ቻይና ሰፊ፣ የበለፀገ የታሪክ እና የባህል ብዝሃነት የታደለች ምድር ናት:: በዚህ ጽሑፍ እጅግ ሰፊ እና ብዙ መልካም ነገር በጉያዋ የያዘችውን ቻይናን እንጐበኛለን:: በጉብኝታችን ወደ መዲናዋ ቤጅንግ ሻንጋይ በማቅናት ታላቁን የቻይናን ግንብ (the Great wall of china) ጨምሮ ጥንታዊዎቹን ከተሞቿን ቅርሶች፣ የቲያሚን አደባባይን እና የገነት መቅደስን እንቃኛለን::
ቤጅንግ አስደማሚ ከተማ ናት:: ቻይና ጐራ ብለን ቤጅንግን አለመጐብኘት አንችልም:: የፓንዲንግን ሰማይ ጠቀስ ህንፃ፣ ብርቅየውን እንስሳ ፖንዳን ማየትም ግድ ነው::
መቸም ሀገረ ቻይናን ለመጐብኘት ያቀደ ሁሉ ታሪካዊ ቦታዎቿን፣ ተፈጥሯዊ መልክአ ምድሯን፣ ትናንትን ከዛሬ ጋር ያስተሳሰሩ ባህላዊ ቅርሶቿን፣ 21ኛውን ክፍለ ዘመን እንደመስታዎት የሚያሳዩ የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ተቋማቷን ለመጎብኘት መሻቱ አይቀሬ ነው::
ታላቁ የቻይና ግንብ በዓለም እጅግ ከታወቁ ቅርሶች መካከል ቀዳሚዉ ነው:: መቸም ሀገረ ቻይናን የረገጠ ጎብኝ 13ሺህ ማይል የሚያቆራርጠውን፣ እንደ ዱላ ቅብብል ትውልድ በቅብብሎሽ የገነባውን እና አሻራውን ያስቀመጠበትን ይህን ቅርስ ማየቱ ግድ ነው:: የጥንት የቻይና ነገሥታት ከወራሪዎች ለመከላከል የገነቡት ጠመዝማዛው ግንብ የታላቋ ቻይና መገለጫ ለመሆን በቅቷል::
በዚህ አካባቢ ጧት ማታ በብዛት የሚስተዋለው ጎብኚ አስደናቂውን ጥንታዊ የምህንድስና ጥበብ ከማድነቅ ባለፈ ዙሪያ ገባውን የሚያስቃኘው ገዥ ምድር መሣጭ ነው:: ለሁሉም ታላቁን የቻይና ግንብ ( the Great wall of china) በአካል ለመጐብኘት የተዘጋጀ ምቹ ጫማ እና አልባሳት መልበሱን፣ የሚጐነጨው ውኃ እና የፀሐይ መከላከያ መነፅር ማድረጉን መርሳት የለበትም::
ሀገረ ቻይናን ስንጐበኝ ብርቅየውን የቻይና እንስሳ ፓንዳን እንድንመለከት ወደ ፓርኮች ጐራ ማለታችን አይቀሬ ነው:: የፓንዳ ተመራጭ ምግብ የከርቀሀ ቅጠል ነው:: ፓንዳ የሚኖረው በማእከላዊ ቻይና ተራሮች ነው:: ይህን ውብ እንስሳ የጎበኘ ማንም ጐብኚ ከጉብኝቱ በኋላ ፓንዳን ከቻይና ጋር ማስታወሱ ግድ ነው::
የረዥም እና ውስብስብ የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤቷ ቻይና እንደ ጥንቱ ዛሬም ብርቅ እና ድንቅ ሀገር ናት::
ቅድመ ታሪኳን ወደ ኋላ እንበለውና የጥንታዊቷን ቻይና ታሪክ ሥልጣኔዋ ከፈነጠቀበት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2100 እስከ 221 ጀምረን ብንፈትሽ እንደ አብዛኛው ጥንታዊ ሥልጣኔ የቢጫ ወንዝ ወይም (yellow river) የተባለው ሥልጣኔዋ በታሪክ ይጠቀሳል:: ቻይናን የሚጐበኝ፣ መረጃዎችን እና መጽሐፎችን የሚያገ ላብጥ ሁሉ ይህን ሀቅ ይረዳል::
ከቢጫ ወንዝ ማዶ ሰሜናዊ ቻይና የቻይና ሥልጣኔ መሠረት ነው ማለት ይቻላል:: የሻንግ እና ዞሆ ሥርዎ መንግሥትም ከቻይና ማዕከላዊ መንግሥት ምስረታ ጋር ይነሳሉ::
ስለ ቻይና ሲወሳ ስለ ኦፒየም ጦርነት (the opium war) (1839 – 1860) አለማንሳት አይቻልም:: ይህ ታሪካዊ ጦርነት በቻይና እና ብሪታኒያ መካከል የተካሄደ ነው:: የኋላ ኋላም የቻይና የባሕር በሮች እና የውጭ የንግድ መስመሮች የውዴታ ግዴታ እንዲከፈቱ ምክንያት ሆኗል:: ይህ ወቅት ብሪታኒያ ሆንግ ኮንግን የከጀለችበት ዘመንም ነው::
ስለ ቻይና ሲወሳ የማይታለፈው ሌላው ቁም ነገር በቻይና ብሄራዊ ፖርቲ (ኮሚንታንግ) እና በቻይና ኮሚኒስት ፖርቲ መካከል የተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ነው:: በጦርነቱ ፍጻሜ ኮሚኒስቶች ድል ቀንቷቸው በ1949 የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በማኦ ዜዱንግ ተመሥርቷል:: የዛሬዋ ገናና፣ ሥልጡን ሀገር ቻይና የመሠረት ድንጋይ የተጣለውም ያን ጊዜ ነው፤ በሊቀ መንበር ማኦ ዜዱንግ::
ቻይናን ከጐበኜን አይቀር ዝነኛውን የባህል አብዮቷን አለማንሳት አንችልም:: ይህ ዘመን (1966 -1976) ለአሥር ዓመት ገደማ ነው የቆየው:: ከባህል አብዮቱ ጠንሳሾች መካከል ደግሞ ግንባር ቀደሙ ማኦ ነው:: የባህል አብዮቱ የኮሚኒስት ፖርቲውን ባለንጣዎች ከቻይና ለማጽዳት ነው የተወጠነው::
የቻይና የምጣኔ ሀብት ተሀድሶ በማኦ ጀምሮ በተከታዩ ፕሬዝዳንት ዴንግ ዚያፒንግ ቀጥሏል:: ከማኦ የሥጋ እረፍት በኋላም የቻይና ለውጥ እና የዕድገት ግስጋሴ አልቆመም:: ትልቁ እና ፈጣኑ የዓለም ምጣኔ ሀብት ጉልህ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥም አስከትሏል::
የሀገረ ቻይና ታሪክ አካል የሆነው የሆንግ ኮንግ ጉዳይ ደግሞ ማንኛውንም ጎብኝ የሚስብ ነው:: በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በብሪታኒያ ስር የነበረችውን ሆንግ ኮንግን ቻይና ሉአላዊ አካሏ አድርጋ በ1997 ተረክባታለች:: እንዲሁም ማካኡ የቻይና ልዩ ግዛት ስትሆን ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እ.አ.አ እስከ 1999 የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ሆና ቆይታለች:: አሁን እንደ ሆንግ ኮንግ ሁሉ ማካኡም አንድ ሀገር፣ ሁለት ሥርዓት እና ፖሊሲ በሚለው መርህ የቻይና ሉአላዊ ግዛት ናት::
ቻይና ዛሬ ከዓለማችን ባለፀጋ ሀገራት አንዷ ናት:: በባህል እና ቅርስ የዳበረው ሥልጣኔዋ፣ ፈጣኑ ማህበራዊ ዕድገቷ የቻይና መገለጫ ነው:: ትናንት እና ዛሬ የየራሳቸውን ታሪክ እያስመዘገቡ ቀጥለዋል::
ቻይና ዛሬ በዓለም ላይ ከባድ ተፅእኖ ካሳደሩ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት:: የቻይና ምጣኔ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ፣ፖለቲካ እና ባህል በሚገርም ሁኔታ እየተንሰራፋ ነው:: ምጣኔ ሀብቷን እንኳ ብንወስድ በምድራችን ሁለተኛውን ትልቅ ምጣኔ ሀብት ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ እየመራች ትገኛለች:: ላለፉት ጥቂት አሥር ዓመታት ፈጣኑን የምጣኔ ሀብቷን ዕድገት የገታው አልነበረም:: በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጐቿን ከድህነት በማላቀቅ ተአምር ፈጥራለች:: በቻይና የተሠራ (made in china) የሚለው የሸቀጣ ሸቀጦች መለያ ዛሬ የትም የሚገኝ ጽሑፍ ነው፤ በዚህም ሀገራት ወደ ቻይና እያማተሩ ነው::
ቴክኖሎጂን ስናነሳ ደግሞ በቴክኖሎጂ ፈጠራ በተለይ በዘመናዊ ሰው ሠራሽ አስተውሎት AI (Artificial Intelegence) ዘርፍ ቻይና ልቃ ሄዳለች:: ንግድም ሆነ ማህበራዊ መስተጋብሯ በዚህ ቴክኖሎጅ መመራት ከጀመረ ስነባብቷል:: በቻይና ታዋቂዎቹ ሁዋዊ፣ አሊባባ፣ ቴንሰንት እና ዚዮሚ ከቻይና አልፈው ዓለም ያወቃቸው ፀሐይ የሞቃቸው ኩባንያዎቿ ምርት እና አገልግሎት እፁብ ነው::
የቻይና የውጭ ግንኙነት ደግሞ ዓለም አቀፍ ትኩረት ያገኜ ነው፤ በተለይ ደግሞ ከቤልት ኤንድ ፖንድ (Belt and Pond) ዓለምን የማስተሳሰር እቅዷ ጋር:: ይህ እቅዷ ሀገራት በቻይና በኩል እንዲገናኙ እና እንዲተባበሩ ያለመ ነው::
የበለፀገው እና የዳበረው የቻይና ባህል ጥንታዊ እንዲሁም ረዥም ታሪክ አለው:: ሥነ ጽሑፏ፣ ኪነ ጥበቧ፣ ትውፊቷ… ለዛሬዋ ቻይና መሠረት ነው:: የቻይና ሲኒማ እና ሙዚቃም ዛሬ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እያገኘ ነው::
የመረጃ ምንጫችን፡- ብሪታኒካ፣ የቻይና ስቴት ካውንስል
(ታደሰ ፀጋ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


