ላውድ አንቶኒ ባሲንግ ሳይንቲስት፣ መሐንዲስ እና ሥራ ፈጣሪ ነው። ጋና ተወልዶ ያደገው አፍሪካዊው ላውድ በሜዲካል ምርመራ /ዲያግኖስቲክስ/ የሥራ ክፍል /ዲፓርትመንት /፣ ኩዋሜ ንክሩማህ የተሰኘው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኩማሲ ጋና እና ኢንካስ ዲያግኖስቲክስ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ነው፡፡
ላውድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ዶክትሬቱን በክሊኒካል ማይክሮ ባዮሎጂ ይዟል:: በባዮ ሜዲካል ኢንጅነሪንግ፣ በሜዲካል ላብራቶሪ እና በክሊኒካል ማይክሮ ባዮሎጂ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪውን ተመርቋል:: በጋና ውስጥ የሕክምና መሳሪያ (የባዮቴክ ኩባንያ) መሥራቹ ላውድ፤ በተለይም ለአፍሪካ ገበያ የመመርመሪያ መሳሪያዎቹን ፈተና መቋቋም የሚያስችል ማምረቻ ደርጅት የመሠረተ መምህር ነው።
በጤናው ዘርፍ (በሜዲካል ዲያግኖስቲክስ) ትምህርት ክፍል ፣ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፣ በክኑስት እና የኢንካ መመርመሪያ መሳሪያዎች መስራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና መምህር በመሆን እያገለገለ ነው። ላውድ አንቶኒ ከተማሪነቱ ጀምሮ በጤናና በሌሎች ዘርፎች ምርምር ለማድረግ ከፍተኛ ፍቅር ነበረው::ፍላጎቱን ለማሳካትም ያጠናቸውን የማይክሮባዮሎጂ እና የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፎች መሠረት አድርጎ በአፍሪካ ውስጥ ባሉ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ለሚደርሱ ተላላፊ በሽታዎች ቀላል መመርመሪያ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ላይ ትኩረቱን አደረገ።
በአፍሪካ በተለይም በሀገር ውስጥ ምርቶች መመርመሪያ መሳሪያዎችን መሥራቱ ለምርምር ተግባሩ ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። ላውድ እስካሁን ባደረገው ምርምር 13 የሰው ጤና እና ሦስት የግብርና መመርመሪያ(ዲያግኖስቲክስን) እንዲም ሦስት ሞለኪውላዊ የነጥብ እንክብካቤ /ኬሚካላዊ/ ምርቶችን አዘጋጅቶ ለገበያ አቅርቧል።
ላውድ የዓለም ጤና ድርጅትን /ተመድ/ ጨምሮ ለበርካታ የሥራ ቡድኖች አባል በመሆኑ በተለይም በሽታን በመመርመር /ዲያግኖስቲክስ/ የአፍሪካን የመመርመሪያ መሳሪያ ችግር አስወግዶ ራስን ለመቻል የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ምርምር /ግሎባል ዲያግኖስቲክስ/ ሲምፖዚየም በህንድ ጂ20/G20/ ግሎባል ዲያግኖስቲክስ መሪዎች ስብሰባ እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት በሩዋንዳ ለአፍሪካ የኤች አይ ቪ መመርመሪያ አምራቾች ወርክሾፕ በመሳሰሉት ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የምርምር ሥራውን አቅርቧል።
በሀገሩ እንዲሁም በአፍሪካ የሕክምና ላብራቶሪ ሳይንስ ፕሮግራሞችን እውቅና በመስጠት ለባለሙያዎች በምርመራ /በዲያግኖስቲክስ/ እንዲሰለጥኑ በማድረግም ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
ከዓለም አቀፍ ትብብር በመፈለግ ለበርካታ ዓመታት የምርምር ልምድ ያካበተው ላውድ፤ እ.አ.አ ከ2009 እስከ 2013 ከሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ ከ13 ሀገራት ከተውጣጡ ተመራማሪዎች ጋር የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ከሌሎች ጋር ፕሮጀክት ላይ ሠርቷል።
እ.አ.አ. ከ2015 እስከ 2016 ደግሞ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በጋና እና በፓፑዋ ኒው ጊኒ እንዲሁም ከዌልደን ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤት ፑርዱ ዩኒቨርሲቲ ጋር በዩናይትድ ስቴትስ አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን በሞባይል በመታገዝ የኤች አይ ቪ መመርመሪያዎችን ሠርቷል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ተመራማሪው በጋና፣ በአይቮሪኮስት እና በካሜሩን ያለውን ፈጣን ምርመራ ለመገምገም በአውሮፓ እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በክሊኒካል ሙከራዎች በአጋርነት (EDCTP) በገንዘብ የተደገፈ ፕሮግራም ይመራል። በናይጄሪያ፣ ማሊ፣ ስፔን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ ኬፕቨርዴ፣ ኬንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎቹን በማስታወቂያ ሰሌዳዎች እና በገጽ ለገጽ ግንዛቤ ፈጥሯል፡፡
ላውድ የ2016 ማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎው በቢዝነስ እና ሥራ ፈጠራ መሥመር ውስጥ የሚገኝ እና ቀደም ሲል የምእራብ እና የመካከለኛው አፍሪካ ክልላዊ አማካሪ ቦርድ የግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።
ላውድ ባሁኑ ወቅት በአሜሪካ ማይክሮባዮሎጂ ማህበር (ኤኤስኤም) የወጣት መሪዎች ክበብ አባል እና በጋና ወጣት አምባሳደር ነው። እሱ የዓለም አቀፍ የኩማሲ ማዕከል /ሃብ /ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የውይይት፣ ድርጊት እና ለውጥ አራማጅ እንደሆነ መረጃዎች አመላክተዋል:: የወጣቶች ዓለም አቀፍ መረብ እና የወጣት አፍሪካዊያን መሪዎች ኔትወርክ ጋና የቀድሞ ፕሬዝዳንትም የነበረው ላውድ እርሱም ሆነ ሀገሩ የወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አባል እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ላውድ አንቶኒ የአፍሪካን የፈጠራ ሥነ-ምህዳር ለማጠናከር ያለመ እና ለአፍሪካ ፈጠራ ሽልማት የታጨ የመጀመሪያው ጋናዊ ነው። እ.አ.አ. በ 2017 ከ50 ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጋናውያን እና በ2017 ከ40 ዓመት በታች ካሉ ታዳጊ መሪዎች በጋና በጤና እና ደህንነት ምድብ አሸናፊ ሆኗል።
ላውድ በ2018 በርተን ሞርጋን የንግድ ሞዴል ውድድር በፑርዱ ዩኒቨርስቲ በማህበራዊ ፈጠራ መስመር/ትራክ/ ውስጥ አንደኛ እና በ2017 ሽሩዝ ፈጠራ ውድድር ላይ በሽንት ላይ ተመስርቶ በጾታዊ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች መመርመሪያ ኪት በማዘጋጀት በሁለተኛነት አሸንፏል።
እ.አ.አ. በማርች 2019 ላውድ በሞለኪውላር /ኬሚካል/ ላይ የተመሠረተ ፈጣን የሙከራ ኪት በማዘጋጀት ችላ ለተባሉት የሐሩር ክልል (በርሃማ ቦታ) በሽታዎች በ2019 በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ፈጠራ ፈተና ውስጥ ካሉ ምርጥ 30 ፈጣሪዎች አንዱ ሆኖ ተመርጧል። እ.አ.አ. በማርች 2020 ላውድ ከጋና፣ ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ የተውጣጣ ቡድንን በመምራት የዓለም ጤና ድርጅት በኮቪድ19 መፈተሻ እና መከታተያ መድረክ አሸንፏል። እ.አ.አ. በየካቲት 2020 ላውድ ከኢንካ ዲያግኖስቲክስ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድንን በመምራት ከክኑስት ጋር በመተባበር ለኮቪድ19 ፈጣን መመርመሪያ ኪት ለማዘጋጀት እና በግንቦት 2020 የአፍሪካ ዶት ኮምን በኮቪድ-19 ላይ የፈጠነ አፍሪካዊ ፈጠራዎችን አሸንፏል።
በሀምሌ 2020 በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ግብ መሳካት ባደረገው ጥረት በታህሳስ 2020እ.አ.አ ከ50 ተፅእኖ ፈጣሪ ጋናውያን ወጣቶች እንዲሁም በግንቦት 2021 በጋና ውስጥ ካሉ 50 ምርጥ ወጣት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች አንዱ ሆኖ ተመርጧል።
የመረጃ ምንጮቻችን ስኮላር ጅፒኤስ፣ አፍሪካ ዲቭሎፕመንት ፣ ኮንቲንየስ ኤዱኬሽን ሰርቪስ እና ዌብ አብ ክዌስት ናቸው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም