ሃይማኖታዊ በዓላት እና ማሕበራዊ ፋይዳቸው

0
164

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት  ሕዝቡን እርስ በርስ ከማስተዋወቅ ባለፈ አንድነትን ለማጠናከር ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡ በጥር ወር ብቻ የሚከበሩት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ እና በአደባባይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ለዚህ ዋና ማሳያ  ናቸው፡፡

በየዓመቱ በላሊበላ ከተማ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል  በርካታ ምእመናን እና ጎብኚዎች ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ይታደሙበታል፡፡ በዚህም ወደ ከተማዋ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለማክበር የአካባቢው ወጣቶች ዘር፣ ቀለም፣ ጎጥ፣ ሀብታም፣ ደሀ…ሳይሉ ሁሉንም የመጡትን እንግዶች ማረፊያ ቦታ አዘጋጅተው ዝቅ ብለው እግራቸውን ያጥባሉ፤ ረሀባቸውን ያስታግሳሉ… ይህ ድርጊት ከነዋሪዎች አልፎ ከተማዋን በእንግዶች ዘወትር እንዳትረሳ ያደርጋታል፡፡ የሕዝብን ማሕበራዊ ግንኙነት ያጠናክራል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ሌሎችንም ማረፊያ ሆቴል  በማስያዝ፣ መረጃ በመስጠት፣ የጤና እክል የገጠማቸውን ወደ ጤና ተቋም በማድረስ የሚያደርጉት መስተንግዶም ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስገኘው  ማህበራዊ ግንኙነት ላቅ ያለ ነው፡፡ ለአብነት በ2017 ዓ.ም በላሊበላ የገና በዓልን ለማክበር ለመጡ እንግዶች የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ወጣቶች የእግር አጠባ ሥነ ሥርዓት አድርገዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ የደብረ ሮሀ ቅዱስ ላሊበላ አስተዳዳሪ ለአሚኮ እንዳሉት ለሰው ልጆች ከፍቅር ሁሉ የሚቀድመው ወደ ከተማዋ ሩቅ መንገድ ተጉዘው የደረሱ ታላላቆችን፣ ባልንጀራን…ተቀብሎ በዚህ መንገድ እግር ማጠብ፣ ቦታ ማሳየት…በእንግዶች ልብ የማይረሳ ትስስርን ይፈጥራል፡፡  ሃይማኖቱ ያስተማረው የትሕትና ምልክትም  ነው፡፡

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ወንድምነህ ወዳጀ በበኩላቸው “በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል  የሚከናወን የእግር ማጠብ ሥነ ሥርዓት በዓሉ የፍቅር፣ የትሕትና፣ የሰላም መሠረት መሆኑን የምንማርበት ነው” በማለት አስገንዝበዋል፡፡

በኦርቶዶክስ ተከታዮች ዘንድ በዓለም ብሎም በሀገራችን በጥር ወር ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት ሌላው ነው፡፡

ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

ለሦስት ቀናት ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ በተከታታይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል

ታቦታቱን ለመሸኘት ብሄር ሳይለይ በአንድ ላይ በአካባቢው ነዋሪ ሲከበር ማኅበራዊ ትስስርን ይፈጥራል፤ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ሕይወት እና አንድነት በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክራል፡፡

የጥምቀት በዓል የውጪውን ነዋሪ  ወደ ሀገር ቤት፣ የገጠሩን ወደ ከተማ፣ የከተማውን ወደ ገጠር ከያሉበት ያሰባስባል፡፡ ዘመድ ከዘመድ ይጠያየቃል፡፡ ይህም ባሕልን ከመጠበቅ እና ከማስቀጠል አኳያ የጥምቀት በዓል የጎላ ድርሻ አለው፡፡

ከዚህ በዘለለ ጥምቀት ደማቅ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ገጽታዎች አሉት፡፡ ጥምቀት ለሰላም እና ለዕርቅ፣ ለሀገር የመልካም ገጽታ ግንባታ፣ ለአንድነት እና ለመከባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

የበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓቱ የዓለምን ሕዝብ ትኩረት በመሳቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ለማሕበራዊ ትስስር ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን በጎንደር ከተማ የቀሃ ኢየሱስ ወፋሲለደስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቆሞስ አባ ገብረ መድህን  ገልፀዋል፡፡ “በዓሉ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ያሉ ምዕመናን ተገናኝተው በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ የሕዝብን መቀራረብ በማጠናከር ለማህበራዊ ትስስር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንዲሆን አስችሎታል” ብለዋል።

እንደ እምነቱ ሊቃውንት የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ከባሕላዊ ወግ እና ሥርዓት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ህብረ ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባሕሩ የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት እና በትዳር ለመተሳሳር ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን በዓል ዘር እና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ሕዝብን ያቀራርባል፤ የመረዳዳት ባሕልንም ያሳድጋል፡፡

በአጠቃላይ በሃይማታዊ አስተምሮው ማቴ 11፡2 ላይ እንደሰፈረው “ኢየሱስ ክርስቶስ  የትሕትናው ነገር እጅግ ድንቅ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪ ሲሆን ራሱ በፈጠረው ፍጡር በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፤ አንዳች ኃጢአት ሳይኖርበት ለሰው ልጅ ሲል ጽድቅን ለመፈፀም ተጠምቀ፡፡ ሰማያዊው ንጉሥ በምድራዊው ሰው ተጠመቀ፡፡ እሳትነት ያለው መለኮትን ያለመለየት የተዋሐደ ሥጋ  ፍፁም ሰው ሆኖ ተጠመቀ፡፡ በእሳት እና በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው እርሱ በውኃ ተጠመቀ፡፡ ፍጡራን በስሙ የሚጠመቁት እርሱ በፍጡር እጅ ተጠመቀ፡፡ ፈጣሪ የሆነው ራሱ በፈጠረው ውኃ ተጠመቀ፡፡ ኃጢአት የሌለበት እና የሰውን ልጅ ኃጢአት የሚያስወግድ እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከኃጢያተኞች ጋር አብሮ ተጠመቀ፡፡ ይህንን ሁሉ ያደረገው ትሕትናን ለማስተማር ነው፡፡ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና” በማለት ነው የትሕትናን እና የፍቅርን አምላካዊ ስጦታነት የሚያስገነዝበው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል  በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው  ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት  ጥምቀት ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ኅብረ ብሔራዊ በዓል መሆኑን አንስተዋል፡፡

በማከልም “ጥምቀት ባሕላዊ በዓላችን ነው። የኢትዮጵያ የመስክ ላይ ትዕይንት ማቅረቢያ በዓል ነው። መስኩና ወንዙ ይታይበታል። ልብሳችንን እና የወግ ዕቃዎቻችንን ለዓለም እናሳያለን። የፀጉር አሠራራችንን እና ዜማዎቻችንን እናቀርባለን። ጥምቀት የኢትዮጵያ ባሕል የአደባባይ መዘክር ነው። ጥምቀት ኅብረ ብሔራዊ በዓልም ነው። የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች ለማየት የፈለገ ሰው አንዱ አማራጩ የጥምቀት አደባባይ ነው። በአንድ አደባባይ ሺህ ዓይነቱን ኀብረ ብሔራዊ ማንነታችንን ማየት ይቻላል። የክት የተባለው የባሕል ልብሳችን ይወጣል፤ ታይተው የማያውቁ ጌጣ ጌጦች ብቅ ይላሉ፤ በጥምቀት የኢትዮጵያን መልከ ብዙ ገጽታ ማየት ይቻላል” ነው ያሉት።

“እነዚህን የመሰሉ ዕሴቶቻችንን ስላስረከቡን ቀደምቶቻችንን እናመሰግናቸዋለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ጥምቀት ከተማን ከገጠር ከማገናኘት ባሻገር የውጪውንም ከሀገር ቤት ያስተሣሥራል ብለዋል። ይህም ኅብረ ብሔራዊ ትሥሥራችንን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። የጥምቀትን አስተምህሮ ለሀገር ግንባታ በመጠቀም፤ ባሕላዊ እሴቱን በማጎልበት እና ኅብረ ብሔራዊነቱን በማጠናከር በዓሉን እንድናከብር” በማለት ነው የጥምቀትን ማሕበራዊ ፋይዳ በማንሳት ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ደግሞ “ኢትዮጵያዊያን ከመለያየት ይልቅ የፈጣሪ ክቡር ሥራ ለሆነው የሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት ትኩረት አንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ በዓሉ የአንድነት፣ የአብሮነትና የደህንነት ተምሳሌት መሆኑን በመግለጽ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት በጋራ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here