በብራዚል ፒራንጌ ኖርቴ የባሕር ዳርቻ በ1888 እ.አ.አ የተተከለው “የካሺው” ዛፍ ወደ ጐን ቅርንጫፉ እየሰፋ ስምንት ሺህ አራት መቶ ካሬ ሜትር ማልበሱን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
ዛፉ መጀመሪያ ከተተከለው ወይም ከበቀለው እናት ግንድ 164 ጫማ ወይም 55 ሜትር ወደ ጐን የተዘረጋ ነው:: በዚሁ ስፋቱም በትልቀነቱ በዓለም ክብረ ወሰን መዝገብ መስፈር ችሏል:: አሁን ላይም እድገቱን ወይም ጐን መስፋቱን አለማቆሙም ተጠቅሷል::
የድረ ገጹ ጽሁፍ እንዳመላከተው የዓለም ክብረወሰን መዝጋቢ ድርጅት ባለሙያዎችን ጠቅሶ የዛፉ እናት ግንድ አንድ ሲሆን ቅርንጫፍ የሚያወጣው ወደ ጐን ነው:: ቅርንጫፎቹ ክብደት ስለሚኖራቸው ወደ መሬት አዘምብለው አፈር ሲነኩ በዛው ስር አውጥተው የራሳቸውን ቅርንጫፍ ማብቀል ይቀጥላሉ::
በመሆኑም አንድ ግንድ መሰረቱ ቢሆንም ወደ ጐን የተዘረጉ ቅርንጫፎች ክብደታቸው እንዲጐነበሱ ሲገደዱ መሬት ነክተው ሌላ ስር እያወጡ የዛፉን ስፋት እንዳስቀጠሉት ነው የተብራራው::
ባለክብረ ወሰኑ ሁለት ሄክታር መሬት የሸፈነው ዘርፋፋው “የካሺው” ዛፍ እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያ የአንዱ ዛፍ ቅርንጫፍ እስከ 50 ሜትር ይዘረጋል።
በዚሁ ስሌት ባለ ክብረ ወሰኑ ሁለት ሄክታር ያለበሰው ዛፍ መሬት እየነኩ ስር አውጥተው እድገታቸውን ያስቀጠሉ የ70 ዛፎች ያህል ስፋት መያዙ ልብ እንዲባል ነው የጠቆሙት ባለሙያዎቹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም