“ሀይ ባይ ያጣው” የባሕር ዳር የዝርፊያ ወንጀል

0
213

የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እንደማንኛውም ሕግ የራሱ የሆኑ መሠረታዊ መርሆዎች አሉት:: ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ መርህ አንዱና ዋነኛው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ ሲሆን በቀጥታ ከወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ዓላማ ጋር የሚገናኝ ነው::

የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ዓላማ የመንግሥት ፣ የሕዝብ እና የግለሰቦችን ደህንነት እና ሰላም ማስጠበቅ መሆን አለበት የሚል መሠረታዊ ሐሣብ ላይ የተመሠረተ ነው :: በዚህም የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቶችን የሚገዛ ነው::

ንፁሐን ከአጥፊዎች በአግባቡ የሚለዩበት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ከፈፀሙት ጥፋት ጋር ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያገኙበት ፣ ለጥፋታቸው ኃላፊነት መውሰዳቸው የሚረጋገጥበት እና በወንጀሉ የተፈጠሩትን ችግሮች በማስወገድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የሕብረተሰቡን እና የመንግሥትን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ መቻል አለበት ሲል ፍትሕ ቢሮ የሰዎችን ደህንነት እና ሰላም ለማስከበር ሕግ እና ሕገ መንግሥትን መሰረት አድርጎ ይጠቅሳል ::

ይሁን እንጂ ይሄ ሕግ ባለበት ሀገር  ብሎም የመንግሥትን ሕግ እና ሥርዓት የሚያስከብሩ የፀጥታ አካላት እና ተቋማት ባሉበት በባሕር ዳር ከተማ በማንኛውም ሰዓት የዝርፊያ ወንጀል በጦር መሳሪያ ጭምር በመታገዝ እየተፈፀመ በመሆኑ ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸዋል::

ወ/ሮ ማንጠግቦሽ ሙሉ በጠዋት ወደ  ሥራ ለመሄድ ታክሲ ለመያዝ ከጠዋቱ አንድ ሰአት አካባቢ ወደ አመልድ አካባቢ ሲደርሱ በወቅቱ ባገኙት ዳማስ የተባለ ተሽከርካሪ ተሳፍረው ትንሽ እንደተጓዙ ‘እትዬ ተሽከርካሪው ተበላሸ ይውረዱ’ ብለው ሲያስወርዷቸው ቶሎ ብለው ስልካቸውን ሲመለከቱ ባለመኖሩ ለመከተል ያደረጉት ጥረት  ባይሳካም ለሚመለከተው የፀጥታ አካል አመልክተው ተመላልሰው መልስ ቢጠይቁም የወንጀለኞቹ አለመያዝ ፣ ስልካቸው አለመመለሱ እንዳሳዘናቸው እና ሌላ ስልክ ገዝቶ ለመያዝም ፍራቻ እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ::

ሌላው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተበዳይ ደግሞ በፍኖተ መስመር እየሄዱ እና ወደ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ በባጃጅ ያሉ ወጣቶች ሁለት በመሆን አስቁመው ያላቸውን ሁሉ እንደወሰዱ ገልጸዋል፤ የተቀሙበት ሰዓት ያልመሸ (ሰው በሚንቀሳቀስበት ሰዓት) ከመሆኑ ውጭ በሰዓቱ ለሚመለከተው የፓሊስ አካል ችግራቸውን ቢነግሩም የፀጥታ ችግሩ አለመፈታቱን ገልፀዋል::

በአካባቢያቸው ከግለሰብ አልፎ በመኪና የታገዘ እና የተደራጀ የግለሰብ ቤትንም ጭምር ዘረፋ ከሰሞኑ በድጋሚ መፈፀሙ ደግሞ ምንም ዓይነት ችግር በህብረተሰቡ ላይ ቢደርስ ለችግሩ መፍትሄ ይመጣል ፣ የጸጥታ አካሉ ይተባበረናል የሚል እምነት እየጠፋ መምጣቱን  ይናገራሉ::

በከተማው ሁሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ የስርቆት ወንጀሉ በባጃጅ እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ፣ በጦር መሳሪያ ታግዞ የሚፈፀም መሆኑ ደግሞ ሰዎች ሲዘረፉ ከጠፋባቸው ንብረት ይልቅ ለነፍሳቸው መትረፍ ብቻ እንዲጨነቁ የሚያደርግ እና በሰላም ወጥቼ እገባለሁ የሚል በራስ መተማመንን የሚነጥቅ ተግባር መፈፀሙ የከተማዋን ሰላማዊ ገፅታ እያበላሸው መሆኑን በመጥቀስ ነው::

በቀበሌ አራት ዋናው ገበያ ለምለሚቱ ጎጃም (ባህርዳር) ህንፃ አካባቢ ከሚያልፍ የጭነት መኪና ጭነት እያንከባለሉ ሲያወርዱ ከረዳቱ በስተቀር ተዉ የሚል መጥፋቱን የታዘቡት ደግሞ በዛው በንግድ ሥራ የተሰማሩ ግለሰብ ሰዎች ተረባርበው እንዳያስጥሉ በተናጠል የሚደርስባቸውን በቀል በመፍራት ችላ ማለታቸውን ተናግረዋል::

በወንጀል ተከሰው የተያዙ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ቅጣት አስተማሪ ቢሆን እና ጠንካራ የሕግ ቁጥጥር ቢኖር የመቀነስ እንጂ የመጨመር ሁኔታ የማያሳየው የዝርፊያ ወንጀል በጦር መሳሪያ ጭምር ታግዞ በየጊዜው ሲፈፀም ሕግ እና የፀጥታ ተቋማት የት አሉ ያስብላል?  እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ችግሮቹን በመከታተል እና መፍትሄ በመስጠት ምን ሠራ? ስንል ጠየቅን::

የባሕር ዳር ከተማ ፓሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር  ዋለልኝ ቢምረው ከተፈጠረው ክልላዊ ችግር ጋር ተያይዞ  ስርዓት አልበኝነት እና የወንጀል ድርጊቶች በከተማው እየተፈፀሙ መሆኑን አረጋግጠውልናል::

በባጃጅ ሆኖ ስርቆት መፈፀም ፣ ማታለል፣ ፣ማጭበርበር እና ማጅራት መምታት እየተፈፀመ ነው:: አሁን ችግሩን ለማስቆም በሰፊው እየተሠራ ቢሆንም ሙሉለሙሉ ችግሩን ማስቀረት አልተቻለም:: እስካሁን ከ40 በላይ የወንጀል ተሳታፊዎች ተይዘዋል ፤ እነዚህ ሰዎች ባጃጅም ትጥቅም የያዙ ናቸው ፤ ለሕግ ቀርበዋል:: ቀጣይም ለመያዝ ከህብረተሰቡ ጋር እየተሠራ ሲሆን አሁን አሁን ህብረተሰቡ በብሎክ እየተደራጀ አካባቢውን እንዲጠብቅ እየተደረገ ነው::

አሁን በቀን በባጃጅ እየተፈፀመ በመሆኑ ለማስቆም እየተሠራ ቢሆንም ስላልቆመ የህብረተሰቡ ቅሬታ ተገቢ ነው :: የተፈጸሙ ችግሮችን እና ወንጀለኞችን በማጥናት ክትትል ላይ ስለሆንን በማሕበረሰቡ ትብብር በቀጣይ የሚያዙ ወንጀለኞችም እንደሚኖሩ ኮማንደር ዋለልኝ ተናግረዋል::

ህብረተሰቡ ወንጀል ሲፈፀም እና ሲያይ፣ የተጠቀሙበትን ተሸከርካሪ ሰሌዳ ለፓሊስ ጥቆማ በመሥጠት እና ስምሪት ውስጥ ያልገቡ ባጃጆችን ባለመጠቀም ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት::

ከወረዳ የተለያየ አካባቢ የገቡ በርካታ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ስላሉ እስካሁን ከ100 በላይ የገቡትን ሰሌዳ ፈትቶ የሚንቀሳቀስ ወደ 30 ባጃጅ በፓሊስ ቁጥጥር ስር ቢያዝም ወንጀሉ ስለቀጠለ በቂ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል::

ወንጀል ለመጠቆም ህብረተሰቡ ወደ ፓሊስ ጣቢያ ሲኬድ ደግሞ ‘በቂ የፓሊስ ሃይል የለንም’ የሚል የቸልተኝነት መልስ እየተሰጠ ስለሆነ በፓሊስ በኩል በቂ ሃይል የለም ወይ ? ብለን  ላቀረብነው ጥያቄ “ከተማ ውስጥ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እና ሌቦችን ለመያዝ ያን ያህል የሚባል ችግር የለብንም ይሄ ፓሊስ የራሱ የመምራት ችግር ነው  ” ያሉት  ኮማንደር  ዋለልኝ እንደ ባሕር ዳር ከተማ ከሚያስፈልገው ደረጃ(መስፈርት) አንፃር ግን  የሚመጥነው የሰው ሃይል አለ ማለት አይቻልም ብለዋል::

ከነችግሩም ቢሆን ሥራውን ለመሥራት በሚያስችል ሁኔታ የስርቆት እና ማጅራት መምታት ወንጀሎችን እንፈታለን ብለው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here