ሀሰተኛ ብር እና የሕግ ተጠያቂነት

0
152

መግቢያ

ገንዘብ የአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት ነው። በመሆኑም ማንኛውም መንግሥት የገንዘቡን ሕጋዊነት እና ተቀባይነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋል።

ገንዘብ በአንድ ሀገር ውስጥ መገበያያ (medium of exchange) ሰነድ መሆኑን የሚያስረዱት ደግሞ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት የገንዘብ ኖታቸውን የመወሰን ሉዓላዊ ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ የመገበያያ ገንዘባቸውን ይወስናሉ፡፡ ስለሆነም በሀገራችን ብር ሕጋዊ ገንዘብ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ ቁጥር 1359/2017 አንቀጽ 6 (15) መሰረት የኢትዮጵያ የሕጋዊ ገንዘብ ብር እንደሆነ እና ይህም የሀገሪቱ ሕጋዊ ገንዘብ እንደሆነ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የወረቀት ብር (የብር ኖት) ግብይት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ይሁን እንጂ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚዘጋጁ ወይም ሐሰተኛ የብር ኖቶች በተለያየ መንገድ በግብይት ወቅት ሲሰራጩ ይስተዋላሉ። ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ የሚቀበለውን ገንዘብ በጥንቃቄ የመመርመር እና ወንጀልን በጋራ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት አመላክተዋል።

የሐሰተኛ ገንዘብ ምንነት

ሐሰተኛ የብር ኖት ወይም ሐሰተኛ ገንዘብ ማለት በብሔራዊ ባንክ እውቅና ሳይኖረው ሕጋዊውን ገንዘብ በማስመሰል የሚሰራ ነው።

“ሀሰተኛ ገንዘብ ምን ማለት እንደሆነ በወንጀል ሕጋችን ላይ ትርጉም አልተሰጠውም” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ፤ ሀሰተኛ ገንዘብን አስመልክቶ ከተደነገጉት የወንጀል ድንጋጌዎች ይዘት በመነሳት ሀሰተኛ ገንዘብ ማለት ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ እንዲያገለግል በሕግ የመገበያያ ገንዘብ የመስራት ወይም የማሰራት ሥልጣን ባለው አካል አማካኝነት ወይም ፍቃድ ሰጭነት ከተሰሩት የመገበያያ ገንዘብ ጋር ተመሳስለው የተሰሩ ወይም ፍቃድ በሌለው አካል ሙሉ ለሙሉ ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ ሆነው የተሰሩ የብር ኖቶች መሆናቸውን ያብራራሉ።

ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ መሰረት ከባድ ወንጀል ሲሆን ይህንን ገንዘብ ያዘጋጀው አካል ብቻ ሳይሆን ገንዘቡን ይዞ የተገኘው ሰው ጭምር በሕግ የሚጠየቅበት ሁኔታ ተደንግጓል።

የሀሰተኛ ገንዘብ ጉዳቶች

የኑሮ ውድነትን (inflation ) ያባብሳል፣ ማህኅበረሰቡ በመገበያያ ገንዘብ ላይ ያለውን ዕምነት እና ጤናማ የሆነ የገበያ ሥርዓት ላይ  ጉዳት ያደርሳል፡፡ ሕገ ወጥ የሀብት ክምችትን ይፈጥራል፣ የሀገሪቱ ገንዘብ ተአማኒነት ሲያጣ ሰዎች በባንክ እና በገንዘቡ ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር የምጣኔ ሀብት ውድቀትንም ያስከትላል።

የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች

በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 359 ጀምሮ እስከ 362 ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ሀሰተኛ ገንዘብን የመስራት እና የማዘዋወር የወንጀል ድርጊቶች እና የሚያስቀጡ የቅጣት መጠን ተደንግገው ይገኛሉ፡፡

  • ሀሰተኛ ገንዘብ መሥራት

በብሔራዊ ባንክ አዋጅ ቁጥር 1359/2017 አንቀጽ 6 (1 እና 2 ) መሰረት የወረቀት ብሮችን እና ሳንቲሞችን የመቅረጽ፣ የማተም፣ የማስቀረጽ፣ የማሳተም፣ የማሰራጨት፣ የማስወገድ እና እንዲወገዱ የማድረግ ብቸኛ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው። በመሆኑም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 356 ሕጋዊ መገበያያ የሆኑትን ገንዘቦች ያለፍቃድ መስራት ወይም አስመስሎ መስራት ከአምስት ዓመት በማያንስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

  • ወደ ሀሰተኝነት መለወጥ

በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 357 መሰረት ሕጋዊ ገንዘብን ከትክክለኛው ዋጋቸው በላይ እንዲዘዋወሩ ለማድረግ በማሰብ መልካቸውን መለወጥ፣ እውነተኛ መልካቸው ላይ ሌላ ነገር መጨመር፣ ቀለማቸውን መለወጥ ወይም ሌላ ማናቸውም አይነት ዘዴን በመጠቀም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ወደ ሀሰተኝነት መለወጥ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡

  • ዋጋውን ዝቅ ማድረግ

በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 358 መሰረት በኬሚካል፣ በፊዚካል፣ መካኒካል ወይም ማናቸውንም ዘዴ ተጠቅሞ ሕጋዊ የሆኑትን ገንዘቦች ዋጋቸው ዝቅ እንዲል ማድረግ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ ይህ ወንጀል በሀገራችንም ሆነ በውጭ ሀገር ቢፈጸም የሚያስቀጣ ነው፡፡

  • ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ከአገር ማስወጣት፣ ይዞ መገኘት፣ ማስቀመጥ እና ማቅረብ

በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 359 ሀሰተኛ የሆኑ ወይም ዋጋቸው ዝቅ እንዲል የተደረጉ ገንዘቦችን እውነተኛ እንደሆኑ ወይም ሙሉ ዋጋቸውን እንደያዙ አስመስሎ ራሱ እንዲገበያይባቸው ወይም እንዲዘዋወሩ ለማድረግ በማሰብ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ ከሀገር ማስወጣት እንዲሁም ይዞ መገኘት፣ ማስቀመጥ እና ማቅረብም ጭምር ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡

  • ማዘዋወር

በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 361 ላይ እንደተደነገገው ሀሰተኛ የሆኑትን ወይም ወደ ሀሰት የተለወጡትን ገንዘቦች እውነተኛ አስመስሎ ወይም ከተወሰነው በላይ ዋጋ እንዳላቸው አስመስሎ በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም ከሀገር ውጭ ማዘዋወር ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ የተቀነሰውን ገንዘብ ሙሉ ዋጋ እንደያዙ አስመስሎ ማዘዋወር ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም ቅጣት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እንደተገለፀው ወንጀል አድራጊው ገንዘቡን እውነተኛ ነው በሚል እምነት ወይም በትክክለኛው ዋጋው ከተቀበለ በኋላ ሀሰተኛ መሆኑን እያወቀ ከኪሳራ  ለመዳን ሀሰተኛውን ወይም ወደ ሀሰት የተለወጠውን ገንዘብ ያዘዋወረ እንደሆነ በቀላል እስራት ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም ዋጋው የተቀነሰውን ገንዘብ ሙሉ ዋጋው እንዳለ በማስመሰል ያዘዋወረ እንደሆነ ተጠያቂ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 360 እነዚህ ከላይ የተገለፁት ወንጀሎች በገንዘብ ኖቶች ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ከተፈጸሙ ሕጉ ድርጊቱ የተፈጸመው የሀሳብ ክፍል እንዳለ ግምት ይወሰዳል፡፡ በመሆኑም ዐቃቢ ሕግ በሚያቀርበው ክስ ማስረዳት የሚጠበቅበት ግዙፋዊ ፍሬ ነገር መፈጸሙን ብቻ ነው፡፡ የሀሳብ ክፍሉን የማስረዳት ሸክም ያለበት ተከሳሽ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 362 መሰረት ከላይ የተገለፁት ወንጀሎች የተፈጸሙበት የገንዘብ መጠን ማነሱ ከወንጀል ተጠያቂነት አያድንም፡፡ ሕጉ ባስቀመጠው መሰረት የገንዘቡ መጠን ትንሽ ከሆነ ቅጣቱ ቀላል እስራት ይሆናል፡፡

  • በገንዘብ ላይ አደጋ ማድረስ

በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 370 እና 371 እንደተመላከተው እነዚህን የሀሰት ገንዘብ ከመስራት ጋር በተገናኘ ሌላው  መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ሰው አግባብ ያለው ባለስልጣን  በግልፅ ሳያዝዘው ለገንዘብ ማተሚያ ወይም መሥሪያነት የሚያገለግሉትን የመሳሪያ ፎርሞች፣ ወረቀቶች፣ ሞዴሎች እና መሰል እቃዎችን የሠራ፣ ከእጁ ያስገባ፣ ወደ ሀገር ያስገባ ወይም ያስወጣ፣ ለሌላ ሰው ያቀረበ ወይም አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ እንዲሁም እነዚህ ገንዘብ እንዲሠሩ የሚሰጡ ትዕዛዞችን የተቀበለ፣ የፈጸመ፣ ያስፈጸመ፣ ለሌላ ሰው ያስረከበ እንደሆነ በቀላል እስራት እንደሚቀጣ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በአንቀጽ 779 መሰረት በሀሰት የተዘጋጀ ወይም ወደ ሀሰት የተለወጠ ገንዘብ በእጁ የገባ ሰው ገንዘቡ የመጣበትን ሁኔታ ካወቀ ይህንን ወይም የሀሰት ገንዘቡ በእጁ የሚገኝ መሆኑን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳይዘገይ ካላስታወቀ እና ገንዘቡን ካላስረከበ በገንዘብ ቅጣት ወይም በእስራት እንደ ሚቀጣም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ማንኛውም ሰው እያወቀ ወይም ማወቅ እየተገባው ሀሰተኛ ገንዘብ ያስቀመጠ፣ የያዘ እና ለግብይት ያዋለ እንደሆነ እስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣ የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል ነው ያሉት፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሀሰተኛ የብር ኖት ይዞ መገኘት እና መጠቀም ቀለል ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ሕጉ የሀገርን ኢኮኖሚ እና የዜጎችን ጥቅም ለመጠበቅ ሲል በዚህ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ወይም ተባባሪ የሆኑ አካላትን በእስራት እና በገንዘብ ይቀጣል።

ስለሆነም ማንኛውም ሰው ሀሰተኛ ገንዘብን ከመስራት እና ከማዘዋወር የወንጀል ድርጊት ሊቆጠብ እና ከወንጀል ተጠያቂነት ሊድን የገባል።

የሕግ አንቀጽ

የሕገ መንግሥት የበላይነት መርህ

ሕገ መንግሥት መሠረታዊ እና ወሳኝ ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ እና በሕዝብ የሚጸድቅ ቃል ኪዳን ስለሆነ ከሌሎች ሕጎች ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 እንደተደነገገው ሕገ መንግሥት ማለት የሀገሪቱ የበላይ ሕግ እና በሀገሪቱ ለሚወጡ ሕጎች ሁሉ መነሻ ምንጭ ሆኖ የተቀረጸ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የመንግሥት አካል ወይም የባለሥልጣን ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል ሲሆኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጩ ከሆነ ተፈፃሚነት የላቸውም፡፡ በዚህ መርህ መሠረት ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ተቋማት ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን እና የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 . ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here