ለመልካም አገልግሎት አሰጣጥ መፍትሄው የቱ ነው?

0
768

“እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንደሚባለው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ድሮም ቅሬታ ያላጣው የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የአገልጋይነት ስሜት መዳከሙን በርካቶች ያነሳሉ፡፡ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚስተዋለው ችግር በክልሉ ምክር ቤትም አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ ለችግሩ አሳሳቢነት ማሳያ ነው፡፡
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚደረገውን ሂደት እንደገደበው የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለአሚኮ ተናግረዋል። የሰላም ዕጦት ግብር እንዳይሰበሰብ፣ የመንግሥት ሰራተኛው እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ እንዳይሰራ በማድረግ ሕዝብ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዳያገኙ እንዳደረገውም አፈ ጉባኤው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያደረገውን ጥናት ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ለብዙኃን መገናኛዎች መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ተቋሙ በ15 የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከየካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ባደረገው ጥናት ችግሮች መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡
በጥናቱ ከተለዩት ችግሮች መካከል በሕግ በተሰጠ የሥልጣን ወሰን ብቻ ኃላፊነትን አለመወጣት፣ ለሕዝብ አስተያየት ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት፣ የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን ለተገልጋይ ግልጽ አለማድረግ እና ውሳኔውን ለተገልጋይ በጽሑፍ አለመስጠት ይገኙበታል፡፡ በሕግ የታዘዙ መረጃዎችን ይፋ ማድረጊያ የመረጃ ማዕከል አለመኖር፣ ቢኖርም የማይሠራ እና አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑ ደግሞ ለአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩ መንስኤ መሆኑን ለይቷል፡፡
በሕግ የታዘዙ የመሥሪያ ቤቶች የወደፊት ተግባራት እና ውሳኔዎች ለሕዝብ በወቅቱ ይፋ አለማድረግ፣ መረጃ እንዲሰጥ ለሚቀርብ ጥያቄ ተገቢ እና ወቅታዊ ምላሽ አለመስጠት፣ በሕግ የታዘዙ የሥራ ሪፖርቶችን ለሚመለከተው አካል አለማቅረብ እና የግልጽነት ችግሮች በጥናቱ የተረጋገጡ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ይፈጥራሉ የተባሉ ግኝቶች ናቸው፡፡
የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለሚፈልጉ ሁሉም ዜጎች ተደራሽ አለመሆናቸውም በጥናቱ ተለይቷል፡፡ በዚህም ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋዊያን ክትትልና ቁጥጥር ተገዥ ያለመሆን ችግሮች ተስተውለዋል፡፡ መረጃ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ዜጎችን በእኩልነት እና በፍትሐዊነት አለማስተናገድ፣ የአስተዳደር መመሪያዎች ሲረቀቁ ዜጎች እንዲሳተፉ እኩል ዕድል አለመስጠትም ከፍትሐዊነት አንፃር የታዩ ክፍተቶች ሆነዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩን ለመፍታትም በአሁኑ ወቅት በርካታ የመንግሥት ተቋማት አሰራራቸውን እየፈተሹ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎችን እያስተዋወቁ እና ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡ ለዚህም የደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር አንዱ ማሳያችን ነው፡፡
የአስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረሚካኤል ለአሚኮ እንደገለጹት አገልግሎት ሰጪው ተገልጋይን እንዴት ማስተናገድ እንዳለበት አውቆ የመምራት፣ ባለጉዳይ ለአገልግሎት ሰጪው ምን እንደሆነ ያለማወቅ ችግሮች ለአገልግሎት አሰጣጡ ዋና ተግዳሮት ሆነው መለየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ቁጥጥር መላላት ደንበኛ በሰዓቱ አገልግሎት አግኝቶ እንዳይመለስ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ የሀገሪቱ የመንግሥት ተቋማት የሥራ መጀመሪያ ሰዓት 2:30 ሆኖ እያለ ከሦስት ሰዓት በኋላ መግባት፣ ከዚያም 11:30 ሳይሆን ቢሮን ዘግቶ መውጣት ሕዝብ በዕለቱ እንዲፈጸሙለት አስቦ የመጣባቸው ጉዳዮች እንዳይፈጸሙ በማድረግ በአገልግሎት ፈላጊውና በአገልግሎት ሰጪው መካከል ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳድር ችግር እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታውን ምክንያት በማድረግ ቢሮ ያለመክፈት እና ሠራተኛው የሚጠበቅበትን አገልግሎት ያለመስጠት ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ መሆናቸውንም መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል ፡፡
መምሪያው ለተገልጋይ መጉላላት እና ፈጣን ምላሽ አለማግኘት ማነቆ ናቸው ያላቸውን ችግሮች ከለየ በኋላ ተገልጋይ የሚበዛባቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ አንድ ማዕከል ማምጣቱን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ እስክንድር ገለጻ ተጓዳኝ የሆኑ ተቋማትን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ደንበኛው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ አጠናቅቆ እንዲመለስ የሚያደርግ ነው፡፡ ለአብነትም የከተማ መሰረተ ልማት መምሪያው በሥሩ ሕንጻ ሹም፣ መሰረተ ልማት እና መሬት አስተዳደርን ያቀፈ ሆኖ ከዚህ በፊት አገልግሎቶችን በተለያዩ ቦታዎች ይሰጥ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ በተሳሰሩ አንድ ማዕከል የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ ከመሆኑም ባሻገር በአገልግሎት ሰጪው እና ፈላጊው መካከል መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል፡፡
ለአሰራሩ ተግባራዊነትና መስፋት ለአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና መሰጠቱን፣ መምሪያውም በተሰጠው ሥልጣንና ኀላፊነት መሰረት ክትትልና ቁጥጥር እንሚያደርግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፣ ቅድሚያ የሰላም እና ደኅንነት ሥራዎችን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here