ለመጪዉ የትምህርት ዘመን

0
11

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? እየተጠናቀቀ ያለው የክረምት ጊዜስ እንዴት ነው? ልጆች ቀጣዩ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እየተቃረበ ነው:: እናንተም ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው? ልጆች፣ ለቀጣዩ ዓመት የትምህርት ዘመን የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ የሚገኝ ልጅ እናስተዋውቃችሁ::

አዶኒያስ ዳንኤል የ10 ዓመት ልጅ ሲሆን በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው:: የሚማረውም በባሕር ዳር አካዳሚ ትምርት ቤት ነው:: አዶኒያስ ያለፈውን ዓመት የትምህርት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንዳለፈው ይናገራል:: በቀጣይ ዓመት አራተኛ ክፍል የሚሆነው አዶኒያስ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል::

አዶኒያስ የአራተኛ ክፍል መጽሐፎችን በወላጆቹ አማካኝነት በማግኘት ክረምቱን በሙሉ ሲያነብ ከርሟል:: አጋዥ መጽሐፎችንም እንዲሁ ሲያነብ ቆይቷል:: በሦስተኛ ክፍል ቆይታው የከበዱትን እና ለቀጣይ አራተኛ ከፍል ሲሆን የሚያግዙትን ነገሮች አስጠኚ ተቀጥሮለት እየተማረ ይገኛል::

ፊልም ማየት፣ የተረት መጸሐፎችን ማንበብ እና ከጓደኞቹ ጋር መጫወት እንደሚወድ የሚናገረው አዶኒያስ ክረምቱን ከመጫወት ባሻገር ቁምነገር ሲሠራበት እንደቆየ አጫውቶናል:: ወላጆቹን በሚችለው አቅም ማገዝ ሌላው ተግበሩ እንደሆነ ነግሮናል:: በአቅራቢያው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያንም የአብነት እና የግዕዝ ትምህርት እንደሚማርም ገልጾልናል::

ልጆች እናንተም ለቀጣዩ ዓመት የትምህርት ዘመን አስቀድማችሁ መዘጋጀት እንዳለባችሁ ከአዶኒያስ መማር ትችላላችሁ:: የሚከብዷችሁን የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ ቀድማችሁ ከታላላቆቻችሁ፣ ከአስጠኚዎች ወይም ከወላጆቻችሁ ብትረዱ በቀጣዩ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣ ያግዛችኋል::

ተረት

ውሻዉ

አንድ ቀን አንድ የተራበ ውሻ ምግብ ፍለጋ ቀኑን በሙሉ ሲንከራተት ከዋለ በኋላ በስተመጨረሻ ከአንድ ስጋ ቤት ደረሰ:: በዚያም ትንሽ ስጋ ያለበት አጥንት አገኘ:: ያገኘውን ምግብ ተደብቆ የሚበላበት ቦታ ይዞት ሄደ:: አጥንቱን ለረጅም ጊዜ ሲቆረጥም ቆየ እና ውኃ ጠማው:: የውኃ ጥሙን ለማርካት ወደ ወንዝ ወረደ::

አጥንቱን ሌላ ውሻ እንዳይወስድበት ስለፈራ በአፉ አንጠለጠለው:: ውሻው ከወንዙ እንደደረሰ ከወንዙ ጫፍ ቆሞ ውኃ ሊጠጣ ሲል የራሱን ነጸብራቅ ተመለከተ:: የራሱ ነጸብራቅ መሆኑን ግን መረዳት አልቻለም:: ይልቁንም ወንዙ ውስጥ የታየው ነጸብራቁ ሌላ አጥንት የያዘ ውሻ መሰለው:: ስለዚህ “በውኃ ውስጥ ከማየው ውሻ ተጨማሪ አጥንት ማግኘት እችላለሁ” ብሎ አሰበ:: ስግብግብ ስለሆነ በውኃ ውስጥ ባየው አጥንት በጣም ጓጓ:: በውኃ ውስጥ የሚታየውን ውሻ ለማስፈራራት አፉን ሲከፍት አጥንቱ ወንዝ ውስጥ ገባበት:: ውሻውም እያዘነ ተመልሶ ሄደ:: ልጆች ከዚህ ተረት የምንማረው ያለአግባብ የሌሎችን መመኘት የራስን እንደሚያሳጣ ነው::

ይሞክሩ

  1. ሳይጠይቁኝ የምሰጠው፤ ሳልወርስ የምወስደው፣ ሳልጠየቅ የማካፍለው፣ ሳላሥር የምይዘው፣ ምንድን ነው?
  2. ትንሽ ዕቃ ከገደል ተጣብቃ ምንድን ናት?
  3. ብልሃተኛ ነጋዴን ጉም ለብሶ ይቀሙት እወቅልኝ?

መልስ

  1. ፍቅር
  2. ጆሮ
  3. ንብ

ነገር በምሳሌ

ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች

አንድ ሰው ራሱን ካገለለ ጥሩ ነገር በሚከፋፈልበት ጊዜ በቀላሉ ሊረሳ እና ሊታለፍ ይችላል።

 

ጥሩ ዛፍ ላይ ከወጣህ ወደ ላይ የሚገፋህ ሰው አታጣም

ጥሩ እና ተገቢ የሆነ ግብ ላይ ለመድረስ የምትጣጣር ከሆነ ድጋፍ ማግኘትህ አይቀርም ማለት ነው።

 

ውኃ እና ሰላም  ሲያጧቸው ዋጋቸው ይታወቃል

የአንድን ነገር ዋጋ ስናጣው ነው የምናውቀው።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here