ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ!

0
155

የአንድ ሀገር  ዜጎች ጠላት እና ወገን ተባብለው ሲታኮሱ እና ሲገዳደሉ  ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ሶስት ዓመታትን ተሻገረ። በእርግጥ በኦሮሚያ ክልል ከሶስት ዓመት ቀደም ብሎም  ግጭቱ ተጀምሮ ነበር።  ኢትዮጵያ በጦርነት እና ግጭት ምክንያት ጉዞዋን ወደ ሗላ አድርጋለች። የትምህርት ቤት በሮች  የተማሪ ማዕከል ሳይሆኑ የጦር ምሽግ ሆነዋል። በጤና ተቋማት ከወላድ እናቶች ይልቅ በጦርነት የቆሰሉት  ለመታከም በዝተው እየታዩ ነው።

የሀገሪቱ ተቋማትም  በጦርነት እና ግጭቱ ምክንያት ተልዕኳቸውን በአግባቡ መፈፀም ተስኗቸው የሕዝብ አመኔታ እያጡ እና የመፈፀም ብቃታቸው እየወረደ ይገኛል። ሀገር ተቋም ከሌላት፣ ስርዓቷ ከተናጋ፣ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል  ያለው ግንኙነት ከሻከረ  ለመንግሥታዊ ውድቀት እንደተጋለጠች ማሳያ ይሆናል።

የንግግር ጆሮ ተደፍኖ በየቀኑ አስከሬን ሪፓርት  ማድረግ የሰርክ ዜና ሆኗል ። ተደመሰሰ፣ ተከበበ፣ ተማረከ፣ እንዲህ ሆነ እንዲያ ሆነ የሚለው  ዜና በርክቶ እየተሰማ ነው። ይህ በዛሬም ሆነ በታሪክ  ጥቁር ነጥብ የሚያስቀምጥ ሁነት ነው።

በመገዳደል፣ በመተኳኮስ፣ በመቧደን፣ በሴራ፣ በፍረጃ ዘላቂ የሀገር ሰላም የሚመጣ ቢሆን ከደቡብ ሱዳን እስከ ሶማሊያ፣ ከየመን እስከ ኢራቅ፣ ከኮንጎ እስከ ሊቢያ ሰላማቸውን ባገኙ ነበር።  ጦርነት ሐብትን እና ሰውን በልቶ ሀገርን የሚጥል የክፉ ፖለቲካ ውጤት ነው። በተለይ የዕርስ በዕርስ ጦርነት ሲሆን ደግሞ ያለአንዳች ድል ኪሳራው ይበዛል።

በአማራ ክልል አስቸኳይ አዋጅ ታውጆ ለአስር ወራት ዘልቆም ሰላሙ በተሻለ ሁኔታ አልተገኘም። አሁንም የአርሶአደሩ ቀዬ የበሬ እና የጅራፍ ጩኸት ሳይሆን በመሳሪያ ጩኸት እየታወከ ነው። መንገዶች ለመጓዝ አስተማማኝ አይደሉም። የጦርነት እና የግጭት ስሜቱ የመጋጋል እንጅ የመስከን ሁኔታ ብዙ አልታየበትም። በመሆኑም  ችግሩ ፖለቲካዊ በመሆኑ ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት ተገቢ ነው።  በውጊያ  አንድ ሀይል ቢያሸንፍ እንኳ  በጠቅላላ ሀገር ላይ የሚኖረው ኪሳራ ከባድ ነው። ሁሉም ወገን የሚያሸንፍበት ፖለቲካዊ  ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር  ነገሩ ሁሉ የእንቧይ ካብ ነው የሚሆነው። ባለቅኔው  ዮፍታሔ  ንጉሴ

“ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ

ነገራችን  ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ” እንዳለው ትብብር እና የሁሉም ወገን ይሁንታ የሌለበት አጥር ሲናድ እንደ እንቧይ ካብ ነው። ትብብር፣ አብሮነት እና ወላዊ (የጋራ) ተጠቃሚነት የሚመጣው ደግሞ በሀቀኛ ንግግር፣ ውይይት፣ ድርድር እንጂ በመተኳኮስ አይሆንም።  የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የጤና ተቋማት የሕዝብን ጤና እንዲጠብቁ፣ ጠብመንጃ የያዙ እጆች ወደ ዶማ መጨበጥ እንዲመለሱ፣ ነጋዴው እንዲነግድ፣ ሸማቹ እንዲሸምት ሰላምን በሀቀኛ ውይይት ማፅናት ያስፈልጋል።  ሰከን ብሎ ሆኖ፣ ነገሮችን በጥሞና ተንትኖ፣ በቀና ልብ ሁኔታውን ተገንዝቦ ወደ ውይይት ሜዳ መዝለቅ ሀገር እና ሕዝብን የመውደድ፣ ነፍስን የማዳን ሞራላዊ እና ወገናዊ ሀላፊነት ነው።

ታዋቂው የሕንድ የነፃነት ታጋይ እና የሰላማዊ ፖለቲካ ምልክት የሆነው ማህተመ ጋንዲ “ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ የሚለው መርህ ዓለምን በሙሉ ዓይን አልባ ያደርጋል” እንዳለው በግራ እና በቀኝ መተኳኮሱ ከቀጠለ ሟች ሕዝቡ እና ሀገሪቱ ይሆናሉ። መፍትሄው ይቅርታ፣ ውይይት፣ ንግግር እና ድርድር እንደ ሁኔታው መሆን ይኖርበታል። ግጭትን በግጭት፣ ጦርነትን በጦርነት  አሸንፎ ወደ ተሟላ ሰላም መምጣት ስለማይቻል ወደ ሰላማዊ የንግግር ፖለቲካ መምጣት ነፍስ የማዳን ሰብዓባዊ ተግባር ጭምር ነው።

 

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here