በአማራ ክልል አሥር ወራትን ባስቆጠረው ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ባልተመለሱበት ወቅት ከሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች እንደሚሰጡ ተገልጿል:: የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሁናዊ ዋነኛ ትኩረትም የፈተና ዝግጅት ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች የንቅናቄ መድረክ እያዘጋጀ ነው:: የማካካሻ ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ይዘቶች በወቅቱ እንዲሸፈኑ፣ የፈተና ጥያቄዎችን በማዘጋጀት የተማሪዎችን ዝግጁነት ማረጋገጥ እና በሥነ ልቦና ማብቃት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራም ቢሮው የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት አሳስቧል::
በክልሉ በተዋረድ የሚገኙ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት እና የየትምህርት ቤቶች መምህራን እና አመራሮች ተፈታኞቻቸው በወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ ክፉኛ ሳይረበሹ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን በቀደሙት ሕትመቶቻችን መዘገባችን ይታወሳል::
በእርግጥ በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም እጦት አሁንም ድረስ መቀጠሉ የተማሪዎችን ሥነ ልቦና ክፉኛ በመፈተን ውጤታማ ጥናት እንዳያደርጉ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል:: የጥይት ድምጽ በተደጋጋሚ መስማት፣ የመንገዶች መዘጋት፣ በተለያዩ ቦታዎች እየተስተዋሉ ያሉ ዝርፊያዎች እና እገታዎች አሁንም ተማሪዎች ትምህርታቸውን የማስቀጠል ፍላጎት የገቱ ሆነው ይነሳሉ::
የሥነ ልቦና ባለሙያው የሺዓምባው ወርቄ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እያጋጠሙ ያሉ እንደ ጦርነት የመሰሉ ማኅበራዊ አለመረጋጋቶች ሰዎች ለጭንቀት፣ ለድባቴ፣ ብዙዎች ለሕይወታቸው ልዩ ትርጉም እንዳይሰጡ ይልቁንም ለተስፋ ቢስነት ተገዥ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አስረድተዋል:: ይሁን እንጂ አንዳንድ ችግሮች እኛ የማንቆጣጠራቸው፣ ምናልባትም የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ የማናደርግባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: በመሆኑም ተማሪዎች የተነሱለትን ዓላማ ለማሳካት በቅድሚያ ሊያደርጉት የሚገባው ብቸኛው አማራጭ ከእነሱ የሚጠበነቀውን እና ለስኬት የሚያበቃቸውን ብቻ ከመከወን ውጪ ስለሌላ ነገር ሊያስቡ እንደማይገባ ባለሙያው መክረዋል::
እኛም ተማሪዎች በችግር ውስጥም ሆነው ያቀዱትን የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያግዟቸዋል ያልናቸውን የአጠናን ስልቶች ልናስነብባችሁ ወደናል:: ተማሪዎች ክልሉ ያጋጠመውን ቀውስ ተቋቁመው ትምህርታቸውን በአግባቡ ከማስቀጠል ባለፈ ዓመቱን በድል ለማጠናቀቅ ጠንካራ የፈተና ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል::
ቶፕ ዩኒቨርሲቲ፣ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ ተቋማት ድረ ገጾች ላይ ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከውጤታማ የአጠናን ስልቶች የመጀመሪያው በቂ እንቅልፍ ማግኘት ነው:: አንድ ሰው በአማካኝ በቀን እስከ ስምንት ሰዓት መተኛት እንዳበት የጤና ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ያሳያል:: በቂ እንቅልፍ አለማግኘት የማስታወስ ችሎታ ከመቀነስ ጀምሮ በሰዎች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ የከፋ አሉታዊ ጫና ይፈጥራል:: ከዚህ በተቃራኒ በቂ እንቅልፍ ማግኘት የትምህርት አቀባበልን ለማዳበር፣ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን እና አለፍ ሲልም ጤናማነትን በማረጋገጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ያግዛል::
እንደ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ተማሪዎች ቀናቸው መልካም ሆኖ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ከተፈለገ አመጋገብን ማስተካከልም ይገባል:: ጥሩ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል ሰውነት ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ እና ንቁ አዕምሮ እንዲኖር በማድረግ በቀን ውስጥ ሊከወን የታሰበውን ዕቅድ በወቅቱ ለመፈጸም ያስችላል:: በመሆኑም ተማሪዎች በተለይ ለመደበኛ ጥናትም ሆነ ለፈተና ለመዘጋጀት ሲያስቡ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ ሊመገቡ እንደሚገባ መረጃዎች አመላክተዋል:: የተለያዩ የጎመን አይነቶች፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ስፒናች፣ ቃሪያ፣ ብሮኮሊ፣ ብርቱካን እና ሌሎች ኮምጣጤ ፍራፍሬዎች፣ ዳቦ፣ አቮካዶ፣ እንቁላል፣ አሳ፣ ለውዝ እና ቡናማ ቸኮሌት ለአዕምሮ የተመቹ የምግብ አይነቶች መሆናቸውን ያስታወቀው ደግሞ ሄልዝላይን የጤና መረጃ ድረ ገጽ ነው::
በዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ በቀጣይነት ተግባራዊ መደረግ እና በሁሉም ተማሪዎች ዘንድ በልዩነት መታየት ያለበት ዕቅድ ማዘጋጀት ነው:: የትምህርት አይነቶችን በይዘት ክብደታቸው ልክ መለየት፣ በቀኑ የተማሩትን ለመከለስ የሚሆን እና ለእያንዳንዱ የትምህርት አይነት ተመጣጣኝ የጥናት ሰዓት መመደብ ተገቢ ነው::
የጥናት ጊዜን ሁሌም መጀመር ያለበት በጥዋት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ:: ጠዋት ላይ ጭንቅላታችን እረፍት አድርጎ በአዲስ መንፈስ ሁሉንም ነገር ስለሚጀምር በዚህ ሰዓት ማጥናት ውጤታማ እንደሚያደርግ ይታመናል::
ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በዋናነት ውጤታማ ያደርጋል ያላቸውን የአጠናን ስልቶች ጠቁሟል:: ለመረዳትም ሆነ ለማስታወስ የሚያግዘው የመጀመሪያው ውጤታማ የአጠናን ሥነ ዘዴ ቅኝት ማድረግ ነው:: ይህም አንድን የትምህርት አይነት ምዕራፍ ለማንበብ ከመጀመር በፊት አጠቃላይ ይዘቱን እና ርእሶቹን ማየትን ያጠቃልላል:: ቀጥሎ የሚመጣው ራስን ጥያቄ መጠየቅ ነው:: ይህ ማለት ስለሚጠናው ይዘት ምንነት እና በምዕራፉ ውስጥ ጠቃሚ ሊባል የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ ራስን መጠየቅ መልስ ለማግኘት ስለሚገፋፋ ውጤታማ ለመሆን ይረዳል::
ይህን ተከትሎ ወደ ማንበብ ወይም ማጥናት መግባት ይገባል:: በዚህ ወቅት ታዲያ የይዘቱ ዋነኛ ቃላትን እስከፍቻቸው ማስመር ወይም ማስታወሻ ደብተር ላይ ማስፈር በቀላሉ ለማስታወስ እንደሚረዳ ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ድረ ገጽ የተገኘው ጽሑፍ ያትታል::
ተማሪዎች መጻሕፍትን እያነበቡ በሚያጠኑበት ወቅት አንኳር ይዘቶችን እያሳጠሩ በማስታወሻ ደብተር እንዲይዙ ይመከራል:: ይህም በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ይዘቶችን በቀላሉ ለማስታወስ እና አይረሴነት እንዲኖራቸው የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው::
ክለሳን ባህል ማድረግ ሌላው ጥሩ እና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል የአጠናን ዘዴ ተደርጎ ተመላክቷል:: በተጨማሪም የማስታወስ ችሎታን ለማዳበር እና በራስ የመተማመን ክህሎትን ለማሳደግ ራስን በራስ መፈተን እንዲሁም ከሌሎች ተማሪዎች ጋርም መጠያየቅ ይመከራል::
በእያንዳንዱ የጥናት ጊዜ በቂ ረፍት መውሰድ ይገባል:: ይህም አዕምሮን ዘና በማድረግ የተሻለ የጥናት አቀባበል እንዲኖር ያስችላል:: የእግር ጉዞ ማድረግ፣ የተለያዩ አካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን መሥራት፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ አጫጭር ፊልሞችን እና ድራማዎችን ማየት ለአዕምሮ ዳግም ዝግጁነት ያግዛል::
ጥናቱ ግቡን እንዲመታ ፀጥ ያለ ቦታን መምረጥ፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ነጻ መሆን፣ ጥናትን ይዘቱ ከባድ ነው ከሚባለው የትምህርት አይነት መጀመር፣ ያለፉ ፈተናዎችን እና መልመጃዎችን መሥራት ዓመቱን ብቁ ሆኖ ለማጠናማቀቅ የሚያግዙ የፈተና መዘጋጃ ዘዴዎች ሆነው ተመላክተዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም