ለመጪዉ ዘመን የተነደፈዉ

0
137

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (NASA) በ2016 እ.አ.አ ወደ ጠፈር ለሚያደርገው ተልዕኮ አዲስ የተነደፈ የጠፈርተኞች ልብስን በጣሊያን በተካሄደው የስነህዋ ጉባኤ ላይ ለእይታ ማብቃቱን ዩፒ አይ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም “Artimis lll mission’’ ለተሰኘው በ2026 እ.አ.አ ወደ ህዋ ለሚያደርገው ተልእኮ “አክስዮም ስፔስ” እና “ኘራዳ” በተሰኙ ድርጅቶች በትብብር የተነደፈ አዲስ የጠፈርተኞች ልብስ ለእይታ አብቅቷል::
አዲሱ የጠፈር ልብስ ንድፍ በጣሊያን ሚላን ከተማ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የህዋ ጉባኤ ላይ ለመጪው ዘመን የጠፈር አልባሳትነቱ ፀድቆ እንዲሰራበት ይፋም ሆኗል:: የጠፈር ልብሱ ንድፍ ቀደም ብሎ በጠፈር ተልእኮ ለተስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ የተዘየዱበትም ነው ተብሏል:: ለአብነት ንድፉ ሊለዋወጥ፣ ሊሰፋ፣ ሊጠብ እንዲሁም ተልእኮዎቹን መሰረት አድርጐ ማስማማት የሚቻል መሆኑን በጠንካራ ጐንነቱ የንድፉ አቀራቢ ምክትል ኘሬዘዳንት ራስል ራልስተን አብራርተዋል:: ምክትል ኘሬዘዳንቱ የሰው ልጅ በጠፈር ለሚያደርገው አሰሳ የጠፈርተኞች ልብሱ ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረውም ለጋዜጦኞች በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል::
አክስዮም ስፔስ የተሰኘው ተባባሪ የጠፈር ልብስ አዘጋጁ ድርጅት ኘሬዘዳንት ማት ኦንድለር ልሂቃንን ያካተተው እርሳቸው የሚመሩት ቡድን የነደፈው አዲሱ የጠፈርተኞች ልብስ ባለፉት ዓመታት በነበሩ የጠፈር ተልእኮዎች ለተስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ የሚዘይድ መሆኑንም ጠቁመዋል::
ሁለቱ ድርጅቶች በትብብር አዲስ የጠፈር ልብስ ንድፍ መሰራታቸው ለሌሎችም በኢንዱስትሪው በትብብር እንዲሰሩ መሰረት የሚጥል መሆኑን ነው የተሰመረበት – በድረ ገፆች::
“ፕራዳ” የተሰኘው ድርጅትም አዲሱ የጠፈር ልብስ ቀለሙ ምን መምሰል እንዳለበት፣ የሚከሰቱ ችግሮችን እንዲቋቋም ግብአት በመምረጥ፣ ስፌቱ እንዴት መሰራት እና ምን መምሰል እንዳለበት በንድፉ አማራጭ በማቅረብ እና በመወሰን ተሳትፏል::
የጠፈር ልብሱ ሙቀት እና የፀሀይ ብርሃንን አንፀባርቆ እንዲመልስ፣ በጨረቃ ላይ አቧራ ወደ ውስጥ እንዳይገባው የሚከላከል ሆኖም ነው የተሰራው ::
የጠፈር ልብሱ ናሙና አቅራቢ ምክትል ኘሬዘዳንት ራሰል ራልስተን “ፕራዳ” የተሰኘው ድርጅት የጠፈር ልብሱ ውበት እንዲኖረው ያቀረበውን አማራጭ ተቀብለውታል:: ሁለቱም ድርጀቶች በልብሱ መገጣጠሚያዎች ላይ በጉልህ የሚታይ ቀይመስመር መኖር አለበት በሚል ያቀረቡት ከሌሎች የጠፈር ተጓዦች መለያ በመሆኑ፣ ለጠፈርተኞች ቡድን መሪም ልዩ ቀይ ምልክት ይኑር የሚለውን ጨምሮ ይሁንታን አግኝቷል::
በማጠቃለያነት አዲሱ የጠፈር ልብስ ንድፍ ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት የኦፓሎ ጠፈርተኞች ከለበሱት የተሻለ ለእንቅስቃሴ የሚመች የጤና ክትትል ስርዓትንም የሚያካትት መሆኑ ነው የተገለፀው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here