ሆሊውድ – የአሜሪካ ለዘብተኛ ኀይል

0
253

“እኛ ሁላችንም ሚዲያ የምንጠቀም ሰዎች የማሕበረሰብ ቀያሾች ነን።ማሕበረሰብን የከፍታ ማማ ላይ ልንሰቅለው  ወይም መቀመቅ ልናወርደው እንችላለን” በማለት ዊሊያም በርናባክ የተናገረው ሐሳብ የሚታይ፣   የሚሰማ፣ የሚደመጥ  እና የሚነበብ መረጃ የሰውን አዕምሮ እንዴት እንደሚቀይሩት የሚያሳይ ነው።

ሲኒማ ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል የዓለምን መልክ እና አስተውሎት ይቀይረዋል። ስሜታችንን፣ ሐሳባችንን፣ ድርጊታችንንም ጭምር የሚቀይር ተወዳጅ የተግባቦት ዘርፍ ነው። ይህንን መሣሪያ ለዓመታት የተጠቀመችው አሜሪካ በሆሊውድ በኩል በልስላሴ ገብታ ማድረግ የምትፈልገውን ፈጽማለች የሚሉ በርካቶች አሉ። በቀጥታ ጦርነት በመግጠም፣ በውክልና ጦርነት፣ አድራጊ ፈጣሪነት፣ የዓለም የበላይ የመሆን ፍላጎት ያላት አሜሪካ ፊልም ደግሞ ሌላው ለዘብተኛ ኀይሏ ነው።

ከጦርነት በላይ አሜሪካ በፊልሞቿ  ያሰበችውን እና ማድረግ የምትችለውን ቀድማ በማሳየት እኔ እበልጣለሁ ብላ ቀድማ አሸናፊ ሆናለች።አሜሪካ የተስማማችበት ቅዱስ፣ እሷ ያልደገፈችው ደግሞ እርኩስ ሆኖ ለዓመታት ቀጥሏል።

ባህል፣ አመለካከት፣ ፕሮፖጋንዳ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ መልካም ገጽታ ግንባታ በአሜሪካው ፊልም ኢንዱስትሪ በኩል የተሰራጩ ሐሳቦች ናቸው።

በባህል ተጽእኖ ዘርፍ  ፊልሞች በአለባበስ፣ አኗኗር፣ አመጋገብ፣ እሳቤ እና እሴት በኩል ቀሪው ዓለም በሆሊውድ በኩል አሜሪካን እንዲያስብ አድርገዋል። በአስተሳሰብ ረገድ  በርካታ የሆሊውድ ፊልሞች የሐሳብ ነጻነት እና ዲሞክራሲን በማስተጋባት የአሜሪካን ሕልም ለማሳየት ቀርበዋል።በዚህም ሀገሪቱ ለሰው ልጆች ቀናኢ መስላ በአዎንታዊ መልኩ እንድትታይ ተደርጓል። የነጻነት እና ዲሞክራሲ ምንጭ እኔ ነኝ ብላ ከዜናዎቿ እና ድርጊቶች ባሻገር  በፊልሞቿ ለዓለም ተናግራለች። ጦርነትና ውጥረት በሚከሰትባት ጊዜ አሜሪካ ሆሊውድን በመጠቀም አጀንዳዋን ታሳያለች፤ጠላቷን ጥላሸት ትቀባለች ወይም  ስለ ግጭት አላስፈላጊነት ታወራለች። እ.ኤ.አ 2019 የአሜሪካው ሆሊውድ 42 ቢሊየን ዶላር ገቢ አስገኝቷል። ይህም የሀገሪቱን ጠቅላላ ሀገራዊ እድገት 3.2 በመቶ ድርሻ ይይዛል። የመዝናኛው ዘርፍ  ቁንጮ ሆሊውድ የሚያስገኘው ገቢም ቀላል አይደለም። የሆሊውድ ከዋክብት እና ፊልም ሰሪዎች የአሜሪካ አምባሳደሮች ናቸው። በባህል ልውውጥ፣  በፊልም ፌስቲቫል እና በሌሎችም የሀገሪቱን እሴት እና ባህል ያስተዋውቃሉ። ፊልም ለዝብተኛ ኀይል ሆኖ የሕዝብን ማንነት ለሌላው ዓለም ለማሳወቅ ጥቅም ላይ ይውላል። የአሜሪካ መንግሥት ሆሊውድን  እና ግለሰቦችን ተጠቅሞ ገጽታውን በመልካም ይገነባል። በ1914  በሎስ አንጀለስ ከተማ ምስረታውን ያደረገው ሆሊውድ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ዲፕሎማሲያዊ  ተጽዕኖውን ሲያሳርፍ ቀጥሏል። ለዛሬው የሀገሪቱ መልክ እና ቁመና ከመቶ ዓመታት በላይ የተሻገረው ግዙፉ የፊልም ኢንዱስትሪ አሻራው ትልቅ ነው።

ሆሊውድ በዓመት እስከ 500 የሚጠጉ ፊልሞችን በመሥራት ለተመልካች ያደርሳል።  ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ሲታይም የአሜሪካ ፊልም ኢንዱስትሪ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ሰዎችን በዓመት  ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። አንድሪው አሊ “ሆሊውድ  የአሜሪካ ምስል እና ዓለም አቀፍ የፊልም ኢንዱስትሪ” በሚል ባሰናዳው ጽሑፍ “በአፍሪካ በተለይም በእኔዋ ናይጀሪያ በጎዳናዎች የሚጓዝ ሰው  የህንድ ወይም የቻይና አይደለም የአሜሪካ ፊልሞችን ማስታወቂያ በስፋት ያያል” በማለት ለናይጀሪያዊያን የአሜሪካ ፊልሞች  የፊልም ደረጃ ልኮች ሆነው መወሰዳቸውን ጽፏል።

የዓለም ስርዓትን የገነቡት አውሮፓዊያን እና አሜሪካዊያን በባህላቸው መሠረት የሰዎችን ዕይታ ለውጠውታል ይላል። የፊልም ሠሪነት እና ደረጃን በሆሊውድ መለካት በአፍሪካ ብቻ የተለመደ እሳቤ እንዳልሆነ አንድሪው ያሳያል።  የፊልም ሠራዎች የሆሊውድን መስፈርት እና አጀንዳ ቀረጻ ዓርዓያ አድርገው ወስደውታልም ብላል።

የሌሎች ሀገራት ምርጥ ፊልሞች የሆሊውድን መንገድ ተከትለው የሚሠሩ መሆናቸውን በዚህም የሆሊውድ ድጋሚ (ኮፒ) መሆናቸውን አንድሪው ጽፋል።

ስለ አሜሪካ ሲናገርም “የሆሊውድ ሰዎች ፊልም በመሥራት እና በመሸጥ ምርጦች ናቸው። የሆሊውድ ስኬትም የተወሰነው ፊልሞችን ለሁሉም ተመልካቾች ስለሚሠሩ አይደለም። ይልቁንስ ፊልሙ ለእናንተ እንደተሠራ ማሳመን በመቻላቸው ነው”  በማለት አንድሪው ይናገራል።

ሆሊውድ አሜሪካን የተስፋ ምድር፣ የዲሞክራሲ ማዕከል እና ጠበቃ፣ የነጻነትን ጥቅም የምትደግፍ አድርጎ ያቀርባታል።

ለዘብተኛ ኀይል (ሶፍት ፖዎር) በማይዳሰሱ በባህል፣ በእሳቤ፣ በአመጋገብ፣ አለባበስ፣ በተቋማት በኩል ፊልምን በመጠቀም ፍላጎትን ማሳኪያ መንገድ ነው። የሰውን ልቦና በቧልት፣ በሳቅ፣ በደስታ፣ በኀዘን፣ በማስገረም ገዝቶ ሐሳብ እና ስሜትን እንዲሁም ድርጊትን የመቆጣጠር ስልት ነው።

ሆሊውድ  ዴስኒ፣ ፓራማውንት ምስሎች፣ ዋርነር ብሮስ፣ ዩኒቨርሳል ምስሎች እና ሌሎች መሠል የቀረጻ ስቱዲዮዎች አሉት። ሆሊውድ ከ 100 በላይ በተሻገረው ዕድሜው የቧልት፣ ድራማ፣ የድርጊት፣ ሙዚቃዊ፣ የፍቅር፣ የአስፈሪ፣ የሳይንስ ፈጠራ እና የጦርነት ፊልም ዘውጎችን በመሥራት ቀጥሏል።

ሆሊውድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ፊልሞችን በመሥራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተመልካች ማግኘት ችሏል። በዘመናት ጉዞው ሆሊውድ ጠንቀቅ ያሉ ሙያተኞች ያሉበት የፊልም ኢንዱስትሪ ሆኗል። አንድን ርዕሰ ጉዳይ አድምቶ ይሠራል፤ስብጥር (በዘውግ፣በሴራ፣ በታሪክ፣ አለመሰልቸት)፤ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ምስለ ንድፍ (ግራፊክስን) በመጠቀም የቴክኖሎጅ ዕድገትንም ማሳየት ችሏል። አቬንጀርስ፣ ፕላኔት ኦፍ ዘኤፕስ፣ ግራቪቲ፣ ጀርሲክ ፓርክ፣ አቫተር ፊልሞች በቴክኖሎጂ ተጠቃሽ  ረቂቅ ሆነው ከተሰሩት መካከል ይጠቀሳሉ።

ቴህራን ታይምስ አሜሪካ የመከላከያ ኃይሏን ፔንታገንን፣ የደህንነት ተቋሟን ሲአይ ኤን እና የፊልም ተቋሟን ሆሊውድን በማቀናጀት ዓለም አቀፍ ገጽታዋን ለመገንባት ተጠቅማባቸዋለች ይላል። ሁለቱ ተቋማት ሆሊውድን በመጠቀም በጦርነት አቅም ጠንካራ መሆናቸውን ለማሳየት እንደሚሰሩበት  ቴህራን ታይምስ ይጠቅሳል። ሲአይኤ እና ፔንታገን ሆሊውድን 2500 ፊልሞችን በፈለጉት መልኩ እንዲሠራ አስገድደውታል። አንዳንድ ፊልሞች ፔንታገን  ሐሳቦቹን ተቀብሎ ባለማጽደቁ መንግሥት ለመሥሪያ የሚሆን ገንዘብ ሳይፈቅድላቸው ቀርቷል።

ፓራማውንት የሚባለው የሆሊውድ ስቱዲዮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው “ ቶፕ  ገን” የተሰኘው ፊልም አሜሪካ በቬትናም ላይ በወሰደችው የጦር ርምጃ ወቅት ነበር የተለቀቀው። አሜሪካ በዚህ ጦርነት ሽንፈት ገጥሟት ነበር። የአሜሪካ ሕዝብ በዚህ ተቆጥቶ ነበር። በወቅቱ የነበረውን የሕዝብ ቁጣ ለማርገብ  እናም ብዙ ወታደር ወደ ሠራዊት እንዲገባ አሜሪካ  በዚህ ፊልም ታበረታታ ነበር። ፊልሙም  ሕዝቡ ተሸናፊነትን እንዳይቀበል የሚያደርግ ነበር።

ሆሊውድ ከ1910- 1920 ባሉት ዓመታት የሚያዘጋጃቸው ፊልሞች ለደሀዎች እና ለስደተኞች የሚሰሩ ነበሩ። በ1917 የተሠራው ኢሚግራንትስ ከአውሮፓና ሌሎች ሀገራት የተሰበሰቡ ስደተኞችን በማሰባሰብ የሀገር ግንባታ ላይ ያተኮረ ነበር።

የሀገር ፍቅር ስሜት፣ የሃይማኖት፣ የቤተሰብ እሴትን እና  ታታሪነትን የሚያሳዩ ነበሩ። አሜሪካ ከተለያዩ የባህል እና እምነት የተሰበሰቡ ሰዎችን ወደ አንድ በማምጣት ሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጠንከር ሆሊውድን ትጠቀም ነበር። በሒደትም በ1964 የተለያዬ የቆዳ ቀለም ያላቸው ተዋንያንን ማካተት የጀመረበት ሆነ። ይህም የአሜሪካን የሲቪል መብት ጽንሰ ሐሳብ ለዓለም ያስተዋወቀ ነበር።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ መንግሥት  የብሔራዊ ደህንነት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ፊልሞችን በገንዘብ  መደገፍ ጀምሯል። ፊልሞቹ የናዚን ሐሳብ የሚሞገቱ፣ የኮምዩኒስት ሐሳብን የሚያወግዙ፣ የሰዎችን የዜግነት ስሜት ከፍ የሚያደርጉ እንዲሆኑ ተደርጓል። በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት (ፔንታገን) እና በሆሊውድ መካከል የማይበጠስ ጠንካራ አንድነት ተመሥርቷል። የአሜሪካን ጦር የሚያጀግኑ፣ ፕሮፖጋንዳ የሚያስተጋቡ ብዙ ፊልሞች ተሠርተዋል።

የአሜሪካ ጦር ሰው እና መሣሪያ ለፊልም ሥራ ተግባራት ለሆሊውድ  ያውስ ነበር። ፊልሞች አሜሪካ በታሪክ ውስጥ ያላትን ውክልና ከፍ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀትን ተጉዘዋል። ራምቦ ቁጥር 2 የቬትናምን ጦርነት በሚመለከት፣ ራምቦ ቁጥር 3 ደግሞ የአፍጋኒስታንን ጦርነት የሚመለከቱ ሆነው ቀርበዋል።

ብዙ ፊልሞች የአሜሪካ ጦር በግጭት ወቅት ያለውን አቅም ለማጉላት ቀርበዋል። አሜሪካን ስናይፐር በ2015 ሲለቀቅ በኢራቅ የተሳተፈን የአሜሪካ ወታደር ታሪክ ያሳያል።በፊልሞች ውስጥ ያሉ ገጸ ባህርያት አሜሪካ ለማንም የማትንበረከክ ጉልበታም ሀገር መሆኗን በሚያሳይ መልኩ ተቀርጸዋል።

አሜሪካ በየጊዜው የፊልሞቹ መዳረሻ ገበያ በማስፋት የቀጠለች ሀገር ናት።እ.ኤ.አ በ1979፤ 75  ሀገራት ውስጥ ፊልሞች ይሠራጩ ነበር። በ2000ዎች ደግሞ 150 ሀገራት ውስጥ ተደራሽ ሆነዋል።

ደይሌ ኦብዘርቨር አሜሪካ ሆሊውድን የፖለቲካዊ እሴቶቿ፣ ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት በማስተጋባት የውጪ ግንኙነት ሥራዋን ለመሥራት ትጠቀምበታለች ይላል። ፔራል ሃርበር እና ዘፒያኒስት ፊልሞችን የሚመለከት ሰው አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገለልተኛ ነበረች ብሎ እንዲረዳ ይገደዳል የሚለው ዴይሊ አብዘርቨር ጃፓን እና ጀርመን ለሌሎች ሀገራት ስጋቶች ነበሩ ብሎ ጥላቻን ያዳብራል ይላል። በቀዝቃዛው ጦርነት የሶብየት ዩኒየንን ሶሻሊስታዊ ርዕዮት በማውገዝ በኩል የሆሊውድ ድርሻ ትልቅ ነበር።

ዘ አይረን ካርቴን እና ማይፋቮሬት ስፓይ የተሰኙ ፊልሞች ለዚህ ተግባራቸው ይጠቀሳሉ። ራምቦ የሚለውን ፊልም ወንዳ ወንድነትን በማጉላት ሰዎችን በተፅእኖ ስር የጣለ ነበር የሚሉ አሉ። ወንድነት ይበልጥ መጉላቱ ደግሞ የሴትነትን ሚዛን ያጎድለዋል ተብሎ ይታመናል።

ዘ ፓትሪዮት የሚለው ፊልም የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያሳይ፣ ሴቪንግ ፕራይቬት ራይን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በሚመለከት፣ ኦፕሪሽን ራጅ እና ቲርስ ኦፍ ዘሰን  አሜሪካ የዓለም አዳኝ እና የስደተኞች ደሴት መሆኗን ለማሳየት የተሠሩ ናቸው ።

አሜሪካ የአረብ፣ የቻይና፣ የሰሜን ኮርያ እና የሩሲያን ገጽታዎች ለማጉደፍ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲዋን በፊልም ለመደገፍ ሠርታለች።

አረቦችን በፊልሞች ውስጥ አሸባሪ እና አክራሪ በማድረግ በብዙ ፊልሞች አቅርባለች።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here