ለማይከፈል ውለታዋ

0
121

የህዳር  2 ቀን 2017 ዓ.ም

በተሽከርካሪ መገልበጥ በደረሰባቸው አደጋ ላለፉት 25 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ የሆኑ እናቱን ለማስደሰት ሀብት ንብረቱን ሽጦ፣ በጀርባው አዝሎ በማጓጓዝ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቦታዎችን በማስጐብኘት ላይ ያለ ወጣት በበርካቶች ከመመስገኑ ባሻገር ለሌሎች ተምሣሌትነቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ በጥቅምት ወር አጋማሽ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
ታያኦ የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር ወላጆቹ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ አባቱን በሞት ተነጥቆ እናቱ አካላቸው ተሽመድምዶ የአልጋ ቁራኛ የሆኑት፡፡ እሱ እና ታላቅ እህቱ ታዲያ እናታቸው በአደጋው የጀርባ አጥንታቸው እንደማይሰራ በመረጋገጡ የመንከባከቡን ሥራ ይያያዙታል፡፡ ታያኦ እድሜው ከፍ፣ አካሉም ጠንከር ሲል በጥጥ እርሻዎች በለቀማ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ እናትና እህቱን ከመደጐም ባሻገር ገንዘቡን አጠራቅሞ የራሱን ሬስቶራንት መክፈት ቻለ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የእናቱ የጀርባ አጥንት ጉዳት የማይድን ከመሆኑ ባሻገር በጊዜ ሂደት እየተባባሰ ለህልፈት እንደሚዳርጋቸው ተነገረው- ለታያኦ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ታዳጊው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ በውሳኔውም በንግድ ስራው ላይ መሰማራቱን አቁሞ ቤቱን እና መኪናውን ሸጦ አንደበታቸው የማይናገረውን፣ ሽባ እናቱን በጀርባው ተሸክሞ በቻይና የሚገኙ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቦታዎችን ያስጐበኛቸው ጀመር፡፡
በልጅነቱ እንዳዘሉት ባዘላቸው ልጆቸው ጀርባ ላይ ሆነው የቲያንሽን ተራራ፣ የቲያንቺን ሀይቅ፣ የቤጂንግ ቲያንሚን አደባባይን፣ ታላቁን ግንብ ወዘተ ጎብኝተዋል፡፡ እናቱ ግን ለልጃቸው የሚሰጡት ምላሽ የለም፤ ብቻ በየጉብኝት መዳረሻዎች ፈገግ ሲሉ ፊተቸው ሲፈካ ይመለከታል – በቃ የደስታው ምንጭ፣ ክፍያው እሱ ነው፡፡
የ31 ዓመቱ ታያአ እናቱን በጀርባው ተሸክሞ በቲያንሚን አደባባይ የተነሳቸው ፎቶ ግራፎች በማህበራዊ ድረ ገፆች ተለቀው በስፋት ተሰራጭተዋል፡፡ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎችም አድናቆታቸውን አጉርፈውለታል፡፡ የተሰጡት የማበረታቻ አስተያየቶች ለፅናቱ ለጥንካሬው ለእናቱ የከፈለው መስዋእትነት ተወድሶለታል፡፡
ወጣቱ ታያኦ ይህንን ስንቅ አድርጐ ከእናቱ ጋር እስከ ህልፈታቸው ለማጓጓዝ መወሰኑ ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here