“ሁሉም ሙዚቃዎች በዘመናቸዉ ጥሩ ናቸው”

0
206

ሙዚቃን አጥብቆ ይወዳል፤ ትውልድ እና እድገቱ  ባሕር ዳር ከተማ  ነው:: ማንኛውም ሰው ለሚወደው ሙያ እስትንፋሱ እስኪወጣ መታገል እና መስዋዕት መክፈል አለበት ብሎ ያስባል፤ ሙዚቃ አቀናባሪዉ አበበ ኪሮስ:: የበኩር እንግዳ አድርገነዋል፤

መልካም ንባብ!

 

ትውልድና እድገትህ ምን ይመስላል?

ተወልጄ ያደኩት ባሕር ዳር ከተማ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ በጠይማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣  ሰባት እና የስምንተኛ ክፍልን ደግሞ በቀድሞው በድልችቦ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ነው የተከታተልኩት::  ከዘጠነኛ  እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በግዮን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት:: ከ12ኛ ክፍል በኋላ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ  በጋዜጠኝነት (ጆርናሊዝም) በ10+3 ተምሪያለሁ::  “ጆርናሊዝምን’’ የመረጥኩት ጋዜጠኛ እሆናለሁ በሚል ሳይሆን በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው ከሚሰጡ ትምህርቶች ለሙዚቃ ይቀርባል በሚል ነው:: ግን ወደ ሙያው አልገባሁም::

 

ወደ ሙዚቃው እንዴት ልትገባ ቻልክ?

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ  ሙዚቃው ዓለም እንድገባ ያደረገኝ ያኔ አንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የሙዚቃ ትምህርት ራሱን ችሎ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጥ ስለነበር ከሌሎቹ ትምርቶች የበለጠ ትኩረት እሰጠው ነበር:: ክፍለጊዜው ሲደርስም በጣም ደስ ይለኝ ነበር:: ከዚያም በ1989 ዓ.ም  በባህልና ቱሪዝም አማካኝነት በአጼ ሠርጸ ድንግል ትምህርት ቤት በክረምት ወቅት ለሁለት ወራት ስለሙዚቃ ትምህርት እንደሚሰጥ ሰው ነገረኝ:: እኔም ጊዜ ሳላባክን ከሰልጣኞች አንዱ ሆንኩ:: በስልጠናውም ሙዚቃ ምን እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ተረዳሁ::  ከዛ በፊት ከእኔ በዕድሜ  ይበልጡ የነበሩ የሰፈር ልጆች ክራር ሲጫዎቱ ከስራቸው ቁጭ ብዬ እመለከት፤ አዳምጥም ነበር:: ከዛ ራሴ ከወዳደቁ ጣውላዎች  ክራር አዘጋጅቼ እንደነገሩ አድርጌ መሞከር ጀመርኩ:: ያኔ ምንም አይነት እውቀት አልነበረኝም፤ ክራሩን ከማየት ውጪ በእጄ እንኳ ነክቼ አላውቅም ነበር:: እያንዳንዱ የክራር  ክር  ምን አይነት ድምጽ እንዳለው አላውቅም ነበር::  በስልጠናውም ሙዚቃ፣ ቅኝት፣ ኖታ እና ሪትም ምን እንደሆኑ ተረዳሁ:: የነበረኝ ልምድም  በሥልጠናው ዳበረ ግንዛቤየም ሰፋ:: የተሻለ መሞከር ጀመርኩ:: ከዛ ፍላጎቴን የሚያውቅ አንድ የሠፈር ልጅ ጥራቱን የጠበቀ የራሱን ክራር በስጦታ ሰጠኝ:: ሌት ተቀን እያልኩ መለማመድ ጀመርኩ፤ በሂደትም ክራር መጫዎት ቻልኩ::

 

ሰርከስ አልማን እንዴት ነበር የተቀላቀልከው?

ያኔ ለሙዚቃ ስልጠናው ስንሄድ ሰርከስ አልማ ከሚሠሩ ልጆች ጋር እንገናኝ ነበር:: ልጆቹም ያለኝን ችሎታ በማየት ሰርከስ አልማ መግባት እንደምችል ነገሩኝ:: ከዚያም በ1994 ሰርከስ አልማ ገባሁ:: በወቅቱ አልማ የባህል ቡድን እንጅ ሰርከስ አልነበረውም:: ሰርከስ ትግራይ እና ሰርከስ ጅማ በወቅቱ በጣም ታዋቂ ነበሩ:: ከነሱ በማየት እኛም ተግባራዊ ማድረግ ጀመርን:: ሰርከሰኞች ሰርከሱን የሚያሳዩት በሙዚቃ በመታጀብ ነበር:: በሰርከሱም  ለኪስ 120 ብር በወር እየተከፈለኝ ክራር መጫዎት ጀመርኩ::

አልማ እየሠራሁ ቤዝ የሚባል የሙዚቃ መሳሪያ የመጫዎት እድሉን አገኘሁ:: ቤዝ የጊታር አይነት ነው:: ድምጹ ለሙዚቃ መሠረታዊ የሚባል እና በጣም ወሳኝ ነው:: ከዚያም ክራር የሚጫዎት ሌላ ሰው ሲመጣ እኔ ወደ ቤዝ ጊታር ዞርኩ:: ልምድ የለኝም፤ ግን እጄ አያርፍም፤ መነካካት ስለምወድ ድምጹ ማረከኝ እና ወደ ቤዙ ተሳብኩ:: ባንዱን ሙሉ ለማድረግ እኔ ቤዙን ያዝኩ ሌላ ሰው ክራሩን ያዘ::

 

ሙዚቃ ማቀናበሩንስ እንዴት ለመድክ?

ትምህርቴን 1990 ዓ.ም ላይ አጠናቅቄ ሙሉ ስዓቴን ሙዚቃ ላይ ማዋል ጀመርኩ:: ኦሳ የሚባል ድርጅት በየቀበሌው ያቋቋመው የጸረ – ኤድስ ክበብ  ነበር:: እኔም ቀበሌ 10 በሚገኘው  እፀ-ሕይዎት የሚባል ክበብ ገባሁ:: ክበቡ  በሙዚቃ ጭምር ነበር ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥረው እኔም ክራር እጫዎት ነበር:: ከጠዋት ጀምሮ እስከ 10 ስዓት ድረስ ልምምድ እናደርግ ነበር:: ከዚያም በ1996 ዓ.ም ኪቦርድ ለመጫዎት ሙከራ ማድረግ ጀመርኩ:: ኪቦርድ በባህሪው እንደሙሉ ባንድ አድርጎ ስለሚያጫውት ሌት ተቀን በራሴ ማንዋሉን በማንበብ ተለማምጄ መጫዎት ቻልኩኝ:: ክራሩንም ተውኩት:: ሙዚቃ ማቀነባበር የጀመርኩትም ያኔ ነው:: ከዚያም በ1998 ዓ.ም ሙሉዓለም የባሕል ማዕከል  በባሕል መሳሪያ ተጫዋችነት ተወዳድሬ ተቀጠርኩ:: ኪቦርድ ብጫዎትም ብዙ የሚጎድለኝ ነገር ስለነበር ያን ጉድለቴን እስክሞላ ክራር ለመጫዎት በመወሰን ነበር በክራር ተጫዋችነት የተቀጠርኩት:: ሁለት ዓመት ክራር ከተጫዎትኩ  በኋላ አሁንም የሙዚቃ መሳሪያ ሳይ መነካካት ስለምወድ  የተቀመጠ ኪቦርድ ነበር እሱን መጫዎት ጀመርኩ፤ በባህል ማዕከሉ የሚሠሩ መዝሙሮች ሲኖሩም በኪቦርዱ  እቀርጽ  ነበር:: ምድቤ ግን የባህል መሳሪያ መጫዎት ነበር:: ይህን ማደርገው ፍላጎት ስላለኝ ነው:: 2000 ዓ.ም አካባቢ ሚሊኒዬም ባንድ የሚባል ዘመናዊ ባንድ ተቋቁሞ ነበር:: ከዚያም ባንዱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሙሉዓለም የባህል ማዕከል ሲጠቃለል ወደዛው ገባሁ:: በ2010 ዓ.ም የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ሲመጣም ኪቦርድ ተጫዋች ሆንኩ::

ለመጀመሪያ ጊዜ ስቱዲዮ ኮምፒዩተር ያየሁት በለጠ የሚባል ልጅ ከአዲስ አበባ መጥቶ ሙሉዓለም ሲቀጠር ‘መሳሪያው አለኝ፤ ለምን አብረን አንሠራም’ ሲለኝ ተስማምቼ  አብሬው መሥራት ስጀምር ነው::  ለመጀመሪያ ጊዜ ኪቦርድ ላይ የምቀርጸው ሙዚቃ እንዴት ኮምፒዩተር ላይ እንደሚቀረጽ አወቅኹኝ:: የባህል ማዕከሉ የሚሠራቸውን ሕብረ ዝማሬዎች ማቀናበር ጀመርኩ:: በተለይም የኮረና ሕብረ ዝማሬን አቀናብሬያለሁ:: የኦሮሚኛ የዘይኑ ሙሃባውን ስለኮሮና የታጫዎተውን፣ የመለሰ ካሳሁንን፡- ናፈቀኝ ሀገሬን፣ ያኢስ ራያ፣ አጄልጂል፣ ሰንደልዬን፤ የአበበ ሰማኸኝን ሰናድሬ፣ የገብርየን ቢተው አደቡን ላስገዛው፤ የአሸናፊ ተክለኃይማኖትን አቻም የለሽ የሚለውን፣ የሙሉዓለም የባሕል ማዕከሉ ድምጻዊያን ያወጡት የጋራ አልበም ውስጥ ጎንደርኛውን አቀናብሬያለሁ:: እንዲሁም ጎጃምኛውንም በጋራ ሠርተናል:: ሌሎች ስማቸውን በደንብ ማስታወስ አልቻልኩም እንጂ የበርካታ ጀማሪ ድምጻዊያንን ሙዚቃ አቀናብሬያለሁ::

 

ሙዚቃ ከማቀናበር በተጨማሪ ሌላ የምትሞክረው ችሎታህ ምንድን ነው ?

አሁን ከሙዚቃ በተጨማሪም ዜማ መስጠት ለምጃለሁ:: ዜማ መሥራት የጀመርኩት ከሙዚቃ ማቀናበር በመጣ ልምድ ነው:: ድምጻዊያን ሙዚቃ ቀርጸው ሲመጡ ያኔ ዜማውን አስተካክላለሁ:: የት ላይ ቢስተካከል ቆንጆ እንደሚሆን አቀናባሪው ያውቀዋል:: ሙዚቃው ለጆሮዬ ካልጣመኝ ላቀናብረው አልችልም:: ስለዚህ ያን ዜማ አስተካክላለሁ:: ለመጀመሪያም ጊዜ የጎጃምኛ ዜማ ሰርቼ ቢያድጌ ለሚባል ጀማሪ ሙዚቀኛ ሰጥቻለሁ:: የሙዚቃ መሳሪያ በመነካካት ዜማ ይመጣልኛል::

 

ሙዚቃ ከባድ ነው ወይስ ቀላል? ለማቀናበርስ የትኛውን ሰዓት ትመርጣለህ?

ሙዚቃ ከባድ ነው:: የአምስት ደቂቃ ሙዚቃ ለመሥራት የረጅም ጊዜ ድካም እና ልፋት ይጠይቃል:: ሪኮርዲንግ (ቀረጻ) አለ፤ ስልተምት አለ፤ የሚያስፈልጉ ድምጾች አሉ፤ ድምጻዊው ጋር ይሄዳል ወይስ አይሄድም የሚለውን ማረጋገጥ አለ:: ሙዚቃ ሰውን የማሳመን ሥራ በመሆኑ ከባድ ነው ብዬ ነው የማስበው:: ሙዚቃ የማቀናብረው በማንኛውም ጊዜ ነው:: በምሽትም በሌሊትም ሊሆን ይችላል:: ጊዜ አይገድበኝም::

 

“የኢትዮጵያ ሙዘቃ ድሮ ቀረ” የሚሉ አሉ፤ ይህን እንዴት ታየዋለህ?

የሀገራችን ሙዚቃ ሁሉም በዘመኑ ልክ ነው ብዬ ነው የማስበው:: የድሮዎቹ ዘመን አይሽሬ ናቸው በሚለው ብስማማም  አሁንም ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች አሉ የሚል እምነት አለኝ:: በድሮው ዘመን በራሱ ቆንጆ ሙዚቀኛ አለ፤ ቆንጆ ያልሆነም አለ:: በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጥሩ ጥሩ ዜማና ግጥም ቅንብር ያላቸው ሙዚቃዎችና ድምጻዊያን አሉ:: እንደዚሁ ጥሩ ድምጽ የሌላቸው ግጥሙ እዚህ ግባ የማይባል፣ ቅንብሩም እንደዚሁ ጥሩ ያልሆነ ሙዚቃ አለ:: ሁለቱም በየራሳቸው ዘመን መጥፎም ጥሩም ጎን አላቸው ብዬ ነው የምፈርጃቸው::

 

በአሁኑ ዘመን ድምጻዊያን የሚያሰሙን በኮምፒዩተር የታገዘ ተፈጥሯዊ ያልሆነ ድምጽ ነው፤ ይህን እንዴት ታየዋለህ?

ይህ ቴክኖሎጂ ወደኛ ሀገር የገባው በቅርብ ጊዜ በመሆኑ እንጅ  በውጪው ዓለም  የተለመደ ነው:: የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም:: ኮምፒዩተር በመኖሩ የሙዚቃውን ደረጃ እንዲጠብቅ ያደርገዋል እንጅ እየጎዳው አይደለም ብዬ ነው የማስበው:: በእርግጥ ማንኛውም ሰው በኮምፒዩተር በመታገዝ ሊዘፍን ይችላል:: ነገር ግን ስሜት አልባ ነው የሚሆነው:: ለአድማጭ ጆሮ ተስማሚ አይሆንም:: ቅንብሩ ብዙ የአርትኦት ሥራ (ኤዲቲንግ) ስለሚኖረው ስሜት አይሰጥም እንጅ መዝፈን ይችላል:: ሙዚቃ ስሜት የሚሰጥ መሆን አለበት:: አንዳንድ የድሮ ሙዚቃዎች  ከእንደገና በዘመናዊ መንገድ ቢሠሩ  ብለን የምናስባቸው አሉ:: እንደ ባለሙያ ስናገር ፈርሰው እንደገና ቢቀናበሩ ተብለው የሚፈረጁ አሉ:: ያኔ ከነ ጉድለታቸው የወጡት ቴክኖሎጂው ስለሌለ ነው ብዬ ነው የማስበው::

ከዛ ይልቅ የአሁኑ ጊዜ ሙዚቃዎች ቶሎ የሚሰለቹት የአብዛኛዎቹ ግጥምና ዜማዎች ጥልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ስለማይችሉ ነው::  ግጥሞቹና ዜማዎቹ ለባለሙያው ስላልተሰጡ ነው:: ሙዚቃ በተፈጥሮ የሚሰጥ ችሎታ ነው:: ብዬ ነው የማስበው:: እናም ችሎታ ያላቸው ሰዎች ግጥሙንና ዜማውን ቢሠሩት መልካም ነው:: ይሁንና  አሁን ላይ ጀማሪ ድምጻዊያን የግጥም እና የዜማ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች ከፍለው ለማሠራት ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቋቸው እነሱን ማሠራት አይችሉም:: በዚህ ምክንያት ራሳቸው ግጥሙንም ዜማውንም ለመሥራት ይገደዳሉ:: በጀማሪ ገጣሚም ስለሚጠቀሙ ዘፈኑ ያን ያህል ሳቢ እና ማራኪ ሳይሆን ይቀራል:: እኔ በዚህ ጉዳይ የምመክረው   ድምጻዊያን የግጥም እና የዜማ ችሎታ ከሌላቸው  በዘርፉ ችሎታ ላላቸው ባለሙያዎች ግጥሙንና ዜማውን ቢተውሏቸው መልካም ነው:: በእርግጥ ለታዋቂ የሙዚቃ ግጥም ደራሲ እና የዜማ ባለሙያ እንዲሳተፉ ማድረግ ከባድ ነው:: ክፍያው በጀማሪ የማይታሰብ ነው:: አሁን ላይ ከ30ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ይጠየቃሉ::

 

የሀገራችንን አንድነትና ሰላም እንዲጎለብት የሚያደርጉ ሙዚቃዎች በበቂ ሁኔታ ተሰርተዋል ብለህ ታስባለህ?

ሙዚቃ በባሕሪው የራሱ የሆነ ነጻነትን የሚጠይቅና የሚፈልግ ሙያ ነው:: ነገን የሚያሳይ መሆን አለበት:: እንዳለመታደል ሆኖ በኛ ሀገር ይህ ሁኔታ አልተለመደም:: ሙዚቃችን ሕጸጽ አዉጪ ቢሆን ኖሮ ነጋችንን ለማስተካከል ይረዳን ነበር:: ሕዝብንም መንግሥትንም የሚያስተምር መሆን ነበረበት:: ነገር ግን ያ አልሆነም፤ ለዚህ አልታደልንም:: ሰላምን የሚሰብኩ ሙዚቃዎች በበቂ ሁኔታ አልተሠሩም ብዬ ነው የማስበው:: ምክንያቱም አድማጭ የላቸውም:: ስለፍቅር (የወንድ እና የሴት) እና የሰላም ሙዚቃ አንድ ላይ ቢወጡ ገዥ የሚኖረው ስለፍቅር የተዜመው ነው:: ለአብነትም ከሰሞኑ ስለ ሰላም የተቀነቀነ ያቀናበርኩት ሙዚቃ ነበር:: ሆኖም እስካሁን ስፖንሰር የሚያደርገው አልተገኘም:: ስለዚህ ገዥ ከሌለው ትርፉ ድካም ነው:: ሆኖም በዚህ ጉዳይ የሚመለከተው አካል እና ሕብረተሰቡም ቢሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል::

 

የኢትዮጵያ ሙዚቃ አሁን ባለበት ደረጃ አድጓል ብለህ ታስባለህ?

ሙዚቃችን አድጓል ብዬ መናገር አልችልም:: ምክንያቱም የሀገራችን ሙዚቃ ዘርፈ ብዙ ችግር አለበት ብዬ ነው የማስበው:: ሙያተኛው በተፈጥሮ በተቸረው ችሎታ ተገፋፍቶ ይመጣል እንጅ በትምህርት ታግዞ ያመጣው ነገር የለም:: ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን በቂ የሙዚቃ ማስተማሪያ የትምህርት  ክፍሎች (ዲፓርትመንቶች) የሏቸውም::  ይህ ባለመሆኑ ሙዚቃው ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው:: ጥራት የሌላቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች ናቸው ያሉን:: ሌላው የቅጂ መብት (የኮፒ ራይት) ችግር ነው:: አንድ ሰው ሙዚቃ ሢሰራ ጊዜውን፣ ገንዘቡን አዕምሮውን ተጠቅሞ ነው የሚሠራው:: ታዲያ ይህን  ሁሉ ነገር መሰዋዕት ከፍሎ ተጠቃሚ አይደለም:: ገቢው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: በተቃራኒው የመገናኛ ብዙኃን፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ሙዚቃዎችን የሚጠቀሙ አትራፊ ናቸው:: እነዚህ ተቋማት ተገቢውን ክፍያ ለሙያተኛው ቢከፍሉ ዘርፉ ያድግ ነበር፤ ሙያተኛውም ተጠቃሚ ይሆን ነበር::

 

በሙዚቃ ሥራ የት ቦታ ሂደህ ታውቃለህ?

ከሀገር ውጪ የሙዚቃ መሳሪያ ለመጫዎት ሱዳን ካርቱም ሄጃለሁ:: የክልሉን ከተሞች አዳርሻለሁ:: ከክልሉ ውጭ ደግሞ አዋሳ፣ አዲስ አበባ፣ መቀሌ የመሄድ እድሉ አጋጥሞኛል:: በዚህም ሙዚቃ ቋንቋ ነው የሚለውን አረጋግጫለሁ::

 

በሙዚቃ ማቀናበር ሥራህ ችግር አጋጥሞህ ያውቃል?

እኔ ሙዚቃ ሳቀናብር በቂ ክፍያ አላገኝም:: እንደ ድካሜ አይደለም የሚከፈለኝ:: ሆኖም ፍላጎት ስላለኝ  ወደ እኔ የሚመጡ ድምጻዊያን  ያላቸውን የመክፈል አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት እሠራለሁ:: በሙዚቃ ሕይዎቴ ከባድ ችግር ወይም ሥራየን የሚፈትን ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም:: ሆኖም እንደ ችግር ከተቆጠረ ድምጻዊያን ከእኔ ጋር ለማቀናበር ሲመጡ በመጀመሪያ ግማሽ ክፍያ (ቀሪውን) ተቀብዬ ነው የማቀናብርላቸው:: ሙዚቃው ካለቀ በኋላ ደግሞ ግማሹን ክፍያ ያልከፈሉኝ ድምጻዊያን አሉ:: ሆኖም ሙያውን ስለምወደው አሁንም አከፋፈሉን አላስተካከልኩትም:: ማንኛውም ሰው ለሚወደው ሙያ እስትንፋሱ እስኪወጣ መታገል እና መስዋዕት መክፈል አለበት ብዬ የማምን ሰው ነኝ:: ለአንዳንድ ሰዎች  የምትወዱትን ሥራ ሥሩ:: ያኔ ችግር ወይም ፈተና ቢያጋጥማችሁ አንኳ በቀላሉ ታልፉታላችሁ፤ እንደፈተናም አትቆጥሩትም ማለት እወዳለሁ::

 

ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ!

እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here