“ህፃናት ከሚሰሙት በላይ የሚያዩትን ያምናሉ”

0
114

የአዕምሮ ጤንነት ልጆች ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን የሚመለከቱበት መንገድ ነው:: ወላጆች የልጆቻቸውን ሁኔታ እንዲከታተሉ በየዕድሜያቸው ያለውን የባህርይ ለውጥ ማወቅ አለባቸው:: ይህ ሲባል ልጆች  እንዴት እንደሚያስቡ እና ነገሮችን እንደሚረዱ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት እንደየ ዕድሜያቸው፣ አቅማቸው እና ደረጃቸው በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘትን እንዴት እንደሚማሩ፣  ምን እንደሚሰማቸው፣ እንዴት መረዳት እንደሚገባቸው፣ ለመገንዘብ የዕድሜ ደረጃቸውን አስተሳሰብ ቀድሞ መገንዘብ ለወላጆች ጠቃሚ ጉዳይ ነው::

 

በሰብዕና ግንባታ እና ከሥራ ፈጠራ ጋር በተገናኘ ለግለሰቦች እና ለተቋማት  ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የሥነ ልቦና ድጋፍ በመሥጠት (አሁንም እየሰጡ) እና  በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙትን  እሱባለው ነጋን   በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ አነጋግረናቸዋል::

ባለሙያው እንደሚሉት  በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ያለው የባህርይ ለውጥ ሲከፋፈል ዋናው መሠራት ያለበት ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዓመት ያለው የዕድሜ ክልል ላይ ነው:: ማንኛውም ሕፃን ታዲያ ያደገበት ቤተሰብ እና ማሕበረሰብ፣ የሚከተለው ሃይማኖት  እና ሳይንስ ድምር ውጤት ይሆናል::

እንደ አቶ እሱባለው ገለጻ የልጆች የመጀመሪያ የሕፃንነት ዕድሜ ከአንድ ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያለው ነው:: ይህ የዕድሜ ክፍል የሰው ልጅ ተሠርቶ ያላለቀው የአዕምሮ ክፍል ንፁህ /በተለምዶ ያልተጻፈበት ወረቀት እየተባለ የሚጠራው/ እንደሆነ ማሳያ ነው::

ሕፃናት በዚህ ዕድሜ እንደፈለጉ የሚሆኑበት፣ ምንም ነገር የማይከለከሉ እንደሆነ የሚሰማቸው፣ የሚያደርጉት ነገር ትክክል እንደሆነ የሚያስቡበት፣ የፈለጉትን ማድረግን የሚወዱበት፣ ነፃነትን የተላበሱበት፣ ምንም ውጫዊ ነገር እንደማይበግራቸው የሚያውቁበት የዕድሜ ክፍል ነው:: ይህ የዕድሜ ክፍል በተለይ እስከ ሰባት ዓመት ያለው ድብቁ የአዕምሮ ክፍል የሚሠራበት እና የሚዋቀርበት (ፕሮግራም የሚደረግበት)፣ መጭው ሕይወታቸው የሚወሰንበት ጊዜ ነው::

 

ልጆች  ጥሩም ይሁን መጥፎ  በየጊዜው ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰብ  በሚያዩት እና በሚፈፀሙት ድርጊቶች አዕምሯቸውን የሚሞሉበት የዕድሜ ክልል ከአንድ ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያለው  ጊዜ ነው:: በዚህ ጊዜ ደጋግመው የሚሰሙትን ነገር እውነት አድርገው በሕይወታቸው ሙሉ ይቀበላሉ::

አቶ እሱባለው “ወላጆች ለልጆቻቸው ‘ደጋግመን የምንነግረው ነገር ምንድን ነው?’ ብለው መጠየቅ እንዲሁም በጣም ትኩረት አድርጎ መሥራት ለውጥ እንዳለው መገንዘብ አለባቸው” በማለት ከቤተሰቦቹ ባገኘው የይቻላል መንፈስ ውጤታማ የሆነውን  የቶማስ ኤዲሰንን ታሪክ ጠቅሰው አስረድተዋል፤ “ቶማስ ኤዲሰን ከትምህርት ቤት ሲባረር የአምስት  ወይም የስድስት ዓመት  ዕድሜ ልጅ ነበር፤ ‘ልጅሽ ደደብ ነው’ ብለው ከትምህርት ቤት ቢያባርሩትም እናቱ ግን ‘እሱ የዓለም ብርሐን፤ ተስፋው የለመለመ እንደሆነ ደጋግማ ለህሊናው መገበችው፤ ነገረችው::

 

ገና በሕጻንነቱ ከፍ ያለ ነገርን የማሰብ፣ ያለመታከትን በልጅነቱ ከእናቱ  ተማረ:: ከእናቱ የጥንካሬ መንፈስን እንደተገነዘበው ቶማስ  ሌሎች ወላጆችም  ለልጆቻው መቻልን፣ በጎነትን፣ ደግነትን (መራራትን)፣ ማሸነፍን  የምንነግርበት ዕድሜ ክልል ይህ የመጀመሪያው ዕድሜ መሆኑን መገንዘብ ይገባቸዋል” በማለት ነው ያብራሩት::

ባለሙያው እንዳስገነዘቡት የሀገር ታሪኮችን፣ እንደየዕምታችን ደግሞ መልካም የሠሩ ባለታሪኮችን ታሪክ ማስረፅ ይገባል:: ማንኛውንም ነገር ማድረግ የሚችል ትልቅ አዕምሮ አምላክ እንደቸራቸው፣ ሰውነታቸው ውስን ቢሆንም አዕምሯቸው እንደማይገደብ (እንደማይወሰን)፣ ቤተሰብን፣  ሀገርን እንዲሁም ዓለምን መቀየር እንደሚችሉ መንገር ይገባል፤ ምክንያቱም ይህ የዕድሜ ክልል አቅም የሚገነቡበት ነውና::

በዚህ የዕድሜ ክልል  ቤተሰብ እንደ ችግኝ ልጆቹን ሳይሰለች ደጋግሞው የሚኮተኩቱበት ነው፤ የልጅ ማንነት ሳይሠራ ደግሞ ሃብት እንኳን ቢያወርሰው አይጠቅምም::

 

ስለዚህም ነው ወላጅ ልጁ እንዲሆን የሚፈለገውን ማንነት፣ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ሃይማኖተኛነት እንዲሁም ዓለምን ለማሸነፍ መለኮታዊ ኀይል ያለው አቅም እንዳለው በማሳወቅ ውስጡን ከገነባ ሲያድግ በራሱ አቅም ምንም ነገር ማግኘት እና ማድረግ ያለበት::

ቤት ሲሠራ ትልቁን ነገር የምናውለው ከመሠረቱ ነው፤ ወላጅም ከአንድ ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የማንነቱን መሠረት በአግባቡ፣ በትዕግስት እና በከፍተኛ ጥረት ማነጽ ከቻለ ልጆች በውስጣቸው ጠንካራ ማንነት ይሰርፃል::

ለሕፃን (ለልጆች) ‘ታሪክ እንንገር፣ መንገርም አለብን’  ስንል የምንነግራቸውን ታሪክ በህሊናቸው (በምናብ) ይስላሉ:: ዝም ተብሎ ምክር ብንመክራቸው ግን ከዕድሜ አንፃር ነገሩን አይረዱም:: ከሚሰሙት በላይ ደግሞ የሚያዩትን ነገር ያምናሉ:: እናም ወላጅ የተግባር ሰው መሆን ይገባዋል:: ለምሳሌ አባት ሲጋራ መጥፎ ነው እያለ እየነገረ ሲያጨስ ልጁ ከተመለከተ የአባቱን መጥፎ ነው የሚለውን ምክር በጭራሽ አይቀበልም::

ልጆች በዚህ ዕድሜ መቀጣት ካለባቸው መቅጣት ይገባል፤ ቅጣት ሲባል ግን አካልን በሚያጎድል መልኩ አብዝቶ  መቀጥቀጥ ከሆነ ለአዕምሮ ጠባሳ ስለሚሆን  የሚማሩት ነገር አይኖርም::

 

ጥፋት ላይ ቀድሞ ልክ አለመሆናቸውን ደጋግሞ ሊረዱ በሚችሉበት መንገድ ቃል መርጠን ማስገንዘብ፣ ቀጥሎ አሻንጉሊት  በመቆንጠጥ እነሱ ሲያጠፉ ተመሳሳይ የአካል ቅጣት  ቁንጥጫ ሊቆነጠጡ እንደሚችሉ   በመጠኑ ቆንጥጦ ቀጥቶ ማሳደግ ይገባል::

ከተቀጡ በኋላም ማራቅ አይገባም የሚሉት አቶ እሱባለው፤ የተቀጣበትን ነገር ደጋግሞ መንገር እና ማስረዳት ይገባል ነው ያሉት::

ልጆች ሲነገሩ ቶሎ እሺ ካሉ ነገሩ በሚገባ አልገባቸውም ማለት ነው፤ ደጋግመው ከጠየቁ ግን ነገሩ እንዲገባቸው እየታገሉ ስለሆነ ወላጅ ደጋግሞ ሳይሰለች ማስረዳት አለበት፤ ይህን ማድረግ  ከተቻለ ሲያድጉ ጠያቂ፣ ሞጋች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል::

 

በልጆች አስተዳደግ ከአንድ ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያለው ጊዜ   ከአውሮፓውያን በደንብ ልንወስደው የሚገባው ትልቁ ልምድ  ደግሞ  በቂ ጊዜ በመስጠት ማንነትን እና መክሊታቸውን እንዲሁም ድርጊታቸውን በማየት ፍላጎታቸውን እንዲረዱ የሚያደርጉትን ጥረት ነው::

እንደ አቶ እሱባለው ማብራሪያ ልጆች የማያስፈልጋቸውን ነገር  መከልከልን መልመድ የሚገባቸው በዚህ የዕድሜ ክልል ነው፤ ሰዎች አብዝተው የተከለከሉትን ስለሚፈልጉ  በደፈናው መከልከል /መዝጋት/ ሳይሆን በዝርዝር ለምን እንደማያስፈልጋቸው ካስረዳን በኋላ ነው መከልከል የሚገባው::

በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ የማይገባቸውን ካልከለከልን ሲያድጉ አፈንጋጭ፣ ሙሰኛ እና በቀለኛ ሆነው ሊያድጉ ይችላሉ፤ በመሆኑም በዕድሜያቸው በጥንቃቄ ማንነትን መሥራት ያስፈልጋል::

ለነገ ሀገር የሚረከቡ እና ሀገር የሚሆኑ ልጆች በትክክል የሚሠሩበት ዕድሜ ነው፤ ይህ የምንፈልገው ጥሩ ማንነት የሚሠራው ደግሞ በቤት ውስጥ በዚህ ዕድሜ ክልል መሆኑን ቤተሰብ መገንዘብ እንደሚገባው አቶ እሱባለው አስገንዝበዋል::

በቀጣይ ሳምንት ጽሑፋችን ደግሞ ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ መደረግ ስለሚገባቸው ተግባራት ከአቶ እሱባለው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እናቀርብላችኋላን::

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here