በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 15 የመንግሥት እና ሁለት የግል ትምህርት ቤቶች ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተማሪዎች በተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር እየተሳተፉ መሆናቸውን የከተማው ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) ከሰሞኑ የሁለተኛውን ዙር የተማሪዎች የምገባ ሥነ ሥርዓት በመስከረም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው አስጀምረዋል፤ በወቅቱ እንደተናገሩት በከተማዋ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ በ17 የትምህርት ተቋማት ዘጠኝ ሺህ 221 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ ነው፡፡
ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳር ኮሙኒኬሽን መምሪያ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው መርሐ ግብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲተባበር ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም በምግብ ዕጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡና በንቃት ለመከታተል የሚቸገሩ ተማሪዎችን የሚታደግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም