የዋልሁት በባሕር ዳር መሃል ከተማ፣ በነጭ አፍ ዳውንታውን ነበር። በደስታ ፏ ብልጭ ያልሁበት የውሎ ፍፃሜ በዝናብ እንደሚታጀብ የሰማዩ ጉርምርምታ አሳሰበኝ። በፍጥነት ወደ መኖሪያ ቤቴ ለማምራት ተዘጋጀሁ፤ ሞተር ብስክሌቴን ካቆምሁበት አስነስቸ ጉዞ ጀመርሁ። የዝናቡ መጠን ሲጨምር እኔም የሞተሬን ፍጥነት እያሳደግሁ ጉዞየን አፋጠንሁ። ነገር ግን የጉዞዬ ፍጥነት በተለምዶ ኖክ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ አለፍ ብሎ ተገታ። ከአንድ ባንክ በረንዳ ጥበቃው ጎን ቁሜ የዝናቡን ውርጅብኝ አስታገስሁ።
በነጎድጓድ ድምፅ ታጅቦ የጣለው ከባድ ዝናብ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ወደ ካፊያነት ተቀየረ። ተመስገን! አልሁና ከጎጆዬ ለይቶ መንገድ ላይ ሊያሳድረኝ ነው እንዴ! የሚል ስጋት ላይ ጥሎኝ የነበረውን የዝናብ ውርጅብኝ ጋብ ማለት አረጋግጨ በድጋሜ ጉዞ ጀመርኩ።
ጉዞዬን በቀጠልሁበት አስፋልት መንገድ ላይ ወደየመዳረሻው በፍጥነት የሚወርደው የጎርፍ ድምፅ ፍርሃትን ያጭራል። ምንም አይነት አማራጭ ስላልነበረኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ። “የተባበሩት” ተብሎ ከሚጠራው መስቀልኛ መስመር ላይ እንደደረስኩ ወደ መኖሪያ ሰፈሬ የሚያደርሰኝን ደቡባዊ አቅጣጫ ይዠ አደባባዩን አቋረጥኩ። ከዚህ በኋላ ነበር አስከፊውን ጉዞ በባሕር ዳር ከተማ አስፋልት መንገድ ለመጋፈጥ የተገደድኩት።
ከተባበሩት አደባባይ /መስቀልኛ መንገድ/ ትንሽ ወረድ ብሎ እስከ ባለ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለው አስፋልት በዕለቱ ዝናብ ምክንያት በጎርፍ ሙሉ በሙሉ ተሸፍኗል። የዝናቡን መጣል ተከትሎ የመንገድ መብራት ጠፍቷል። በዚህም የተነሳ መንገዱ በጎርፉ ውሃ መጥለቅለቁን መገንዘብ ተስኖኝ ከነሞተሬ ጉርፉ ውስጥ ተቀላቀልኩ፤ ኧረ! እንዲያውም ከነሞተር ብስክሌቴ ጎርፉ ውስጥ ገብቸ ዋኘሁ ብል ይገልጸዋል።
ጎርፉ ውስጥ ገብቸ ስዳክር ከቤቴ ታደርሰኛለች ባልኋት ሞተር ብስክሌት ሞተር ውስጥ የገባው ውሃ የጉዞ እድሜዋን አሳጠረው። ከሞተሯ ወርጀ መሬት ስረግጥ የጎርፉ ውሃ ጉልበቴ ላይ ደርሷል። ምንም አይነት አማራጭ አልነበረኝም፤ በዚያ አስፈሪ ጨለማ ሙቷን ሞተሬን እየገፋሁ ጎርፉን በብዙ እንግልት አልፌ በፈጣሪ እርዳታ መኖሪያ ቤቴ ለመድረስ በቃሁ። በአንድ ክረምት ባሕር ዳር ከተማ ዋና አስፋልት መንገድ ላይ በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ያሳለፍኩትን አስቸጋሪ የጉዞ ገጠመኝ አቀረብኩ። የፅሑፌ ዓቢይ ትኩረት ግን የእኔን ገጠመኝ ብቻ ማስገንዘብ አይደለም። በባሕር ዳር ከተማ የክረምት ወራት የሚከሰት የጎርፍ መጥለቅለቅ የሚያስከትለው ችግር እኔው ላይ የደረሰው አንድ መገለጫ እንዲሆን በማሰብ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ውበት ዙሪያ ብዙ ተፅፏል፣ ተቀንቅኗል … ሁሉም ትክክል ነው። ባሕር ዳር ውብ ከተማ ናት። አሁን ላይ ደግሞ በቀደምቱ ዋና ጎዳና ግራ እና ቀኝ አሃዱ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ውበቷን ይበልጥ እያጎላው መጥቷል። ጣና ሐይቅ እና ባሕር ዳር ከተማ በሚዋሰኑባቸው አቅጣጫዎች ክፍት እንዲሆኑ የተደረጉት ከተማዋን ከሐይቁ የሚያገናኙ መዳረሻዎችም የውበቷን ድምቀት ከፍ እንዲል አስችለውታል፤ ከሐይቁ የሚወጣው ነፋሻማ አየርም የበጋውን ሃይለኛ ሙቀት ማስታገስ ጀምሯል። እሰየው! የሚያስብል ድንቅ የኮሪደር ልማቱ ውጤት መሆኑንም ልብ ይሏል።
ይህ መልካም ነገር ቢሆንም የተፋሰስ ችግሩ ግን አሁንም መፍትሄ አላገኜም፡፡የክረምቱን መግባት ተከትሎ ዘወትር በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ ይከሰታል።
ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ድርግም የሚለው የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት መቋረጥም ውበቷን በእጅጉ የሚያጎድፍ ነውና ትኩረት ሊሰጠው ግድ ይላል።
በባሕር ዳር ከተማ ከቀድሞው ነዳጅ ማጠራቀሚያ (ዲፖ) ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ፣ ሜላት ካፌ አካባቢ፣ አሮጌው አውቶቡስ መናኸሪያ፣ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና መስቀል አደባባይ መሃል እንዲሁም ከተባበሩት አራት ማዕዘን አካባቢ ወደ ባለ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ ያሉት የባሕር ዳር ከተማ ዋና የአስፋልት መንገዶች ክረምቱን ተከትሎ በሚጥል ዝናብ ሁሌም በጎርፍ ተጥለቅልቀው እንቅስቃሴን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
በባሕር ዳር ከተማ አብዛኛውን ጊዜ መምሸቱን ተከትሎ የክረምቱ ዝናብ ሲጥል መመልከት የተለመደ ነው። ይህ ሰዓት ደግሞ በተለያዬ ምክንያት ከመኖሪያ ቀየው ርቆ የዋለ ሁሉ ለመመለስ የሚሰናዳበት ነው።
በከተማዋ የሚጥለው ዝናብ የሁሉንም ጉዞ ገትቶ ያቆየዋል። ዝናቡ ሲያባራም ጉዞ ይጀመራል። በዚህ ወቅት ነው ታዲያ እነዚያ በጎርፍ የሚሞሉ የባሕር ዳር ከተማ ጎዳናዎች ነዋሪው እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ ፈቃደኛ የማይሆኑት። ተሽከርካሪ ያለው ለመጓዝ ሲጣደፍም በእግረኛው ላይ የጎርፉን ውሃ ከአስፋልቱ ላይ አንስቶ ያከናንበዋል።
ከፊሉ ተጓዥ ጫማውን አውልቆ ለመጓዝ ይጣጣራል፤ ገንዘብ አለኝ ያለ ተጓዥ ደግሞ የመንገዱን በጎርፍ መሙላት አይተው “እናሻግርዎት?” በሚሉ ጎዳና ተዳዳሪ ጎረምሶች ትክሻ ላይ ታዝሎ መሻገርን ምርጫው ያደርጋል፤ ገንዘብ ከፍሎ ከጎረምሳ ተከሻ ላይ ፍጢጥ በማለት አስቸጋሪውን መንገድ ማቋረጥ ይጀመራል።
የከፋው ችግር ግን “ተሸክሜ ላሻግርዎት” ብሎ ከእርስዎ ጋር የተስማማው ጎረምሳ ቃሉን ማጠፍ ሲጀምር ነው። የዕለቱን ዝናብ መጣል ተከትሎ የሥራ እድል የተፈጠረለት ጎረምሳ ታዲያ ጎርፉን አሻግሮዎት ከማጠናቀቁ በፊት መሃል ጎርፉ ላይ እያሉ “ሂሳብ ይጨምሩ? አልያ እዚህ ላይ ላወርድዎ ነው?” የሚል እንግርግሪያ አዘል ጥያቄ ያቀርባል። አማራጭ አልባው ተሻጋሪም ለመጨመር ይስማማል፤ አልያም “አውርደኝ” ብሎ ከነጫማው የፈራው ጎርፍ ውስጥ እየተንቦጫረቀ ለመጓዝ ይገደዳል። የጎርፉ መጥለቅለቅ በሚያስከትለው የጉዞ መስተጓጎል ነዋሪው ለዝርፊያ ይዳረጋል፤ ሌሎችም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሙታል። በመሆኑም ይህ በባሕር ዳር ከተማ አስፋልት ጎዳና ላይ በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚከሰት ጎርፍ መጥለቅለቅ አንደኛው የውበቷ አጉዳፊ መገለጫ ነው።
ጎርፍ መጥለቅለቁ ብቻ አይደለም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የክረምት ወራት ችግር፤ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር የከተማዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይቋረጣል። በአንዳንድ አካባቢዎችም የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች መቆም ተስኗቸው ከነተሸከሙት ገመድ መሬት ላይ ያርፋሉ።
ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል ምናልባት የዝናቡን ጋብ ማለት ተከትሎ ከተለቀቀ ደግሞ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል።
ባጠቃላይ በባሕር ዳር ከተማ አውራ መንገዶች ላይ የሚከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመብራት መቋረጥ የሚያስከትለው ችግር ለመጠቃቀስ ከሞከርሁትም በላይ ነው። ችግሩ በየዓመቱ እየተስተዋለ ቢቀጥልም አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግን አልተገኘም።
ለባሕር ዳር ከተማ የክረምት ወራት ጎርፍ አደጋ በዋናነት ነዋሪዋ ተጠያቂነትን ሊጋራ ግድ ይላል። ምክንያቱም ጨለማን ተገን በማድረግ በፌስታል እና በጆንያ ቆሻሻ ሞልቶ መንገድ ላይ የሚጥል ከነዋሪዋ ውጭ ማን ሊባል ይችላል? ይህ ተግባር ነው ተፋሰሶችን እየዘጋ የጎርፍ መጥለቅለቅን የሚያስከትለው። በመሆኑም ለዚህ ችግር ቁልፉ መፍትሔ ከከተማዋ ነዋሪ እጅ ይገኛል። ቆሻሻን በዘፈቀደ መንገድ ላይ መጣል ሊታረም የሚገባው አስነዋሪ ተግባር ነው።
የከተማዋ አስተዳደርም ቢሆን በዘፈቀደ የተጣሉ ቆሻሻዎች የመንገዶችን አፋሳሽ ከመድፈናቸው በፊት በማስወገድ ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ይገባዋል። በመንገድ ግንባታ ጉድለት የተፈጠረ የተፋሰስ ችግርም የማስተካከል እርምጃን የሚጠይቅ ስለሆነ በከተማ አስተዳደሩ መፈጸም አለበት።
“ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ ነውና በክረምቱ ዝናብ ላይ የሚታከለው የመብራት መቋረጥም ምክንያቱ ተፈትሾ መስተካከል ይገባዋል።
የክረምቱን መግባት ተከትሎ በዚህ ዓመትም ችግሩ እንዳይቀጥል በማለት የታዘብኩትን ከብዙ በጥቂቱ በዚህ ልክ አቀረብኩ። ይህ አምድ የሁላችንም ሃሳብ የሚስተናገድበት ነው። እናንተም የታዘባችሁትን ፃፉበት። የኔን በዚህ ቋጨሁ፡፡
ቸር ይግጠመን!
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም