ለማሳቅ የተፈፀመ ቀልድ

0
10

በማህበራዊ ሚዲያ ወይም “በቲክቶክ” ታዋቂ የሆነው የ27 ዓመቱ ፈረንሳያዊ በፓሪስ ከተማ ጐዳናዎች እየተዟዟረ በህክምና መድሃኒት መስጫ መርፌ “ሲሪንጅ” አልፎ ሂያጆችን የሚወጋ በማስመሰል “ፕራንክ” ወይም በማስደንገጥ ለማሳቅ በፈፀመው ድርጊት በስድስት ወራት እስራት መቀጣቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ትክክለኛ ስሙ ኢላን ኤም ነው በማህበራዊ ሚዲያ አሚን ሞጂቶ በሚል ይታወቃል፤ በፓሪስ የተለያዩ ጐዳናዎች በመዘዋወር በባዶ የህክምና መስጫ መርፌ የሚወጋ በማስመሰል በማስደንገጥ የሚፈጠርባቸውን ስሜት እየቀረፀ  ለእይታ የሚያበቃ ነው፡፡

ግለሰቡ በዚሁ አድራጐቱ ባደረሰባቸው ድንጋጤ የተከፉ ለፖሊስ ክስ አቅርበዋል፤ ጉዳት፣ ሁከት አድርሶብናል የሚል፡፡ ፓሊስም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ መስርቶበታል፡፡ ግለሰቡ ወይም ድርጊቱን ፈፅሟል ተብሎ የተከሰሰው ኢላን ኤምም ድርጊቱን ግለሰቦችን ለመጉዳት ሆን ብሎ አለመፈፀሙን በመግለፅ ምላሽ ሰጥቷል፤ ተከራክሯል፡፡

ክሱን እና የተከሳሹን መልስ የሰሙት ዳኞች ተከሳሹ ጉዳት አላደረሰኩም ቢልም በደረሳቸው ማስረጃ መሰረት  ለቀልድ   በ“ሲሪንጅ” ካስደነገጣቸው መካከል ተጐድተው በጤና ተቋማት   ለመመርመር የተኙ መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢላን ኤም ለችሎቱ ከበየነ መረብ በስፔን እና ፖርቹጋል ሲከወን ያየውን በመኮረጅ በአገረ ፈረንሳይ ዋና ከተማ መፈፀሙን እንጂ ጉዳት ለማድረስ አስቦ፣ አቅዶ አለመፈፀሙን የእምነት ክህደት ማረጋገጫ ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ዓቃቤ ህጎች በግለሰቡ አወዛጋቢ ቀልዶች ምንም ዓይነት እውነተኛ መርፌ የመወጋት ጥቃት አለመድረሱን አረጋግጠዋል፡፡ ብዙዎቹ ተጐጂዎች ግን በድንጋጤ መሰቃየታቻውን፣ ከተጠቂዎች አንዱ ደግሞ በቫይረስ የተጠቃ ያህል በእንቅልፍ ልቡ በቅዥት እየጮኽ እንደሚሰቃይ ነው ያብራሩት፡፡

የተከሳቩ ጠበቃ ፍ/ቤቱ ለተከሳሽ ምህረት እንዲያደርግለት ቢጠይቅም ዳኛው  ተፅእኖ ፈጣሪው “ቲክቶከር” ድርጊት ፍርሃት እና ድንጋጤ ማድረሱን በማረጋገጣቸው  በስድስት ወራት እስር እና ስድስት ወር ገደብ ተወስኖበታል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here