ለልብ ድካም ፈውስ ተስፋ ሰጪው

0
145

ለልብ ድካም ህሙማን ልብ ደም የመርጨት ተግባሯን ለማስቀጠል ሰውሰራሽ መርጪያ ወይም ማስተላለፊያን በመርጃነት በቀዶ ህክምና ማካተት የደከሙ የጡንቻ ህዋሳት እንዲያገግሙ ማስቻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::

በአሪዞና የጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ባደረጉት ምርምር ለልብ ድካም ህሙማን በመርጃነት በልብ የግራ ከርስ ወይም ደም እያጣራ በሚያሰራጨው (Left ventricle) ሰው ሰራሽ መርጫ ወይም ማስተላለፊያ ማካተት የልብ የጡንቻ ህዋሳት እንደገና እንዲያንሰራሩ ማድረጉን አረጋግጠዋል::

ምርምሩ በተለያዩ አገራት በሚገኙ ከፍተኛ የጤና ተቋማት   የተካሄደ መሆኑን ያስነበበው ድረ ገጹ የተገኘው ውጤት ቀደም ብሎ የነበረውን አስተሳሰብ ያስለወጠ ወደፊት መድሃኒት ለመሻት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው ያሰመሩበት – የምርምሩ መሪ ዶክተር ሂሻም ሳዲቅ::

በ2011 እና በ2014 እ.አ.አ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች እና የምርምር ስራዎችን ለህትመት ያበቁት ዶክተር ሂሻም ሳዲቅ ለሰውሰራሽ የልብ መርጃ ምላሽ ከሚሰጡ  ህሙማን ከፊሉ የተገኘው ውጤት የልብ ድካምን በዘላቂነት ማዳን እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ነው የገለጹት::

በስዊዲን እና በጀርመን የምርምር ተቋማት በተናጠል ባደረጉት ምርምርም በናሙና ስራዎቻቸው የልብ የጡንቻ ህዋሳት ማገገም መቻሉን አረጋግጠዋል:: እንዲያውም ጤናማ የልብ ጡንቻ ህዋሳት ከሚባዙበት ስድስት እጥፍ የበለጠ እንደሚያገግሙ ወይም እንደሚታደሱ ነው የደረሱበት::

ዶክተር ሂሻም ሳዲቅ በምርምር ከተገኘው አዲስ እውነታ ማለትም ለልብ ህዋሳት መድከም ዋነኛው ገፊ ምክንያት ረፍት አለማግኘት ሳይሆን እንደማይቀር እምነታቸውን አስፍረዋል:: ለዚህ ደግሞ ከውልደት ጀምሮ ረፍት አልባውን ልብ በሚያሳርፍ ሰውሰራሽ ልብ መርዳት የደከሙ ህዋሳትን ማደስ፣ ማንሰራራት መቻሉን በማስረጃነት ጠቅሰዋል::

በልብ ድካም ለተጠቃ ታማሚ በግራ የልብ ክፍል የሚገጠምለት ሰውሰራሽ መግፊያ በቀጥታ የልብ የውስጥ ክፍልን አልፎ ከዋናው የደምቱቦ “Aorta” ጋራ የሚገናኝ መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪዎቹ ይህ ሂደት ለልብ የእረፍት ጊዜ እንደሚሰጥ ነው የጠቆሙት – ተመራማሪዎቹ:: በመጨረሻም ሰውሰራሽ ማሰተላለፊያ  መርጃ የደከሙ የልብ ህዋሳትን እንዲያገግም ማስቻሉ 25 በመቶ በሚሆኑ ታማሚዎች ላይ ብቻ ነው የተስተዋለው:: ይሄ ማለት ለሰው ሰራሽ ልብ ምላሽ የማይሰጡ፣ የደከሙ ህዋሳት የማያገግሙባቸውንም ለይቶ ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ ከተቻለ የልብ ድካምን ሙሉ በሙሉ ማዳን እንደሚቻል ነው በማደማደሚያነት ያሰመሩበት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here