የሰርከስ ትራኢት አቅራቢዋ ቻርሎት ሜዝ በገመድ ታስሮ ዓየር ላይ በተንጠለጠለ የብረት ቀለበት ላይ በጀርባዋ እና በክንዶቿ መታጠፊያ ብቻ ተመርኩዛ ረዢም ቆይታ በማሳለፏ በአንድ ቀን ሁለት ክብረወሰን ማስመዝገቧን ዩ ፑ አይ ድረገጽ ለንባብ አብቅቷል፡፡
አውስትራሊያዊዋ የ23 ዓመቷ ቻርሎቲ ሜዝ በክብ ቅርፅ በተሰቀለ ብረት ላይ በመገለባበጥ የተያዘውን የ47 ሴኮንድ የሴቶች ክብረ ወሰን በማሻሻል ነው አዲስ ክብረ ወሰን ያስመዘገበችው፡፡
ልምምዷን አጠናቅቃ ክብረወሰን ለማስመዝገብ በባለሙያዎች ፊት ትርኢቷን በአቀረበችበት እለት የተሰማት የቋንጃ መሸማቀቅ ህመም ፈታኝ እንደነበር ያልሸሸገችው ቻርሎት የተንጠለጠለውን ክብ የብረት ቀለበት በሁለት የእጆችዋ መታጠፊያ ይዛ ለ53 ሰከንዶች በመገለባበጥ የመጀመሪያውን ክብረወሰን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ከሷ በፊት ከተያዘው 47 ሰከንድ ክብረ ወሰን ስድስት ሰከንድ መብለጧን ልብ ይሏል፡፡
በዚያው እለት እጆችዋን ወደፊት እንዲሁም እግሮቿን ወደ ኋላ ዘርግታ በክብ የብረት ቀለበቱ ላይ በትከሻዋ ተንጠልጥላ በፅናት 63 ሰከንድ ከ18 ማይክሮ ሰከንድ በመቆየቷ ሁለተኛውን ክብረወሰን ማስመዝገቧም ተገልጿል- በድረገጹ፡፡ በአንድ ቀን ሁለት ክብረወሰን ያስመዘገበችው ወጣት ቻርሎት ስትለማመድ ሞራል የሚሰጣት ሰው ያልነበረ ቢሆንም ለክብረ ወሰን በበቃችበት እለት ግን በርካታ ሰው መገኘቱ እንዳበረታት ጠቁማለች፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም