ሀገር በቀል ዕሴቶች እና ሰላምን የማጽናት ኃይላቸዉ

0
137

አሜሪካዊ ፕሮፌሰር ጆን ፖል ሌደራክ ‘ቢውልዲንግ ፒስ’ (Building Peace፡- Sustainable Reconciliation in Divided Societies) በሚለው መጽሐፋቸው ሰላም ከማኅበረሰብ መጀመር እንዳለበት፣ ባሕላዊ ዕሴቶች ደግሞ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ:: የአሜሪካው የሰላም ተቋም (USIP) በድረ ገጹ እንዳስነበበው ደግሞ ሀገራት ከገጠማቸው የእርስ በእርስ ግጭት የወጡት አካባቢያዊ ማኅበረሰባዊ ዕሴትን በመጠቀም ነው::

እንደ ፕሮፌሰር ፖል ገለጻ በምዕራባውያን የተዘጋጁ የሰላም ስምምነቶች በአፍሪካ ወይም በእስያ ዘንድ እምብዛም ውጤታማ አይደሉም:: በምዕራባዊያን ዘንድ የቀረቡት ስምምነቶች ባሕላዊ እና አካባቢያዊ እውነታዎችን የተከተሉ አለመሆናቸውን ደግሞ በምክንያነት አስቀምጠዋል::

በባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች ዙሪያ በተለይም በአፍሪካ እና በእስያ ሀገራት የተደረጉ ጥናቶች ባሕላዊ መንገዶች ከመደበኛው ሕግ ይልቅ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ስኬት ሲያስመዘግቡ ተስተውለዋል::

የፖል ጥናት እንዳመላከተው በታችኛው እርከን ያሉ መሪዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው። ሽማግሌዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን የሞራል የበላይነት በመጠቀም ተዋጊ ወገኖች እውነቱን እንዲናገሩ እና ይቅር እንዲባባሉ የማድረግ ኃይል አላቸው። ባሕላዊ ሽምግልና ትኩረቱም ጥፋተኛን መቅጣት ሳይሆን የተሰበረውን ግንኙነት መጠገን ላይ ነው።

በሀገር በቀል ዕውቀት ችግሮችን በመፍታት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች ታዲያ የበርካታ ሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤት ለሆነችው ሀገራችን መገለጫ ሊሆን አይገባም ነው የተባለው::

በቅርቡ ባሕር ዳር ከተማ ላይ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሽማግሌዎች ምክክር አሁናዊ ግጭቶች ከሽማግሌዎች አቅም በላይ ሊሆኑ እንደማይገባ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፤ ችግሮቹን ለመፍታትም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የሀገር ሽማግሌዎቹ አክለዋል::

ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተካሂዷል፤ የሕግ የበላይነት እና አማራጭ የሙግት መፍቻ አማራጮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀ ነው:: “የሕግ የበላይነት እና አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላምና ልማት” የሚለው ደግሞ የጉባዔው መሪ ሐሳብ ነው::

በክልሉ 15 ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች በጥናት መለየታቸውን ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል:: ሽምግልና፣ አበጋር፣ ረከቦት፣ ዱለት፣ አማሬ ቁና፣ አውሳይድ፣ ጎራው አባ አሊ፣ ስምንቱ ማይ ቤት፣ ዘወልድ፣ መዛርድ፣ ከፍሎ፣ ሰንዬሰገድ፣ አባሀጋ፣ ዙፋን ዋልዋጅ እና ሰባቱ ከዘራ የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች አካል እንዲሆኑ የተደረጉ ናቸው:: ሕጋዊ ማዕቀፍ የተሰጣቸው የችግር መፍቻ ሥርዓቶቹን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል::

በግጭት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሀገር በቀል ዕውቀት (ባሕላዊ የችግር መፍቻ ሥርዓቶች) ከችግራቸው እንዲወጡ አስችሏቸዋል:: የእኛ ሀገር የዘመናት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው::

ፕሮፌሰር ፖል በሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት በሰፊው ጥናት አድርገዋል። በጥናታቸው እንዳመላከቱት በከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎች ደረጃ የተደረጉ ስምምነቶች ሲፈርሱ፣ በየአካባቢው ያሉት የጎሳ መሪዎች በባሕላዊ መንገድ የሚፈጥሩት ሰላም ግን ጸንቶ ይቀጥላል።

በተመሳሳይ በሩዋንዳ የ ’ጋቻቻ’ ዳኝነት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዳይ እና ተበዳይ ፊት ለፊት ተገናኝተው እውነትን መነጋገራቸው የተበዳዮችን የሥነ ልቦና ቁስል በማከም በቀልን የመፈለግ ስሜትን በ60 በመቶ መቀነስ ተችሏል::

ፋምቡል ቶክ (Fambul Tok) የተሰኘው ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት ደግሞ ከዐሥርት ዓመታት በላይ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ የነበረችውን ሴራሊዮንን ዘላቂ ሰላም እንድትገነባ እንዳስቻላት ነው የሚነገረው።

በአጠቃላይ የሀገራቱ ተሞክሮ የሚያሳየው ዘላቂ ሰላም ከላይ በሚጫን ሕግ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከማኅበረሰቡ ባሕል እና ዕሴት በሚመነጭ ይቅርታ እና ዕርቅ ስለመሆኑ የአሜሪካው የሰላም ተቋም አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም የሽምግልና እና የግልግል ዳኝነት አዋጅ (Proclamation No. 1237/2021) ማውጣቷ ይታወሳል:: አዋጁ ባሕላዊ ሽምግልናዎች ሕጋዊ ዋጋ እንዲኖራቸው እና በሽምግልና የተደረሱ ስምምነቶች በፍርድ ቤት እንዲጸድቁ መንገድ የሚከፍትም ነው::  ይህም ኢትዮጵያ የራሷን ዕሴቶች (ሀገር በቀል ዕውቀት) ተጠቅማ ሰላምን ማስጠበቅ የሚያስችላት ሥርዓት ነው፤ ሥርዓቱን ከመደበኛው ሕግ ጋር አጣጥሞ ማስኬድ ዋነኛው ጉዳይ በመሆኑም ነው በአዋጅ ጥበቃ የሚደረግለት::

ከሰሞኑ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስም አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች ለሕግ የበላይነት እና ለዘላቂ ሰላም ስላላቸው የጎላ ድርሻ በስፋት አንስቷል::

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እና የንብረት መብትን በማስከበር፣ ለኢንቨስትመንት እና የፈጠራ መብቶች ጥበቃ በማድረግ፣  የስልጣን ክፍፍል እና የእርስ በእርስ ቁጥጥር እንዲኖር በማስቻል ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል:: ለአለመግባባቶች ፍትሐዊ እልባት በመስጠትም  ለሕግ የበላይነት መከበርና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከ14 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና ከ200 በላይ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ጋር በመሆን በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን መዝገቦችን ያስተናግዳል:: ከመደበኛው ሕግ በተጨማሪ ደግሞ አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ፤ ይህም በፍርድ ቤቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ እና በሁሉም አካባቢዎች ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ::

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን እና ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ጋር በማጠናከር  የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል:: የሕግ የበላይነት እና ሀገር በቀል መሠረተ – ማሕበረሰብ የሆኑ አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች ዘላቂ ሰላምን፣ ማሕበራዊ መስተጋብርን እና ምጣኔ ሀብታዊ  ዕድገትን ለማረጋገጥ ከፍ ያለ አበርክቶ እንዳላቸውም አስገንዝበዋል::

እንደ ሀገር የፖሊሲ ለውጥ ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን ማጎልበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እንድሪስ ናቸው:: እንደ ሀገር 75 የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች መለየታቸውንም አስታውቀዋል፤ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ውስጥ ያሉ ያለመግባባት መፍቻ መንገዶችን የሕግ ማዕቀፍ ኖሯቸው ዕውቅና መስጠቱን እና ተቋማዊ እንዲሆኑ ማድረጉን አድንቀዋል::

በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ የሰላም እና ደህንት አርክቴክቸር አምባሳደር ሳላህ ሀማድ የአፍሪካ ሕብረት አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን ሀገራት እንዲጠቀሙ እንደሚያበረታታ ተናግረዋል:: አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች በመላው አፍሪካ በስፋት ተግባራዊ የሚደረጉ እና አለመግባባቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት ያስቻሉ መሆናቸውንም ነው የገለጹት:: እነዚህ ሀገር በቀል ሥርዓቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የሕገ መንግሥት መሠረት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓት ባለቤት መሆኗን የተናገሩት አምባሳደሩ፣ “ሰላም እና ደኅንነቷን በዐይነ ቁራኛ ጠብቁላት” ሲሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት:: እነዚህ የሰላም አማራጭ መንገዶች የፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና በእጅጉ በማቃለል፣ ወጪን በመቆጠብ፣ በማሕበረሰቡም ውስጥ መተማመንን እና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር አካታች  ልማትን ለማስፈን ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል::

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ሕዝብ በሺህ ዘመናት ታሪኩ ካካበታቸው ዕሴቶች አንዱ የፍርድ ሥርዓት መሆኑን ተናግረዋል:: ሕዝቡ  ለበርካታ ዘመናት ሽምግልናን ጨምሮ የተለያዩ የዕርቅ እና የግልግል ዘይቤዎችን ሲጠቀም መኖሩንም አንስተል:: የባሕል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ ሕግ መውጣቱ ለባሕላዊ ዕሴቶች ሕጋዊ እና ተቋማዊ ቁመና የሚያጎናጽፍ ጅማሮ መሆኑንም ገልጸዋል::

አቶ ተመስገን እንዳሉት አማራጭ የክርክር መፍቻ ሥርዓትን ማጠናከር እና ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን በተደራጀ መንገድ መመሥረት  ውይይትን፣ መግባባትን እና ስምምነትን ከቅራኔዎች ለማስቀደም ይረዳሉ:: በድኅረ ግጭት ዐውድ ዕርቅ ለማስፈን፣ የተሰበሩ ግንኙነቶችንም መልሶ ለማደስም ከፍተኛ ፋይዳ ኖራቸዋል::

ባሕላዊ የፍትሕ ተቋሞቻችን ማኅበረሰብ አቀፍ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን እንዲፈቱ ማድረግ  ለዘመናት ለቆየው የሽምግልና ሥርዓት አዲስ እና ጠንካራ ተቋማዊ ዕውቅና ይሰጣል ነው ያሉት:: ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን ከዘመናዊ ዕሳቤዎች ጋር በማስተሳሰር፣ በሕግ በመደገፍ እና አሠራሮቻቸውን በማዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚተገበሩ ማሻሻዎች ጋር አሰናስሎ ማዋቀር ደግሞ ዋናው የቤት ሥራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here