በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ብዙዎችን
ለረሃብ፤ለመፈናቀል፣ ለሞትና ለእንግልት እየዳረገ ነው፡፡ በተለይም በዚህ ዓመት
በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች መደበኛው ዝናብም ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡና ምንም
ዓይነት ዝናብ ያልጣለባቸው ቦታዎች መኖር ከዓመት ዓመት በዝናብ ምክንያት
ምርት አልባ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ችግሩ ከሚገመተው በላይ እንዲከብድ ምክንያት
ሆኗል፡፡
ቀስ በቀስ ከአንዱ አካባቢው ወደሌላው እየተባባሰ የመጣው ይህ ድርቅ በሰውና
በእንስሳት ሕይወት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለማቃለል፤የሁሉንም ርብርብ
የሚጠይቅና ለይደር የማይተው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ድርቁ ከሰላም መደፍረሱ ጋር
ተዳምሮ አስከፊ ሰብዓዊ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉ አቀፍ ርብርብን ይጠይቃል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ብዙዎች ለተላላፊ በሽታና ለሞትን
እየተጋለጡ ነው፡፡ ሰዎች በእለት ምግብ፣ እንስሳት በውሃና በግጦሽ እጦት ምክንያት
ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ችግሩን እንዳያልፉት እንኳ ክልሉ ውስጥ ያለው የጸጥታ
ችግር እንደ ተጨማሪ እክል በመሆን የመውጫ መንገዱ እንዲጠብ አድርጓል፡፡ ነገሩ
በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ሆኖ እንዳይቀጥል ሰላም በሚያመጡ ጉዳዮች
ላይ በአንድ በኩል፤ በሌላ ገጽ ደግሞ አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታን ለተጎጂዎች ማድረስ
ቀጠሮ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው፡፡
ዓለምን እኩል እየፈተነ ያለው ድርቅ ወትሮውኑም የዝናብ እጥረት
የነበረባቸውን አካባቢዎች የበለጠ ችግር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ አፋጣኝ
ምላሽ፤የብዙዎችን እርዳታ፤ርብርብና መተጋገዝ የሚጠይቀው ይህ ክስተት ክልሉ
ያለበት የጸጥታ ችግር ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም ሆነ እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት
ሆኗል፡፡ እርዳታው በዘገዬና በተራዘመ ቁጥር ደግሞ በተለይም ሕጻናት፤ሴቶችና
አረጋውያን የበለጠ የመጎዳት እድላቸው ይጨምራል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ወቅት
ሁሉም በመተጋገዝና በመረዳዳት ችግሩን ማስቀረት ባይቻል እንኳ ችግሩን ማቅለል
ከሁሉም የሚጠበቅ ሰብዓዊ ግዴታ ነው፡፡ ዘላቂ ሰላምን የሚያሰፍኑ መንገዶችን
መከተል እና በመሰረታዊ የልማት ጉዳዮች ላይ ማተኮርም ድርቁ ረብን እንዳያዋልድ
የማድረግ አቅም ይኖረዋል፡፡ ድርቅ በተፈጠሮ ጉልበትም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ዋናው
ነገር ድርቁ ወደ ረሃብ ተቀይሮ ሰባዊ ቅጣት እንዳይደረስ መትጋቱ ነው፡፡ ረሃብ
ሰውሰራሽ በመሆኑ “ሰው ለሰው” ከተረዳዳ ችግሩን ማቅለል ይቻላል፡፡ በመረዳዳት
እና በመተጋገዝ፣ አብሮም በመቆም ጊዜ ለማይሰጠው ድርቅ ለወለደው ረኃብ
ሁላችንም የመፍትሄው ባለድርሻ እንሁን!!