ለሁለንተናዊ ዕድገት 30 ዓመታት በትጋት…

0
36

ጋዜጣ ስለሁሉም ጉዳይ ጠቅላላ ዕውቀት ያለው እና አሰላሳይ የሆነ እና ነገሮችን በብዙ አቅጣጫ የሚያይ ትውልድ እንዲፈጠር፣ የጽሕፈት እና የቋንቋ ክህሎት እንዲዳብር፣ ከዚያ አለፍ ሲልም ለአደባባይ ንግግር ክህሎት መዳበር ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡

በማሳወቅ፤ በማዝናናት  በማስተማር እንዲሁም የማህበረሰብ ንቃተ ህሊናን በማጎልበት ጠያቂ ትውልድ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድም ሁነኛ ሚና አለው፡፡ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና የዲሞክራሲ ግንባታን በማጠናከር ሀገር መልክ እንዲኖራትም ሁነኛ ሚና ይጫዎታል፡፡

በተለይም አሁን ባለንበት የዲጅታል ዘመን  ጋዜጣ የራሱ ታላሚ አንባቢ እና ፈላጊ ያለው ዘመን አይሽሬ ታማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆን እንደማጣቀሻነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ብዙዎች ከማህበራዊ ትስስር ገጽ ይልቅ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ያዩትን መረጃ ይበልጥ ማስታወስ መቻላቸው፤ ከማህበራዊ ትስስር ገጽ ይልቅ ጋዜጣ ላይ ያዩትን ይበልጥ ማመናቸው፤ ጋዜጣን ዘመን ቢቀያየር ተመራጭ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ጋዜጣ ሰው ተረጋግቶ እንዲያነብ እና ጥልቅ ዕውቀት እንዲያገኝ ዕድል የሰጠ በመሆኑ ሰዎች በስክነቱ ይወዱታል፡፡

በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ጋዜጣን በሕትመት እና በማህበራዊ ሚዲያ አጣምሮ መስራት አዋጭ ቢሆንም ሕትመት  በባህሪው ከሰዎች አምስቱ የስሜት ሕዋሳት ጋር በቀጥታ የተገናኘ፣ ከማየት እና ከመዳሰስ ባለፈ ጋዜጣ ከሕትመቱ ቀለም እንዲሁም ከወረቀቱ ሽታ፤ ገጹን ባገላበጥን ቁጥር ካለው ንክኪ እና ድምጽ ጋር ከሰዎች ትዝታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ትስስር አለው፡፡

ታህሣሥ 7 ቀን 1987 በመደበኛነት  መታተም  የጀመረችው በኩር ጋዜጣም  ከዚህ አንጻር የተጫዎተችው ሚና  በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለአማራ ክልል ሁለንተናዊ ዕድገት እና ሥልጣኔ መፋጠን የማይተካ አስተዋጽኦ አበርክታለች:: ከምሥረታዋ ጀምሮ ሙስናን፣ ብልሹ አሠራርን  እየተከታተለች በድፍረት በማጋለጥ  ሁሉም በላቡ በወዙ ጥሮ ግሮ እንዲያድር፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ግልጽነት እንዲሁም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ስትሞግት ኖራለች:: ምርትን እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በአርሶ አደሩ ዘንድ ለማስረጽ ረድታለች፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሕዝቡን መረጃ የማግኜት ፍላጎት በመረዳት በበኵር ጋዜጣ ይደርስ ከነበረው መረጃ በተጨማሪ አማራጮችን ለማስፋት፣ የክልሉን ገጽታም በሚፈለገው ልክ ለማስተዋወቅ   ግንቦት 16 ቀን 1989 ዓ.ም “የአማራ ብሔራዊ ክልል ድምጽ” በሚል የስርጭቱ ማብሰሪያ፤ ሚያዝያ 1992 ዓ.ም ደግሞ የ30 ደቂቃ የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀምሯል፡፡

“የሺህ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል” እንዲሉ ቻይናውያን በበኲር ጋዜጣ የዛሬ  30 ዓመታት መሠረቱ የተጣለለት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም  በ30 ዓመታት ጉዞው ስለሕዝብ ማንነት፣ ገጽታ እና እሴት ግንባታ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮነት እና ተደጋግፈፎ ማደግ፣ ስለ ሃይማኖት እና ታሪክ የሚያወሱ፣ ግንዛቤን የሚያዳብሩ፣ ፋይዳ ያላቸው ዘገባዎችን በትኩረት ሠርቷል፡፡ በተለይም ችግሮች ሲፈጠሩ የመፍትሔ አካል በመሆን እና መፍትሔ አመላካች ዘገባዎችን በመሥራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ የመደማመጥ፣ የውይይት እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም እና ሀገር በቀል ዕውቀትን እንደችግር መፍቻነት ደጋግሞ በመስራት ለእሴቶች መጠበቅ ሚናውን ተጫውቷል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን   በይዘት ተመራጭ፣ በተደራሽነት አድማሱም ከዛሬው በላይ የሰፋ፣ በቴክኖሎጂም ተወዳዳሪ እና የላቀ የብዙኃን መገናኛ ተቋም መሆንን አልሞ ወደ ላቀ ከፍታ  የሚያሻግር የአምስት ዓመታት ስልታዊ ዕቅድ ነድፎ እየሠራም ይገኛል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሕዝብ እና መንግሥት የጣሉበትን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ ለዕቅዱ ተግባራዊነት መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ጥራትንም ሆነ ተደራሽነት ለማረጋገጥ፣  ተዓማኒነቱን፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን… አስጠብቆ ለመቀጠል ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here