መምህርነት ሁሉንም ሙያዎች የሚፈጥር ሙያ ነው ይሉታል:: በእርግጥም በመምህርነት ድህነት ተረት ይሆናል፤ ከመኖሪያ ቤት ግንባታ ጀምሮ ግዙፍ ከተማዎች እንዲሁም ሀገር ይገነባል፤ መዳረሻ መንገድ ይከፈታል፤ ኤሌክትሪክ ተፈጥሯል፤ ቴክኖሎጂ ተፈጥሮ የዓለም ሕዝብ ወደ አንድነት መጥቷል::
በአጠቃላይ መምህርነት የሚፈጥራቸው ባለሙያዎች የሚያፈልቋቸው ግኝቶች የሰውን ልጅ አኗኗር አቅለዋል:: መምህራን አሻጋሪ ትውልድን በመቅረጽ የከበረ ሙያ ቢኖራቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያጋጥሙ ግጭት እና ጦርነቶች ግን የሙያው ባለቤቶች በራሱ ስለ ሙያው በነጻነት ምስክርነትን እንዳይሰጡ አስገድዷል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመምህራን ቀንን ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም አክብሯል:: ትምህርት መምሪያዉ ቀኑን ያከበረው “መምህር ዋጋ ከፍሎ ትውልድ ቀራጭ ነው” በሚል መሪ ቃል ነው:: የመምህራንን ልፋት እና ድካም ማስታወስ እና በቀጣይ የሚከናወነውን የትምህርት ሥራ በውጤታማነት ማስኬድ ደግሞ የመድረኩ ዓላማዎች ናቸው:: በዚህም ምስጉን የትምህርት አመራሮች እና ባለሙያዎች፣ የፈጠራ ሥራ የሠሩ ተማሪዎች፣ ለተማሪዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ተቋማት እና ለትምህርት ሥራ ድጋፍ ያደረጉ አጋር አካላት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል:: በጡሮታ የተገለሉ መምህራንም የክብር ሽኝት ተደርጎላቸዋል::
ዕውቅናው ለቀጣይ የትምህርት ዘመን የተሻለ የትምህርት እንቅስቃሴ የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ እንደሚሆን ዕውቅና የተሰጣቸው መምህራን ተናግረዋል::
የመስከረም 16 አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ዘመኑ ዓለሙ ዕውቅና ከተሰጣቸው መምህራን መመካከል ይገኙበታል። መሰል መድረኮች የመምህራንን ክብር ከፍ ከማድረግ ባለፈ የማስተማር ተነሳሽነትን በመጨመር ለትምህርት ጥራት ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ምስጉን ሠራተኛ ተብለው ዕውቅና እንደተሰጣቸው የሚናገሩት መምህሩ፣ ሌሎች መምህራንም ለሀገር እና ለትውልድ ጥሩ ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል። የተሰጠው ዕውቅና በቀጣይ የትምህርት ዘመን የተሻለ መማር ማስተማር ለማከናወን የሚያነቃቃ እንደሚሆን ነው የገለጹት።
ሌላው የሪሲፔንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት መምህሩ ደመላሽ አላየ በምስጉን መምህርነት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ዕውቅናውን የልፋት ውጤት ሆኖ ቢያስደስታቸውም ከዚህ የበለጠ ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም መሥራት ዓላማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች እና መምህራን የነበራቸው የተሻለ ዝግጅት በዓመቱ ለማሳካት ከታቀደው የተሻለ መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል። ለ2018 የትምህርት ዘመንም ከተጠናከረ ዕቅድ ጋር በመሥራት ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። ለዚህም ዕውቅናው ትልቅ ተነሳሽነትን ከከፍተኛ ኃላፊነት ጋር የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ2017 ዓ.ም 136 ሺህ 570 ተማሪዎችን ለማስተማር ዕቅድ ተይዞ እንደነበር ያስታወቁት የትምህርት መምሪያ ኃላፊዉ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) ናቸው:: በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የከረሙት ግን 126 ሺህ 471 ተማሪዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል:: በዙሪያ ወረዳው ከሚገኙ ውስን ትምህርት ቤቶች ውጪ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ማለፋቸውንም ገልጸዋል::
እንደ መምሪያ ኃላፊው በከተማ አስተዳደሩ ሲሰጥ የነበረው መማር ማስተማር ከችግር ውጪ ሆኖ አልተጠናቀቀም:: መማር ማስተማር እንዲቋረጥ ተደጋጋሚ የቦምብ ፍንዳታ መከሰቱ ደግሞ የዚህ ማሳያ ነው:: በዚህም መምህራን እና ተማሪዎች ተጎድተዋል::
የጸጥታ ችግሩ የትምህርት ሥራውን እንዳያስተጓጉለው ከነዋሪው ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጓል:: ከ26 ሺህ 224 የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ ሕዝቡ የትምህርት ዘብ እንዲሆን የማድረግ ሥራም ተሠርቷል:: እነዚህም ሥራዎች የትምህርት ዘመኑን በስኬት ለማጠናቀቅ አጋዥ መሆናቸው ተመላክቷል::
ታስቦ የዋለው የመምህራን ቀን የ2018 የትምህርት ዘመንን በተሻለ መንገድ ለማከናወን ንቅናቄ የተፈጠረበት ነው:: መምህራንን ጨምሮ ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ አድርገው ሲሠሩ ለነበሩ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ምስጋና እና ዕውቅና ሲሰጥ ለ2018 ዓ.ም ዝግጁ የማድረግ ዓላማንም ያነገበ እንደሆነ ዶ/ር ሙሉዓለም አስታውቀዋል::
የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ማሻሻል፣ ሰላማዊ መማር ማስተማርን ማስፈን እና የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን አጠናክሮ ማስቀጠል የትምህርት ዘመኑ ዋነኛ ግቦች መሆናቸውን አስታውቀዋል:: እነዚህም የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ልክ ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል::
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ትምህርት ድህነትን እና ኋላ ቀርነትን ተፋልመን የምናሸንፍበት መሣሪያ ነው ብለዋል:: ትምህርት ላይ በትኩረት የሠሩ ሀገራት በዓለም ዋና ላይ ቁንጮ የሆነውን ኢኮኖሚ እንዲሁም ዓለምን በአንድ እያስተሳሰረ ያለውን ቴክኖሎጂ ማሳካታቸውን ለማሳያነት አንስተዋል::
የአማራ ክልል ሕዝብ ለትምህርት ትልቅ ክብር ያለው፣ የተማረ የሰው ኃይል ችግር ፈቺ ነው ብሎ የሚያምን እንደሆነ ገልጸዋል:: በዚህም ከሀብት ሁሉ አብልጦ ለልጆቹ ማውረስ የሚፈልገው ማስተማርን ነው ብለዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመ ያለው የሰላም መደፍረስ ግን ለትምህርት ቅድሚያ ቦታ የሚሰጠውን የአማራ ሕዝብ ወደ ኋላ እንዲቀር እያደረጉት ነው ተብሏል::
ችግሩ በልጆቻችን የነገ ዕጣ ፋንታ እና በዛሬው ትውልድ ላይ የሚያደርሰው ምስቅልቅል ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል:: እደረሰ ያለው ጉዳት በገንዘብ አይተመንም፤ የደረሰውን ጉዳት ተነጋግረን በአጭር ጊዜ የምንመልሰውም አይሆንም ነው ያሉት:: ትምህርት እንዲቋረጥ በተደጋጋሚ ቦምብ የማፈንዳት ሙከራዎችን ለችግሩ ተጽዕኖ ማሳያ አድርገው አንስተዋል::
“የእኛ ተማሪዎች መስማት የነበረባቸው የትምህርት ቤቶቻቸውን የደወል ድምጽ እንጂ የቦምብ እና የፈንጂ ፍንዳታ አልነበረም” ያሉት አቶ ጎሹ፣ መምህራን ዋጋ ከፍለውም ቢሆን ትምህርቱን በማስቀጠል ተማሪዎች እንዲፈተኑ ማድረጋቸውን ተናግረዋል::
ትምህርትን ከቤተክርስቲያን ጀምሮ እየተማረ ያደገ ማኅበረሰብ ዛሬ እንዴት ልጆቹ ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ ተፈረደበት፤ ትምህርት ቤት በአቅራቢያው እንዲሠራለት ረጅም መንገድን በባዶ እግሩ ተጉዞ መንግሥትን የሚጠይቅ፣ ስሚንቶ በትከሻው ተሸክሞ ትምህርት ቤት በሚገነባት የልጆቹን የነገ የተሻለ ሕይወት የሚሠራው ሕዝብ ላይ ልጆቹን እንዳያስተምር መከልከል ግቡ ምንድን ሊሆን ይችላል? ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አንስተዋል::
እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባዉ አሁናዊ አካሄዱ ራሳችንን በራሳችን ከማጥፋት የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም:: ከአሁን በኋላ መሣሪያ የሚያነግብ ሳይሆን በብዕር ሀገር የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር መታተር ይገባል::
ከጊዜ በኋላ ከተወዳዳሪነት ውጪ ላለመሆንም ልጆቻችን ለሌላ ሦስተኛ ዓመት ከትምህርት ውጪ እንዳይሆኑ መሥራት ተገቢ መሆኑን ነው ያሳሰቡት::
አቶ ጎሹ እንዳሉት ሀገር ጸንታ ታሪኳ ሳይዛነፍ በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ አዕምሮው በዕውቀት የተገነባ ትውልድ ያስፈልጋል::
በተሳሳተ መንገድ ታሪክን መጠቀም ሀገርን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይመራታል:: ይህንን ማስተካከል እና ማረም የሚቻለው በተማረ ትውልድ ብቻ ነው::
ታሪክን በወጉ እና በልኩ የሚናገሩ፣ የሚጽፉ እና የሚያስረዱ፣ ለሀገር ቀጣይነት የሚተጉ ትውልዶችን ለማፍራት ትምህርት መሠረቱ መሆኑን ሲገልጹ የመምህርን ሚና ደግሞ ግንባር ቀደም መሆኑን አንስተዋል:: ይህንንም ለማሳካት መምህራን ችግር ሳይገድባቸው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል:: በቀጣይም መጭውን ትውልድ የሚሠራ ትውልድ ለማፍራት በትጋት እና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ እና የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለማሻሻል የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል:: ከመምህራን ጋር በቅርበት መሥራት እና የጋራ መግባባት መፍጠር የትምህር ዘርፉን ካሉበት ችግሮች ለማውጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል:: በየደረጃው ያለው የትምህርት ባለድርሻ አካልም የመምህራንን ቀን በማክበር ማመስገን እንዳለበት ገልጸዋል፤ ይህም ተነሳሽነታቸውን ከፍ በማድረግ በትምህርት ማሳካት የሚገባውን ግብ ለማሳካት ጉልህ ሚና ለመጫወት ያስችላል ነው ያሉት::
ግዕዝ በአማርኛ
ኀጥአ – አጣ
ነትገ -ጎደለ
ከርመ – ከረመ
ከብረ – ከበረ
ከብደ – ከበደ
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም