ሁለተኛው ጥበብ

0
141

ከሰባቱ ዐበይት የጥበባት ዘርፎች ሁለተኛው ነው:: ስዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ኪነ ሕንጻ፣ ስነ ጽሑፍ፣ ሲኒማ፣ ቴያትር እና ሙዚቃ ተብለው ይከፈላሉ፤ ጥበባቱ:: ይህ ጥበብ ቅርጻ ቅርጽ ይባላል:: ሐውልት ደግሞ የዚህ ጥበብ አንዱ ዘርፍ ነው::

ሮክ ኤንድ ቱልስ ድረ ገጽ የቅርጻ ቅርጽ ስራ በድንጋይ ዘመን ሳይጀመር እንዳልቀረ ይገምታል:: ዘቬነስ ኦፍ ቬርካት በ230 ሺህ ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ፤ ዘ ቬነስ ኦፍ ታን ታን 200 ሺህ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተሰሩ የቅርጻ ቅርጽ ስራዎችን መገኘት ዋቢ አድርጎ ያስቀምጣል::

በሰነድ ተጽፈው የተገኙት እና የዚህ ጥበብ መነሻ ሆነው የሚቆጠሩት በጀርመን ዋሻዎች ውስጥ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ35 ሺህ ዓመታት በፊት የተገኙት የእንስሳት እና ወፍ ቅርጾች ነበሩ::

የግብጽ ፒራሚዶች ኒዮሎቲክ በሚባለው የታሪክ ዘመን የተሰሩ የጥበብ ስራዎች ናቸው:: በግብጽ የመሪዎችን እና የአማልክትን ሐሳቦች እና ምስሎች በሐውልት ማስቀመጥ በስፋት እውቅና ያገኘ ነው:: በግሪክ እና ሜሶፖታሚያ ስልጣኔዎችም ሐውልቶችን መስራት በስፋት የሚጠቀስ ታሪክ ያለው ነው::

ውክልና እና ምልክት መስጠት ሐውልቶች ወይም ቅርጻ ቅርጾች የሚሰሩበት አንዱ ምክንያት ነው:: የሰዎችን የዘመናት አመለካከት፣ ግንዛቤ፣ እምነት ፣ሐሳብ እና ማንነት  ለማሳየት ጥቅም ላይ ይውላሉ:: በጥንት ዋሻዎች ውስጥ በድንጋይ የተቀረጹ ሐውልቶችን በማየት የዛሬ ትውልድ ምን ዓይነት ሰዎች እንደነበሩ ማወቅ ይችላል:: አኗኗራቸው፣ ስራቸው፣ አመለካከታቸውን ለመረዳት እድል ያገኛል::

ሐውልቶች መሪዎችን፣ ግለሰቦችን፣ እንስሳትን ወይም የጎሳ አባላትን በምልክት ለማሳየት እና ለማክበር  ሲሰሩ ኖረዋል:: ንጉሡን እና ንግሥቲቱን እንዲሁም የንጉሣውያን ቤተሰቦችን በሐውልት ማስቀመጥ አንድም የማክበር እና ምልክት ማድረግ ለዘመናት የቀጠለ ልማድ ነው::

በጥንታዊ ግብጽ ፈርኦኖች ጠንካራዎች እና መንግሥታቸው ለማንም የማይሸነፍ መሆኑን ለማሳየት በአደባባዮች እና ሰው በብዛት በሚሰባሰብባቸው ስፍራዎች ሐውልት ሰርተው ያስቀምጡ ነበር::

ይህ ታሪክ አድጎ ዛሬ በመላው ዓለም መልካም ስራ እና ስኬታማ ተግባር ለፈጸሙ ሰዎችም ጭምር ሐውልቶች እየቆሙላቸው ነው:: የእግር ኳሱ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሕይወት እያለ ሐውልት ቆሞለታል:: በሀገራችንም አጼ ቴዎድሮስ፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ እና ሌሎችም መሪዎች ለሰሩት መልካም ተግባር በአደባባዮች ሐውልት ቆሞላቸዋል::

አርበኛው አባት አቡነ ጴጥሮስ ለፈጸሙት የሕይወት መስዋዕትነት ሐውልት ቆሞላቸዋል:: በላይ ዘለቀ ለተጋድሎው ሐውልት ቆሞለታል:: በየዘመናቱ ትውልድ የበላይን ማንነት እና ታሪክ በጥበብ ስራዎቹ እያስታወሰው ይበልጥ ገናና እያደረገው ተጉዟል:: የአይደፈሬነት፣ እምቢተኝነት፣ የሀገር ፍቅር እና ጀግንነት ትርክቶች ሕዝቡን ከትናንት ዛሬ ያስተሳስሩታል:: በላይም ይሁን ዳግማዊ ንጉሥ ቴዎድሮስ በሐውልቶቻቸው  ሲታወሱ ከሕዝብ ልብ ውስጥ የሚያኖራቸው ሕያው  ስራቸው ነው::

ሐውልቶች ለዘመናት ሃይማኖትን ወክለው ቀርበዋል:: በተለይ በቀደመው ዘመን እንደ ዛሬ    ማንበብ እና መጻፍ ባልነበረበት ዘመን የሃይማኖት መሪዎች የቅርጻ ቅርጽ ጥበብን ተጠቅመው መልእክትን ያስተላልፉ ነበር:: ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የአጋንንት እና የሰይጣን ሐውልቶች እንዲሁም ምልክቶች ይቀመጡ ነበር:: በዚህም ሕዝቡ ክፉ እና መጥፎውን ለይቶ  ማወቅ ይችል ነበር፡፡

በጥንታዊት ግሪክ ኦሎምፒያ ከተማ የዜኡስ አምላክ ሐውልት ተቀርጾ ነበር፡፡ ይህም ሐውልት የከተማዋ ሕዝብ ሁልጊዜ አምላክ መኖሩን እንዲያምኑ እናም እንዲያስታውሱ ለማድረግ ነበር፡፡ ከ12 ሜትር በላይ ቁመት ነበረው፡፡ ፊዲያስ በተባለው ቀራጺ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ435 ዘመን ነበር የተሰራው፡፡ 12 ዓመታት ይህን ሐውልት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ ነበር፡፡ ዜኡስ አማልእክት ንጉሥ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ለዚህ ክብሩም ሲባል ሐውልቱ ተሰርቶለታል፡፡

ሐውልቶች ሐሳቦችን  የማስተላለፊያ ጥበባዊ መንገዶችም ጭምር ናቸው፡፡ የከያኒያንን ፈጠራ እና አሻራ ማሳረፊያ ሆነውም ያገለግላሉ፡፡ በእንጨት፣ በወርቅ፣ በነሀስ፣ በመዳብ፣ በብረት፣ በእብነ ብረድ እና በሌሎች እቃዎች ሐውልቶችን መስራት የተለመደ ነበር፡፡

ሐውልቶች በዘመናዊው ዓለም ስነ ውበታዊ ዋጋም አላቸው:: የጌጥነት ጥቅማቸው በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል:: ጥበብነታቸው የሚጎላውም በዚህ ምክንያት ነው::

ሲቪታቲስ ድረ ገጽ በዓለም ግዙፍ ሐውልቶችን በስም ዘርዝሮ አስቀምጧል:: በሕንድ የሚገኘው 82 ሜትር ርዝማኔ ያለው የህንድ ሰው ሳራዳር ቫላባቤህ ፓቴል ሐውልት  በረጅምነቱ ይጠቀሳል፤ የአንድነት ሐውልት ተብሎም ይጠራል:: ይህ ሐውልት የተሰራው እ.አ.አ በ2018 ነበር::   በሰው ሰራሽ ሐይቅ ዳርቻ ለጎብኝዎች ምቹ ሆኖ 7 ኪሎ ሜትር መጠነ ዙሪያ ያለው ነው::

ሳራዳር የሕንድ የነጻነት መሪ ነበር:: ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሀገሩን አገልግሏል:: ሕንዶች ጥቅምት 31 ቀን በየዓመቱ የሳራዳርን ልደት ምክንያት በማድረግ የአንድነት ቀናቸውን ያከብራሉ:: የሕንድ መስራች አባት ነው ብለው ያከብሩታል:: ሕንድ ከቅኝ ግዛት እንድትወጣ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረገ ሰው ነው:: የሕንድን ሕዝብ ለነጻነቱ አታግሎ አንድነት ያለው እና ነጻ ሕዝብ እንዲሆን በማድረጉ ሁልጊዜም በታሪክ ውስጥ ይወሳል:: ሐውልቱም የቆመለት ይህንን ውለታውን ለማስታወስ ነው:: የሕንድ የአንድነት ቀን በዚህ ሰው የልደት ቀን  ይከበራል::

የአሜሪካ ነጻነት ሐውልት በየዓመቱ 4 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎች የሚጎበኙት ድንቅ የሐውልት ስራ ነው:: የአሜሪካ ሕዝብ ለነጻነት እና ዴሞክራሲ ያደረጉትን ጽናት እና ትግል ለመደገፍ ከፈረንሳይ ሕዝብ የተበረከተ የአንዲት ሴት ሐውልት ነው:: ይህች ሴት በሐይቅ ዳርቻ መብራት ይዛ ለዓለም ብርሃን እያበራች ትታያለች:: የፈረንሳይ ሕዝብን የወከሉ ሰዎች አንድ ቀን ለአሜሪካዊያን ምን ስጦታ እናበርክትላቸው ብለው ያስባሉ:: ኦግስቲ ባርቶልዲ የተባለው ቀራጺ ይህችን የነጻነት ሐውልት በመቅረጽ ስሙ ይጠራል:: በፈረንጆች አቆጣጠር በ1886 ተሰራች:: 225 ቶን ክብደት፣ 11 ሜትር ርዝመት አላት::  በየዓመቱ ብዙ ጎብኝዎች ይመለከቷታል:: ነጻነት የዓለም ብርሃን (ላይበርቲ ኢንላይትኒንግ ዘወርልድ) የሚለው የመጀመሪያ ስሟ ነበር:: በሒደት የላይበርቲ ሐውልት ተብላ ስሟ ወደ ነጻነት ተለወጠ::

የተሐድሶ ዘመን ድንቅ የጥበብ ስራ ሆነው ከሚጠቀሱት ሐውልቶች መካከል ሚካኤል አንጀሎ ቅዱስ ዳዊትን የቀረጸበት ስራ ነው:: በፈረንጆች አቆጣጠር ከ1501 እስከ 1505 ባሉት ዓመታት ነበር የተሰራው:: በዚህ ዘመን ይሰሩ የነበሩ ስራዎች የሰው ልጆችን አካላዊ ውበት ማጉላት ላይ ትልቅ ትኩረት ያደርጉ ነበር:: ሚካኤል አንጀሎ አንድ ነጠላ እብነ በረድን በመጥረብ ነበር ይህን ሐውልት የሰራው:: የሰው ልጆችን ጸጉር፣ የቆዳ ልስላሴ በሚገባ ለማሳየት ያደረገው ጥረት የዳዊትን ሐውልት ከሰው ልጆች ጋር ተቀራራቢ መልክ እንድናስተውልበት አድርጓል:: በአካል ትንሹ ዳዊት ከግዙፉ ጎሊያድ ጋር ገጥሞ ማሸነፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ቀርቧል::

ይህ የዳዊት ሐውልት ጽናት እና ጀግንነትን ለዓመታት ለማሳየት ጠቅሟል:: ብዙ አሳቢያን የበለጠ ብዙ እንዲያስቡ፣ እንዲመራመሩና ስራዎቻቸውን የሰው ልጆች በዓለም ውስጥ ያላቸውን ስፍራ እንዲያውቁ አስችሏቸዋል:: ጎሊያድን በጠጠር የጣለው ወጣቱ ዳዊት እርቃኑን ወንጭፉን ይዞ ይታያል:: በመጽሐፍ ቅዱስ ጀግና ሆኖ የተሳለው ዳዊት የአሸናፊነት ምልክት ሆኖ ይጠቀሳል::

የግብጽ ጊዛ አንበሳ ሐውልት ሌላው የጥንታዊ ሐውልት ጥበብ ማሳያ ነው:: ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ2500 ዘመን የተገነባው የጊዛ ሐውልት በሰው ቅርጽ የተሰራ ነገር ግን አንበሳን የሚመስል ነው:: ፊቱ ሰው ይመስላል፤ ጸጉሩ ደግሞ የአንበሳ ነው:: ሰውነቱ የአንበሳ፤ ራሱ ደግሞ የሰው:: የግብጽ ፒራሚዶችን ያሰራቸው የፈርኦን ንጉሥ ካህፍሬ ምስል ነው የሚሉም አሉ:: መገኛ ቦታው በግብጽ ፒራሚዶች ውስጥ ነው:: 240 ጫማ ርዝመት፤ 20 ጫማ ስፋት እና 66 ሜትር ከፍታ አለው:: የሰውየው ፊት 6 ጫማ፣ ጆሮው 3፣ እንዲሁም አፍንጫው 5 ሜትር ከፍታ አለው:: ይህ ሐውልት ከ4500 ሜትር በላይ ከፍታ አለው:: ነፋስ፣ ዝናብ እና ፀሐይን  ተቋቁም ዛሬም ድረስ ለታሪክ ቀጥሏል::

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here