በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ ከሚኖሩ አምስት ሰዎች አንዱ ለቀላል የመንፈስ ጭንቀት፣ ለሥነ ልቦናዊ ችግር ወይም ለአዕምሯዊ መረበሽ ይዳረጋል:: ከአሥር ሰዎች አንዱ ደግሞ ለከባድ የአዕምሮ መቃወስ ተጋላጭ እንደሚሆን ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2019 ይፋ ያደረገው መረጃ ዋቢ ነው::
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ በርከት ያሉ ሀገራት በእርስ በርስ ጦርነት እና ድንበር ዘለል በሆኑ ጦርነቶች ውስጥ እያለፉ ይገኛሉ:: በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ከትምህርት ውጪ ከሆኑት ከ250 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መፍትሔ በራቃቸው ግጭቶች ምክንያት ከትምህርት የራቁ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል::
ኢትዮጵያ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ መልኩን እየቀያየረ መፍትሔ አጥቶ አሁንም ድረስ በቀጠለ ግጭት ውስጥ ትገኛለች:: የሰሜኑ ጦርነት በአማራ ክልል ብቻ አራት ሺህ ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ ማድረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል:: ይህ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ፣ መምህራን ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ፣ የትምህርት እና የፈተና አሰጣጡ ወጥነት እንዳይኖረው አድርጓል:: ጦርነቱ ምንም እንኳ በሰላም ስምምነት ቢቋጭም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል መልኩን ቀይሮ መቀስቀሱን ተከትሎ የጥፋት ዳፋው አሁንም ቀጥሏል::
ሁለተኛ ዓመቱን ይዞ የሚገኘው በትጥቅ የታገዘ ግጭት በ2016 ዓ.ም በአንድ ዓመት ብቻ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ርቀው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል:: ችግሩ የትምህርት ዘመንም ቀጥሏል::
ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር የክልሉ ዕቅድ ነበር:: የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቱ እንዳስታወቁት በዓመቱ ለመመዝገብ ከታቀደው ተማሪ ውስጥ እስከ ሕዳር ወር አጋማሽ ጊዜ ድረስ በተጨባጭ ማሳካት የተቻለው ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል:: ቀሪዎቹ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች አሁንም “ትምህርት ቤቶች መቼ ተከፍተው ትምህርት እንጀምራለን” እያሉ ይገኛሉ::
ግጭቱ ትምህርት ቤቶችን ለተለያየ ጉዳት መዳረጋቸው፤ የውስጥ ግብዓታቸው መዘረፉ፣ ጦርነት ሕይወትን ሲበላ ያዩ ሕጻናት መኖራቸው፣ አሁንም ድረስ በየትምህርት ቤቶች ፍንዳታዎች መኖራቸው፣ ትምህርት የጀመሩትም በስጋት ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን መቀጠላቸው ትምህርት ለትውልድ ግንባታ የሚኖረው አበርክቶ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲቆይ አድርገዋል::
ሀገር እንደ ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ ዘመናትን እንድትሻገር የሚያደርገው ትምህርት ያለምንም መቆራረጥ እንዲቀጥል፣ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ያለ ምንም ሥነ ልቦናዊ መረበሽ ትምህርታቸውን አስቀጥለው ከግብ እንዲደርሱ ምን አይነት ወቅታዊ የመፍትሔ ስልቶችን መተግበር ይገባል? የሚለው የይዘታችን አንኳር ጭብጥ ነው::
ግሎባል ሞኒተሪንግ ሪፖርት “ግጭት እና ጦርነት በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ” በሚል ባጠናከረው ጥናታዊ ጽሁፍ የጸጥታ መደፍረስ በተለይ ታዳጊዎች ወዳልተገባ አካሄድ እንዲያመሩ ሊያደርጋቸው ይችላል:: ተማሪዎች ግጭት በትምህርት ተቋማት የሚያደርሰውን ጉዳት በቅርበት ስለሚከታተሉ፣ የትምህርት እንቅስቃሴ ሲገታ እና ቤት መዋል ሲጀምሩ ወደ ትጥቅ ግጭት ትግል ከመግባት ጀምሮ በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ሊሰማሩ እንደሚችሉ ጥናታዊ ጽሁፉ የጥናት ዳራውን በሶሪያ እና በሌሎች በግጭት ውስጥ ባሉ ሀገራት ላይ አድርጎ ማረጋገጡን አስታውቋል::
ተማሪዎች ረጅም ጊዜን ከትምህርት ውጪ በሚሆኑበትም ወቅት የሚያጋጥማቸው ያልተገባ ጭንቀት እና ድባቴ ሱስን ብቸኛ የመውጫ መንገድ አድርገው ሊወስዱ እንደሚችሉ ጥናቱ ጠቁሟል:: ይህም ሰዎች ለሕይወታቸው ትርጉም ከመስጠት ይልቅ ተስፋ ቢስነት ገዝፎ እንዲታያቸው ያደርጋቸዋል:: የመኖር ጉጉት ያጣሉ፤ ትምህርት ቢጀምሩም እንኳ ግባቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ጥረት በስጋት ምክንያት ይደናቀፋል:: ይህም የሚሆነው ተማሪዎች የሚያጋጥማቸው አዕምሯዊ መረበሽ ሐሳባቸውን ሰብስበው መዳረሻ አላማቸው ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆናቸዋል::
በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ በማይሆኑበትም ወቅት ራስን ወደ መውቀስ ይሸጋገራሉ:: ችግሩም እየጎለበት ሂዶ መጨረሻ ላይ ከሰው እንዲነጠሉ እንደሚያደርጋቸው ጥናቶች ያመላክታሉ::
የሥነ ልቦና ባለሙያው የሺዓምባው ወርቄ ከበኵር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በነበራቸው ቆይታ ተማሪዎች ከግጭት በኋላ ወደ ትምህርት በሚመለሱበት ወቅት በትምህርት ማሳካት የሚፈልጉትን ግብ እንዲያሳኩ ከትምህርት ቤቶች የማኅበረሰብ ክፍሎች እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል::
ከግጭት በኋላ የሚፈጠረው የድህረ አደጋ ሰቀቀን የሚፈጠረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ነው:: ምክንያቱም ብዙዎች ሰዎች ለወራት የጠመንጃ ድምጽ ሰምተዋል፤ ሰዎች ሲገደሉ አይተው ሊሆን ይችላል፤ ቤተሰቦቻቸውን በግጨቱ ምክንያት አጠዋል፤ አስገድዶ መደፈር የደረሰባቸውም ጥቂት ላይሆኑ ይችላሉ:: እነዚህ ሁሉ ጠባሳዎች በቀላሉ ሊረሱ የማይችሉ በመሆናቸው በሰዎች በተለይም በተማሪዎች የወደፊት መዳረሻ ግብ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራሉ::
ችግሩ የደረሰባቸው ልጆች ትምህርታቸውን ቢከታተሉም የደረሰባቸውን ችግር ለማንም መናገር አለመፈለጋቸው ግን የመማር ማስተማር ሂደቱ ዋና እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል የሥነ ልቦና ባለሙያው ጠቁመዋል:: ምክንያቱም የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ተማሪዎች የመረበሽ፣ በቀላሉ የመቆጣት፣ ብቸኛ የመሆን፣ የትምህርት አፈጻጸማቸው መቀነስ እና ሌሎች ምልክቶችን ሊያሳዩ ይችላሉ:: እናት ወይም አባቱ ሲገደል ያየ ታዳጊ አዕምሮው የሚያስበው የተጠቂነት እና የአቅመ ቢስነት ሥነ ልቦና በመሆኑ ከመጠቃት ይልቅ ማጥቃትን (በቀል) ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ሊነሳ ይችላል:: ከግጭት ወይም ጦርነት መልስ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ሕግና ደንብ ተገዥ ላይሆኑም ይችላሉ::
ታዲያ በዚህ ወቅት እያንዳንዱ መምህራን የሥነ ልቦና ባለሙያ ሆኖ ተማሪዎችን ሊያግዝ እንደሚገባ የሥነ ልቦና ባለሙያው ጠቁመዋል:: መምህራን እና ሌሎች የትምህርት ቤቱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተማሪዎች ስሜታቸውን አውጥተው እስከሚናገሩ ከመጠበቅ አካላዊ ስሜታቸውን በመረዳት፣ በመመርመር እና በማጤን የችግራቸው ተካፋይ እንደሆኑ ሊያረጋግጡላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል::
ተማሪዎች የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት መከታተል፣ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ጊዜያትን በአግባቡ መጠቀም፣ ለነገ ግብ አወንታዊ ምልከታ ማድረግ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መክረዋል::
ትምህርት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎችም ነገን በአወንታ መመልከት፣ ቤተሰብን በሥራ ማገዝ፣ ዕውቀትን ሊያስጨብጡ እና አስተሳሰብን በመልካም ሊቀይሩ የሚችሉ መጽሐፍን ማንበብ፣ ነገ ትምህርት እንደሚጀመር አስቦ ለትምህርት ራስን ዝግጁ ማድረግ፣ ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ጊዜ አጥተው ወደ ጎን ትተዋቸው የነበሩ የተለያዩ ክህሎቶቻቸውን ማየት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም