ን በመሰረተው ናጅብ አዙሪ በተባለ አንድ ፍልስጤማዊ አማካይነት ጠንከር ያሉ አቋሞችን አገኘ። ናጅብ አዙሪ ከአንድ ዓመት በኋላ በታተመው፣ ‘ዘ አዌክኒንግ ኦፍ ዘ አረብ ኔሽንስ’ በተሰኘ መፅሐፉ ውስጥ ለአረብ ሀገራት ነፃነት አብዮታዊ መርሀግብሩን በይኗል። ይህም በሜዲትራኒያን ባህር በኩል አቋርጦ ከቲግሪስ እና ኤፍራተስ እና ከፐርሺያ ባህረ ሰላጤ እስከ ሳይናይ በርሃ የተዘረጋ አንድ የአረብ ግዛት እንዲኖር መሰረታዊ ጥያቄዎችን ያስተጋባ የመጀመሪያው አዋጅ ነው። ግብፅ በዚህ ክልል ውስጥ አልተካተተችም፣ ምክንያቱም ኗሪዎቹ ከአረብ ወገን አይደሉም በሚል መነሻ ነበር። በአዙሪ ሀሳብ መሰረት የአረብ ኢምፓየር፣ የአረብ ባህረገብን፣ ኢራቅን እና ፍልስጤምን ጨምሮ ታሪካዊቷን ሶሪያን ያካተተ ነበር። የአዙሪ ፕሮጀክት፣ በመጭዎቹ የአረብ ብሔርተኞች ያለልዩነት ተቀባይነት አግኝቷል። በአረብ ብሔራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አብይ መታጠፊያን አመላክቷል፣ ምክንያቱም የአረብ ሕዝብ መልከአምድራዊ ብያኔዎች ተሰጥቶት ነበር።
እነዚህ የአረብ ብሔርተኝነት ጅማሮዎች በብዙ መሰናክሎች መሀል በማለፍ እየተጠናከሩ ከቱርክ ነፃነታቸውን ለማግኘት ትግላቸውን አስፋፍተው እስከ ድል ተጉዘዋል። ነገር ግን ብዙ ጉድለቶች ስለነበሩት ጠንካራ የአረብ አንድነትን መፍጠር ሳይችል ቀርቷል። ፍልስጥኤማውያንም በዚህ የአረብ ብሔርተኝነት ትግል ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ቢያደርጉም እስከዛሬ የአረብ እስራኤል ግጭት ማዕከል በሆኑ ውስብስብ ሁኔታዎች እንዲያልፉ ግድ ሆኗል። ለመሆኑ የአረብ እስራኤል ግጭት ዋነኛ መንስኤዎች ምንድን ይሆኑ? በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተሰራው የፍልስጤም ድራማ ያስከተለው መዘዝ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎችን እንመርምር።
ይቀጥላል
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም