ሀገር አቋራጫችን እንዳይቋረጥ

0
164

የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር በየሁለት ዓመቱ ከሚያዘጋጃቸው የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች መካከል የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር አንዱ ነው። ውድድሩ በ1973 እ.አ.አ የተጀመረ ሲሆን እስከ 2011 እ.አ.አ ድረስ በየዓመቱ ይደረግ እንደ ነበር ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ድረ ገጽ ያገኝነው መረጃ ያስነብባል። እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ ግን በየሁለት ዓመቱ እየተከናወነ ይገኛል::

በአትሌቲክስ ስፖርት እንደ አገር አቋራጭ ውድድር ፈታኝ እና አስቸጋሪ ውድድር እንደሌለ የዘርፉ ባለሙያዎች  ይናገራሉ። የአትሌቶቹን አቅም እና ጉልበት ይፈትናል፣ ከፍ ካለ ደግሞ ለጉዳት ያጋልጣቸዋል። ምንም እንኳ ውድድሩ ፈታኝ ቢሆንም አዳዲስ ፊቶች የሚታዩበት፣ የመጪው ዘመን የዘርፉ አብሪ ኮከቦች የሚወጡበት ግዙፍ የአትሌቲክስ መድረክ ነው።

በርካታ የኦሎምፒክ  ስመ ጥር አትሌቶች ውድድራቸውን የጀመሩትም በዚህ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ነው። ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ ፣ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና ጥሩነሽ ዲባባን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

አገራችን በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር መሳተፍ የጀመረችው እ.አ.አ በ1981 በስፔን ማድሪድ ከተማ በተካሄደው በዘጠነኛው የመድረኩ ምዕራፍ ነው። በወቅቱ ስምንት አትሌቶችን ማሳተፏን ታሪክ ያወሳል። በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ሙሀመድ ከድር በመድረኩ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አምጥቷል። እንዲሁም በቡድን አዋቂ ወንዶች ኢትዮጵያውያን የብር ሜዳሊያ ማምጣታቸውን ታሪክ ይነግረናል። በአንድ ወርቅ እና በአንድ ብር በሜዳሊያ የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ሆናም ማጠናቀቋ በታሪክ ተመዝግቧል።

በስፔን ማድሪድ ከተማ የተጀመረው የኢትዮጵያውያን ገድል በትውልድ ቅብብሎሽ አሁንም እየተገለጠ ይገኛል። በየሁለት ዓመቱ በሚደረገው በዚህ አስቸጋሪው የዓለም አገር አቋራጭ  ውድድር በርካታ ሀገሮች በየጊዜው የሚሳተፉ ቢሆንም ውድድሩ ግን የኢትዮጵያውያን እና የኬኒያውያን አለፍ ካለም የዩጋንዳውያን ፉክክር ብቻ ነው የሚመስለው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንኳ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ እና ኬኒያ እየተፈራረቁ ውድድሩን በበላይነት መጨረሳቸው አይዘነጋም። የ2024ቱ የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በሰርቢያ ቤልግሬድ በወዳጅነት ፓርክ (park of friendship) መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል።

በዋናነት ውድድሩ ሊደረግ ታስቦ የነበረው በመስከረም 15 ቀን 2023 እ.አ.አ በክሮሺያ ፑላ ከተማ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ነገር ግን አስተናጋጇ አገር ክሮሺያ ለውድድሩ አስፈላጊውን መሰረተ ልማቶች ባለማሟላቷ ውድድሩ እንዲገፋ እና አስተናጋጅ አገርም እንዲቀየር ተደርጓል። ከአንድ ዓመት በላይ ተገፍቶ በተደረገው ውድድር ከ51 ሀገራት የተውጣጡ 485 አትሌቶች በአምስት የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፈዋል።

በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች እና ወንዶች፣ በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ በስድስት ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች እና በ4X2 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ቅብብል በሁለቱም ፆታዎች ፉክክሩ የተደረገባቸው ናቸው። አገራችንም በ14 ሴቶች እና በ14 ወንዶች በአጠቃላይ በ28 አትሌቶች ተወክላ እንደነበር የሚታወስ ነው::

የአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቁ ፍሬዎችም ሁለት ወርቅ ፣ስድስት ብር እና ሁለት ነሐስ በድምሩ አስር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በአክራ ሰማይ ስር የተደገመው የአረንጓዴው ጎርፍ ገድል በቀናት ልዩነት በአውሮፓ ምድር ሰርቢያ ቤልግሬድም በወጣት ሴቶቹ ተደግሟል።

ከ20 ዓመት በታች የስድስት ኪሎ ሜትር ሴቶች ውድድርን ማርታ አለማየሁ፣ አሳየች አይቸው፣ እና ሮቤ ዲዳ ተከታትለው በመግባት ሁሉንም ሜዳሊያ ጠራርገው ወስደዋል። የኔዋ ንብረት ስድስተኛ፣ ለምለም ንብረት ስምንተኛ እና ሽቶ ጉሜ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘው የጨረሱ ሌሎች አትሌቶች ናቸው።

ሌላኛው ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችበት ውድድር ደግሞ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች፣ በቡድን በተደረገ የ4X2 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ቅብብል ነው። ማርታ አለማየሁ፣አሳየች አይቸው፣ ሮቤ ዲዳ፣ የኔዋ ንብረት እና ለምለምን ንብረት በፉክክሩ በመሳተፍ በአስደናቂ ጥምረት እና መናበብ ሁለተኛውን ወርቅ ለአገራቸው አስገኝተዋል። ኬኒያ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ዩጋንዳ ደግሞ ሦስተኛ ሆና ጨርሳለች።

በተመሳሳይ በወንዶች ከ20 ዓመት በታች በድብልቅ ቅብብል ስምንት ኪሎ ሜትር ተሬሳ ቶሎሳ፣ ዳዲ ዱቤ፣ አድሀነ ካህሳይ እና ብሪ አበራ በጋራ ሮጠው የብር ሜዳሊያ አስመዝግበዋል። ይህን ውድድር ኬኒያ በበላይነት ስታጠናቅቅ ታላቋ ብሪታኒያ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች ።

በወንዶች ከ20 ዓመት በታች ስምንት ኪሎ ሜትር በተደረገ ፉክክር መዝገቡ ስሜ የብር ሜዳሊያ እና በአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ደግሞ በሪሁ አረጋዊ በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያ ለሀገሩ አሳክቷል። በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል አልቀናቸውም። ብርቱካን ወልዴ ስምንተኛ፣ መብራት ግደይ አስረኛ ፣ ሲሳይ መሰረት 12ኛ ፣ግርማዊት ገብረእግዚያብሄር 21ኛ እና በቀለች ተኩ 25ኛ ደረጃን ይዘው ነው የጨረሱት። በዚህ ርቀት ኬኒያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።

አገራችን በ2021 እ.አ.አ በአውስትራሊያ ባትረስት ከተካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አልቻለችም። በወቅቱ ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ ፣ ሰባት ብር እና አንድ ነሐስ በድምሩ አስር ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ ከኬኒያ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ አይዘነጋም።

ከዛ በፊት በነበረው በ2019ኙ የዴንማርኩ አገር አቋራጭ ግን አገራችን ኬኒያን እና ዩጋንዳን በመብለጥ በአምስት ወርቅ፣ ሦስት ብር እና ሦስት ነሐስ በአጠቃላይ በ11 ሜዳሊያ በበላይነት ማጠናቀቋ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር መሳተፍ ከጀመረችበት እ.አ.አ ከ1981 ጀምሮ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው እ.አ.አ በ2004 በቤልጂየም ብራስልስ በተደረገው ውድድር ነው። በ30ኛው የመድረኩ ምዕራፍ አገራችን ዘጠኝ ወርቅ፣ ስድስት ብር እና አምስት ነሐስ በድምሩ 20 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። በደረጃ ሰንጠረዡም በበላይነት ማጠናቀቋን መረጃዎች አመልክተዋል።

በአንጻሩ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ታሪክ አንድም ሜዳሊያ ሳታስመዘግብ የተመለሰችበት ጊዜ እንደ ነበር ታሪክ ያስረዳል። በ2010 እ.አ.አ በፖላንድ በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባዶ እጃቸውን መመለሳቸው ይታወሳል። በወቅቱም በአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ብዙ ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወቃል።

በዚህ መድረክ የቀነኒሳ በቀለን ያህል የተሳካለት አትሌት የለም።ኢትዮጵያዊው ጀግና በመድረኩ 16 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ባለታሪክ ነው። ከእነዚህ ወርቆች ውስጥ 12ቱ በግል እንዲሁም አራቱ በቡድን ሥራ የተገኘ ድል ነው።

ቀነኒሳ እ.አ.አ ከ2002 እስከ 2006 ባሉት ጊዜያት በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በተከታታይ ለአገሩ የወርቅ ሜዳሊያ አምጥቷል። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም አምስት ወርቅ እና ሦስት የብር ሜዳሊያ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በማስመዝገብ ከሴቶች ቀዳሚ አትሌት ናት።

በዘንድሮው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር አራት አገራት ብቻ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል። ኬኒያ ፣ ኢትዮጵያ ፣ዩጋንዳ እና ታላቋ ብሪታኒያ ሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ የገቡ ሀገራት ናቸው። ባሳለፍነው የካቲት ወር አጋማሽ በተካሄደው በስድስተኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር በሴቶች ከ20 ዓመት በታች ስድስት ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው አይዘነጋም። በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዝያ በተደረገው የአትሌቲክስ መድረክ የአረንጓዴው ጎርፍ ገድል መደገሙ አይዘነጋም።

በሁለቱም የአትሌቲክስ መድረኮች ማለትም በአፍሪካ እና በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ልምድ ካላቸው አዋቂዎች በተሻለ ወጣቶች ጥሩ  ውጤት ማስመዝገባቸውን ተመልክተናል። ታዲያ በትውልድ ቅብብሎሽ ከዚህ የደረሰው ስመጥሩ አትሌቲክስ ስፖርት እንዳይመክን እና እንዳይደበዝዝ ለወጣቶቹ ተገቢውን ዕድል በመስጠት እና በመተካካት ሰንደቅ ዓላማችንን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ያስፈልጋል።

በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ እስካሁን በድምሩ 295 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከኬኒያ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 109 ወርቅ፣ 120 ብር እና 66 የነሐስ ሜዳሊያዎች አሏት። ኬኒያ በ345 ሜዳሊያ የደረጃ ሰንጠረዡን ስትመራ ዘንድሮ አንድም ሜዳሊያ ያላገኝችው አሜሪካ በ65 ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ከዚህ በፊት በአፍሪካ ምድር ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል። ሞሮኮ ፣ኬኒያ እና ዩጋንዳ ከዚህ በፊት ውድድሩን ያስተናገዱ ሀገራት ናቸው። በቀጣይ የ2025ቱ የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በጃፓን ቶኪዮ የሚደረግ ይሆናል።

የመረጃ ምንጫን ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ድረ ገጽ ነው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here