ለመስኖ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው

0
167

በበጋ መስኖ የማምረት ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፤ በቢሮው የአትክልት እና ፍራፍሬ ከፍተኛ ባለሙያ አወቀ ዘላለም እንደተናገሩት በአማራ ክልል 333 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማት ይችላል፡፡ እስካሁን  መልማት የቻለው ደግሞ 285 ሺህ ሄክታር መሆኑን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂን፣ የተሻሻለ አሠራርን እና የባለሙያ ምክርን በመጠቀም እየተተገበረ ላለው የበጋ መስኖ ልማት ውጤታማነት በሄክታር እስከ 38 ኩንታል ምርት መድረሱን ገልጸዋል።

ለዘርፉ ትኩረት በመስጠትም ከመኸር በተጨማሪ በበጋ መስኖ የማምረት ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በበጋ መስኖ የሚለሙ ሰብሎች በክረምት ከሚለሙት ያነሰ የአደጋ ተጋላጭነት እና የተሻለ ምርታማነት እንዳላቸውም ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡

ባለሙያው እንዳሉት የአርሶ አደሮች የሞተር ነዳጅ ፍላጎት መጨመሩ እና በቆሎ ከጓሮ አልፎ በማሳ መመረቱ የበጋ መስኖ ተቀባይነት ማሳያ ናቸው። የቴክኖሎጂ እና የተሻሻሉ አሠራሮችን መጠቀም ሊጠናከር እንደሚገባ የተናገሩት አቶ አወቀ ዘላለም ባለፉት ዓመታት የተሠራው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎላ ብሎ ቢታይም አሁንም የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቶች የማዳበሪያ፣ የዘር እና መሰል ድጎማዎችን በማድረግ አርሶ አደሮችን ለማስተማር ግፊት ማድረጉ ቋሚ ስላልሆነ በዘላቂነት አርሶ አደሮች በራሳቸው በባለቤትነት እንዲሠሩ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here