“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት”

0
111

“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቀን በአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ አዘጋጅነት ተከበረ።

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ እንደተናገሩት 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሕገ መንግሥት እና ፌዴራሊዝም ዙሪያ በተመረጡ እና በጥናት በተደገፉ ርዕሰ ጉዳዮች በመወያየት እየተከበረ ይገኛል፡፡ ይህም ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱን ለማጠናከር አጋዥ የሆኑ የአስተምህሮ ሥራዎችን ለሁሉም የሀገራችን የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚደርስበት አግባብ የሚከናወን መሆኑን ነው ያስታወቁት።

በዓሉ በክልል ደረጃ በስፖርት፣ በትምህርት ቤቶች ጥያቄ እና መልስ፣ የአቅመ ደካማዎችን ቤት በመጠገን እና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች፣ በፖናል ውይይት እና በሌሎች በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

ቢሮ ኃላፊዋ አክለውም በዓሉን ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንድነት፣ በመተሳሰብ እና በመከባበር ማክበር ሀገራዊ አንድነት ይፈጥራል ብለዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ማብራሪያ በዓሉ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን፤ ትስስርን እና አንድነትን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቱባ ባሕሎቻቸውን እና  ዕሴቶቻቸውን የሚያስተዋዉቁበት መድረክ ነው።

ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ አክለውም “የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን በአንድነት ማክበር ውበታችን እና ጌጣችን ነው፤ ሁላችንም አንድነታችንና የክልላችንን ሠላም በማስጠበቅ ግንኙታችን በማጠናከር ሀገራችን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መሥራት አለብን” ብለዋል።

በተመሳሳይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት የበዓሉ ክልላዊ የማጠቃለያ ፕሮግራም በጎንደር ከተማ ተከናውኗል፤ በዚህ ጊዜ አቶ አገኘሁ እንዳሉት ብዝኃነት በአግባቡ ከተስተናገደ ለሀገራዊ መግባባት እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መሠረት ነው፡፡

ብዝኃነት ለልዩነት ምንጭ እንዲሆን ባለፉት ጊዜያት ሲቀነቀን መቆየቱን የተናገሩት ዋና አፈ ጉባዔው ይህም ለሀገር አንድነት ፈተና ሆኖ መቆየቱን አክለዋል፡፡ ለችግሮቹ መፍትሔ ለማበጀት ታዲያ መሰብሰብ፣ መወያየት፣ መመካከር እና መግባባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ አብሮነት የጋራ ራዕይ ያላቸው ማንነቶች የሚፈጥሩት የመስተጋብር ውጤት መሆኑን በማንሳት ይህም በመተሳሰብ እና በመቻቻል የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ የሚቻልበት መንገድ ነው ብለዋል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር30ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here