“ለህዳሴው ግድብ የተሰጠው ትኩረት ለጣና ሐይቅም ሊሰጥ ይገባል”

0
8

ትውልድ እና እድገታቸው ጎንደር ደንቢያ ወረዳ ቆላ ድባ ከተማ ነው:: እስከ 12ኛ ክፍል በቆላ ድባ ት/ቤት ተምረዋል:: ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን ከያዙ በኋላ በጅማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በጅማ መምህራን ኮሌጅ  ለ10 ዓመታት አስተምረዋል:: በጎንደሩ ፋሲለደስ ትምህርት ቤት እና በጎንደር መምህራን ኮሌጅም በመምህርነት ሠርተዋል:: በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ለ23 ዓመታት አስተምረዋል:: በጣና ሀይቅ ላይ በስፋት ምርምር አካሂደዋል:: የጣና ሀይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡- ዶ.ር አያሌው ወንዴ:: እምቦጭን ከጣና ሀይቅ ለማስወገድ በተደረጉ ጥረቶችና ተዛማጅ ጉዳዮች አነጋግረናቸዋል:: መልካም ንባብ!

 

የእምቦጭ አረም ምንድን ነው?

የእንቦጭ አረም በዓለም አቀፍ ደረጃ በውኃ ላይ ቁጥር አንድ ከተባሉት መጤ እና ተስፋፊ እንዲሁም አደገኛ ከሆኑ አረሞች ውስጥ አንዱ ነው:: ይህም የተባለበት ዋና ምክንያት የእድገት ፍጥነቱ ተወዳዳሪ የለውም:: ከሌሎች የውኃ ውስጥ ከሚያድጉ እጽዋት ተወዳዳሪ የለውም:: በሁለት ሳምት ውስጥ ራሱን እጥፍ ያደርጋል::

 

እንቦጭ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ገባ?

ዋና መነሻው ደቡብ አሜሪካ ነው:: ይሄ መጤ አረም ከአውሮፖ ውጪ በሁሉም የዓለም ክፍሎች ተሰራጭቶ ይገኛል:: የእምቦጭ አረም ወደ ኢትዮጵያ ገባ የሚባለው ከ40 እና 50 ዓመታት በፊት ነው:: የአረሙ አበባ ለዓይን ማራኪ በመሆኑ ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ የተጓዘው በሰዎች እንደሆነ ይነገርለታል:: የአበባውን ማራኪነት ፈልገው በኩሬዎች እና በግቢያቸዉ ዙሪያ አረሙን የተከሉ ሰዎችም ለአረሙ መስፋፋት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ:: የእምቦጭ አረም አበባ ማራኪ ከመሆኑ በተጨማሪ አረሙ ውኃን ለማጣራት እንደሚረዳም ይታመንበታል::

ለአረሙ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አንደኛው ምክንያት ነው የሚባለውም በአዲስ አበባ ‘አባ ሳሙኤል’ በሚባለው አካባቢ የሚገኘውን የውኃ ኩሬ ለማጣራት እምቦጭን ይጠቀሙ የነበረ መሆኑ ነው:: እ.አ.አ ከ1965 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የሚነገርለት የእምቦጭ አረም በጋምቤላ እና በቆቃ ግድብ ላይም በሰው ሠራሽ መንገድ መሰራጨቱ ይነገራል:: እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በጣና ሀይቅ ላይ ምንም ዓይነት መጤ አረም አልነበረም:: በ2003 በየስድስት ወሩ በሀይቁ ላይ በምናደርገው ቅኝት ግን አዲስ የአረም ዝርያ በመገጭ ወንዝ (ወደ ጣና ሀይቅ መግቢያ ላይ) ማግኘት ችለናል:: ይህንኑ አዲስ የአረም ዝርያ ምንነት ስናጣራም አሁን እምቦጭ እያልን የምንጠራዉ መጤ አረም ሆኖ አግኝተነዋል::

 

የእምቦጭ አረም በጣና ሀይቅ ላይ እንዴት ተከሰተ?

አረሙ ወደ ጣና ሀይቅ እንዴት እንደመጣ መላምቶች እንጂ ተጨባጭ መረጃ የለንም:: ከመላ ምቶቹ ውስጥ አንዱ የአረሙ ፍሬ በአዕዋፍ ተጓጉዞ እንደመጣ የሚነገረው ነው:: ሁለተኛው መላ ምት ደግሞ በግብፅ እና በሱዳን አረሙ ቀድሞ የተገኘ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ በግብፅ እና በሱዳን ለአገልግሎት የዋሉ ጀልባዎች እና መቅዘፊያዎቻቸው ወደ ጣና ሀይቅ መጥተው አረሙን አሰራጭተውታል የሚለው ነው:: የዓሳ ማስገሪያዎች እና በጎንደር ያሉ ፋብሪካዎች አረሙን ለውኃ ማጣሪያነት ተጠቅመው አረሙ ወደ ሀይቁ አፈትልኮ ገብቶ ይሆናል የሚሉ መላምቶችም ይሰነዘራሉ::

የእምቦጭ አረም መተላለፊያ መንገዶቹ በርካታ ናቸው:: አረሙን መጤ ያስባለውም ከተፈጠረበት ቦታ በተለያዩ መንገዶች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተጓጓዘ በሀይቆች እና ሌሎችም የውኃ አካላት ላይ ጉዳት በማስከተሉ ነው::

እምቦጭ በጣና ሀይቅ ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ምን ይመስላል?

እምቦጭ አሁን ላይ የጣና ሀይቅ ዳርቻዎችን ከ190 ኪሎ ሜትሮች በላይ ይዟል:: የሀይቁ ዳርቻዎች ደግሞ ለሀይቁ መተንፈሻ ሳንባው እንደማለት ናቸው:: ሀይቁ መተንፈሻውን ሲያጣ የሀይቁ ውኃ ‘ውኃ’ ከመሆን ያለፈ ጥቅም የለውም:: ይህም ማለት ብዝሀ ህይወትን ማስተናገድ አይቻለውም:: በጣና ሀይቅ ዳርቻዎች ላይ በርካታ ለከብት መኖነት የሚያገለግሉ እፅዋት ይበቅላሉ:: አካባቢው ውኃ ገብ በመሆኑም የተሻለ ምርት ይሰጣል:: የዓሳ ጫጩት የሚፈለፈለውም በሀይቁ ዳርቻ ላይ ነው:: የእምቦጭ አረም በሀይቁ ዳርቻ ላይ ተስፋፍቶ መረብ ሲሠራ ወደ ሀይቁ የፀሐይ ብርሃንም ሆነ ሌላ ነገር አይገባም:: ከአረሙ ስርም ህይወት ያለዉ ነገር መኖር አይችልም:: እንደ ደንገል እና ፊላ ያሉ ነባር እፅዋትን ምግብ በመሻማትም ከሀይቁ ላይ እንዲጠፉ ያደርጋቸዋል:: በአጠቃላይ አረሙ የሀይቁን ዳርቻዎች ያዛቸዉ ማለት የሀይቁን እና የሌሎች ብዝሀ ህይወቶችን እስትንፋስ ዘጋ እንደማለት ነው::በጣና ዙሪያ የሚገኙ 60 የዓሳ አስጋሪ ማህበራት አሉ:: ከነዚህ ማህበራት ውስጥ 30ው ማህበራት ዓሳ የማያሰግሩባቸዉ አካባቢዎች በአረሙ በመያዛቸዉ ዓሳ ማስገር አቁመዋል:: የዓሳ አስጋሪዎቹ ቤተሰቦችም የዚሁ ችግር ሰለባዎች ይሆናሉ:: አረሙ የክልሉን የቱሪዝም ሀብትም አውዳሚ ሆኗል:: የከብቶች መኖን አጥፍቷል:: በአጠቃላይ የእምቦጭ አረም ጎጂነት ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቸላል::

አረሙን ለማጥፋት የተሠሩ ሥራዎችን ቢገልፁልን?

እምቦጭን ክረምት በመጣ ቁጥር በዘመቻ መንቀሉ መፍትሄ አይሆንም:: ይህንንም በመገንዘብ የአምስት ዓመት እምቦጭን የማስወገጃ እቅድ ተይዟል:: እቅዳችን በመስከረም ላይ ያለው የአረም መጠን በዓመቱ መስከረም ላይ ሲለካ አንሶ መገኘት አለበት የሚል ነበር:: እስካሁን በሄድንበት አካሄድ የአረሙ መጠን መቀነስ፣ መጨመር፣ መውረድ እና መውጣትን የሚያሳይ ነው፤ በዚህ መልኩ ደግሞ መቀጠል አይቻልም:: አረሙ አሁንም ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ የጣናን የውኃ አካል ሸፍኗል:: በ2013 ዓ.ም 100 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ክልሎች ርብርብ በማድረግ በሀይቁ ላይ የሚታየውን አረም 95 ከመቶ ከሀይቁ ውስጥ ማስወጣት ተችሎ ነበር:: ከሀይቁ ላይ የታረመው 95 ከመቶ የሚሆን አረም ተጓጉዞ እና በእሳት ተቃጥሎ “ተወገደ” መባል ሳይችል ግን ብዙ እንቅፋቶች አጋጥመውናል::

 

በእምቦጭ ዙሪያ የተደረገው ድጋፍ ምን ይመስላል?

በ2013 ዓ.ም በሕዝብ ጩኽት እና ጉትጎታ በሚመስል መልኩ ክልሎች እና ፌዴራል መንግሥቱ የ100 ሚሊዮን ብር በጀት መድበው ጥሩ ሥራ መሥራት ተችሏል:: ሀገር አቀፍ የተፋሰሶች ምክር ቤትም ግድቡ ያለ ጣና የሚሆን አይደለም በማለት ጣና ሀይቅን ብሔራዊ አጀንዳ እናደርገዋለን ብሎ ተነስቶ ነበር:: በገንዘብ ሚኒስቴርም ጣና ራሱን የሚያለማበት በጀት ይመደብለታል የሚል መግባባት ላይም ተደርሶ ነበር:: ጩኸቱ ከፍተኛ ድጋፍ ይዞ የመጣ ቢመስልም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ድጋፉ አመርቂ አልነበረም:: እንቦጭን ለማስወገድ በማሽን ደረጃ ከሦስት አይበልጡም የተለገሱት፤ ገንዘቡም ቢሆን በቂ አልነበረም::

የመንግሥትም ሆነ የብዙኃን መገናኛዎች የጣና ትኩረት ያዝ ለቀቀ የሚል እና የወረት መሆን የለበትም:: የጣና ቤተሰብ መድረክ የተቋቋመው ለጣና ሀይቅ ሁሉም በቤተሰባዊ መንፈስ ለጣና ሀይቅ የድርሻውን እንዲወጣ በማሰብ ነው::

 

እምቦጭን ለማጥፋት ከሁሉም አካላት ምን ይጠበቃል?

የእምቦጭ አረምን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ወይም የጣና ሀይቅ ችግር እንዳይሆን ለማድረግ ብዙ ሀብት ማሰባሰብን ይጠይቃል:: የቅንጅት ሥራዎችንም ይፈልጋል:: ጣናን የሀገር ሀብት አድርጐ ማሰብን ይፈልጋል:: የባለሀብቶችን አና የመንግሥትን ትኩረት ይሻል:: የውኃ

ቴክኖሎጂን እና እውቀትን ይፈልጋል:: ስለ ጣና በሚዲያዎች መወራት ሲያቆም እምቦጭ የጠፋ የሚመስለውን እሳቤ ማስተካከል ይገባል:: በአጠቃላይ ጣናን በዘመቻ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን በቅንጅት እና በእቅድ ሥራዎች ነው ከህመሙ ማዳን የሚቻለው:: ለህዳሴው ግድብ የሚሰጠው ትኩረት ለጣና ሀይቅም ሊሰጥ ይገባል:: በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በክልል ፕሬዝደንቶች እና በከተማ ከንቲቦች የሚመሩ የኮሪደር ልማት ኢኒሸቲቮች እንዳሉ ሁሉ የጣና ኢኒሼቲቭ ሊኖር ይገባል::

እምቦጭን የጣና ብቻ ችግር ማድረጉን ካላቆምን ልናጠፋው አንችልም:: እምቦጭ አረም ከጣናም ሆነ ከአማራ አልፎ በተለያዩ ክልሎች እና የውኃ አካላት ላይ በመገኘት የሀገራችን ችግር እየሆነ ነው:: በተናጠል እና በር ዘግቶ የሚደረጉ ጥረቶች እንደ ሀገር ውጤታማ አያደርጉንም::እምቦጭን ከጣና ሀይቅ ላይ ለማስወገድ በተደረገው ጥረት እምቦጭ ሊገወገድ የሚችል አረም መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሆኗል:: ስለዚህ ተቀናጅቶ መሥራት ከተቻለ እምቦጭን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ማስወገድ ይቻላል::

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here