በኲር በሐምሌ 21 ቀን 2017 እትሟ በ “በኲር ስፖርት” አምዷ በድንቅ የእግር ኳስ አጨዋወቱ ባለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት እንዲሁም ክብር ስለተቸረው ወጣት የባሕር ማዶ ስፖርተኛ ታሪክ አስነብባለች፡፡ በጽሑፉ እንደተገለጸው ባለተሰጥኦዉ የእግር ኳስ ተጫዋች ጥረቱን አጠናክሮ ከቀጠለ የወጣትነት ዕድሜው ሳያመልጠው በእግር ኳስ ስፖርት ባለማችን የቁንጮዎች ቁንጮ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ፣ ነገሩ “ሲያልቅ አያምር” እንዲሉ ሆነና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባድናቂዎቹ ዘንድ በዚህ ጥረቱ እና ስኬቱ ላይዘልቅ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡ የዚህ ስጋት ምክንያቱ ደግሞ ወጣቱ ስፖርተኛ ከማንነቱ በመፋታት ሌላ የእግር ኳስ ተጫዋችን ለመምሰል፣ ቢችል ደግሞ ለመሆን ቆርጦ መነሳቱ ነው፡፡
ወጣቱ ስፖርተኛ ራሱን ሆኖ ለላቀ ስኬት፣ ዕውቅና እና ክብር መትጋት ሲገባው በሌላ የእግር ኳስ ተጫዋች ተጽዕኖ ስር በመውደቅ ሜዳ ላይ እንዲሁም ከሜዳ ውጪ መጥፎ ድርጊቶች ሲፈጽም እንዲሁም መጥፎ ባሕርያት ሲያሳይ ተስተውሏል፤ በጽሑፉ እንደተገለጸው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ታዲያ ይህ 18ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በቅርቡ ያከበረ ስፖርተኛ በተጽዕኖ ስር የወደቀለት ስፖርተኛ በድንቅ የእግር ኳስ አጨዋወቱ ባንድ ወቅት ስሙ ባለም አቀፍ ደረጃ ገንኖ፣ ክብርን እና አድናቆትን ተችሮ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ በሚያሳየው ያልተገባ ባሕርይ እና በሚፈጽማቸው አጓጉል ድርጊቶች ተፈላጊነቱ እየቀነሰ መጥቶ ታላላቅ ያለማችን የእግር ኳስ ክለቦች ፊታቸውን ስላዞሩበት ባገሩ ውስጥ በልጅነት ክለቡ ተወስኖ እየተጫዎተ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡
ይህን ጽሑፍ እጽፍ ዘንድ ምክንያት የሆነኝ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት እያለ ራሱን መሆን ተስኖት ቀድሞት ከክብር ማማ የወረደን ተጫዋች የሚመር ጽዋ ለመጎንጨት “እየተጋ” ያለዉ የባሕር ማዶው የእግር ኳስ ስፖርተኛ በመሆኑ እሱን አስቀደምሁ እንጂ የእኛ የኢትዮጵያውያን እንዲሁም ኢትዮጵያውያት ከማንነት የመሸሽ ችግርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ስለመሆኑ ጠፍቶኝ ወይም ችግሩን ችላ ብየው አይደለም፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት ይነስም ይብዛ የእግር ኳስ ክለቦች አሉን፡፡ ሆኖም ለክለቦቻችን ተገቢውን ትኩረት ስንሰጥ አንታይም፡፡ ጭልጥ ብለን የውጪ የእግር ኳስ ክለቦች አድናቂዎች ሆነናል፤ ከማድነቅም አልፈን አምላኪዎች ሆነናል ብል ብዙም ያጋነንሁ አይመስለኝም፡፡ ያገራችን የእግር ኳስ ክለቦች እንዲሁም የውጪ ሀገራት የእግር ኳስ ክለቦች ውድድር በሚያደርጉበት ሰሞን ጆሯችንን ጣል አድርገን በተለይም ወጣቱ የሚያወራውን ብናዳምጥ ወሬው፣ “እንኳን ደስ ያለን! ክለባችን አሸነፈልን!… ያ እኮ አዛውረን ያመጣነው ጉደኛ ተጫዋች ነው በግብ ያንበሸበሸን!…” የሚል ሆኖ እናገኜዋለን፡፡ ወጣቱ ሰብሰብ ብሎ የእጅ ስልኩን እየጎረጎረ፣ “እንኳን ደስ ያለን! ክለባችን አሸነፈልን!…” ሲል ለሚያዳምጠው ስለሀገሩ ክለቦች እንጂ ስለውጪ ክለቦች የሚያወራ ላይመስለው ይችላል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያዊው ወጣት “ክለባችን” የሚላቸው፣ ደስታውን፣ አድናቆቱን… የሚቸራቸው የባሕር ማዶ የእግር ኳስ ክለቦች ሆነው ታገኟቸዋላችሁ፡፡ “አዛውረን ያመጣነው ጉደኛ ተጫዋች…” የተባለውም አንድ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ተጫዋች ሳይሆን የባሕር ማዶ ተጫዋች ስለመሆኑ ትረዳላችሁ፡፡
ይህን ስታዳምጡ እናንተን ምን እንደሚሰማችሁ ባላውቅም እኔ ግን ራስን ከክብር ማማ የማውረድ የቁጭት ስሜት ገዝፎ ይሰማኛል፤ ‘ይህቺን ሀገር ለማን አስረክበን ነው የምናልፈው?’ የሚል ብርቱ ጥያቄም ያቃጭልብኛል፤ ‘ወጣቱ ይህን ያህል ከማንነቱ ተፋትቶ ባዕድ አምላኪ እስኪሆን ድረስ ለምን ዝም አልን?’ የሚል ቁጭት አዘል ጥያቄም መንፈሴን ይረብሸዋል፡፡ ያገሬ ወጣት፣ “ያ እኮ አዛውረን ያመጣነው ጉደኛ ተጫዋች ነው በግብ ያንበሸበሸን!…” ካለ በኋላ ቀጥሎ የሚያደርገውን ሳስብ ደግሞ ቁጭቴ ይንራል፤ በቁጭቴ መሀልም አንዳች ስጋት ያድርብኛል፡፡
ያገሬ ወጣት ለውጪዉ ተጫዋች አድናቆቱን ከቸረ በኋላ ያንን ተጫዋች ለመምሰል ብቻ ሳይሆን ሆኖ ለመገኜት የማያደርገው ጥረት የለም፡፡ የጸጉር አቆራረጡን ባደነቀው ተጫዋች አቆራረጥ ይቀይራል፤ ያንን ተጫዋች ተከትሎ ጸጉሩን በቀለም ያቅላላል፤ ያንጨባርራል፤ ይጎነጉናል፤ ያስረዝማል፤ የሚያደንቀው ተጫዋች ሎቲ አንጠልጥሎ ካየ እሱም ያንጠለጥላል፤ አካሄዱ ፎቀቅ ፎቀቅ ከሆነ እሱም ሱሪውን ዝቅ አድርጎ ፎቀቅ ፎቀቅ ማለት ይጀምራል፤ ያ ተጫዋች ባንገት ሀብል ስም ወፍራም ሰንሰለት ካጠለቀ የእኛ ወጣትም እንደ ውሻ ወፍራም ሰንሰለት ባንገቱ ያጠልቃል፤ ያ ተደናቂ ስፖርተኛ ኮፍያ የሚደፋ፣ ሻሽ የሚያስር… ከሆነ እሱም ኮፍያ ይደፋል፤ ሻሽ ያስራል፤ ያ ተጫዋች ጣቱን እየቀሰረ፣ ማስቲካ እያንቀጫቀጨ ሰው የሚሳደብ ከሆነም የእኛ ሀገር ወጣት ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ያ ስፖርተኛ ተደባዳቢ፣ ባልባሌ ቦታዎች እየዋለ አልባሌ ነገሮችን የሚፈጽም ከሆነም የእኛ ወጣትም ይህን ከመፈጸም ላይቆጠብ ይችላል፡፡
እርግጥ ነው፤ የእኛ ሀገር ወጣት ጥሩ የሠራን እና ለስኬት የበቃን የባሕር ማዶ ተጫዋችም ሆነ ክለብ ማድነቁ የሚነቀፍ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ከራሱ ማንነት በዚህ ደረጃ መፋታቱ ተገቢ አይደለም በሚል ብቻ የሚታለፍ ክስተት አይመስለኝም፡፡
በባህላችንም ቢሆን እኛ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት ከራሳችን ማንነት ተፋትተን ቢቻል የውጪዎችን ለመሆን፣ ካልተቻለም ለመምሰል በእጅጉ ስንጥር እንስተዋላለን፡፡ ብንችል አያት ቅድመ አያቶቻችን ያወረሱንን የነጻነት ቋንቋ እርግፍ አድርገን ትተን እንግሊዝኛ መናገር የምንሻ እልፍ አእላፍ ነን፡፡ ሆኖም እዚህ ላይ አንድ ደስ የሚለኝ ነገር አለ፤ የራሳችንን ልሳን እርግፍ አድርገን በመተው ባዕድ ቋንቋ ለመናገር የቱንም ያህል ብንመኝም ችሎታችን ስለማያወላዳ (ስለማያኮራ) የማስመሰል ወይም ባዕዳንን የመሆን ጥረታችን በጥራዝ ነጠቅነት አንዳንድ ባዕድ ቃላትን ቀላቅሎ በመናገር ተወስኖ ይቀራል፡፡
ይህን ስል ግን የባዕድ ቋንቋን ጥንቅቅ አድርጎ መናገር መቻል አያስፈልግም ማለቴ አይደለም፤ እንዲህ ዓይነቱ ክህሎት በእጅጉ ጠቃሚ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ሳይ መንፈሳዊ ቅናት እንደሚያድርብኝም ልደብቃችሁም አልፈልግም፡፡ ሆኖም የራስን ትቶ የባዕድን ቋንቋ መጠቀም ከማንነት መራቅ ስለሆነ ይህን አጥብቄ እቃወማለሁ፤ እንዲህ ያለ ያልተገባ ፍላጎት ያለው፣ ከማንነቱ መፋታት የሚፈልግ ሰው እንኳም ችሎታው አነሰው ስልም በማንነቱ ጸንቶ፣ ኮርቶ፣ ታፍሮ እና ተከብሮ እንዲኖር ከመፈለግ እንደሆነ ውድ አንባቢያን እንድትረዱልኝ እሻለሁ፡፡
የራስን ቋንቋ ትቶ የባዕድ ቋንቋን ለመጠቀም የሚደረግ የተናጠል ጥረት ሲደማመር እንደ ሀገር የማንነት ቀውስ ያስከትላል፤ክብርምን ያሳጣል፤ ያስንቃል፤ ከሁሉም በላይ ከታሪክ ያፋታል፡፡ ምክንያቱም ይረርም ይምረርም ታሪካችን ተሰንዶ የተቀመጠው በቋንቋችን ነው፡፡ ከቋንቋችን እየራቅን፣ እየተፋታን… በሄድን ቁጥር ታሪካችንን እያዳፈንነው መሄዳችን እርግጥ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው፤ የኋላው ከሌለ የፊቱ የለምና፡፡
የባዕዳንን ቋንቋ ከፍ ከፍ ማድረግ እና በራስ ቋንቋ ላይ ባዕድ ቃላትን ቀላቅሎ መናገር ፊደል በቆጠረው ቀርቶ ፊደል በእጁ ይብላ በእግሩ በማያውቀው ወገናችን ሳይቀር ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ ፊደል ያልቆጠረው ወገናችን በማንነቱ የሚኮራ ቢሆንም ፊደል ቆጠርን ባዩ “ምሁር” አፍ በፈታበት ቋንቋው የባዕድ ቃላትን እየቀላቀለ ሲናገር ሲሰማ በከማን አንሼ ስሜት እሱም እየቀላቀለ መናገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡
ፊደል ቆጥሬያለሁ የሚለው “ምሁር” በዚህ ደረጃ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ፣ ከክብር ማማ የሚወርድ… ከሆነስ አለመማር ይሻላል ብለን ለማሰብ እስክንገደድ ድረስ ከንግግር አልፎ ባዕድ ቃላትን በጽሑፍ መሀል ማስገባትም፣ በተለይም የንግድ ድርጅትን፣ የመሥሪያ ቤት ስምን… ለማስተዋወቅ የመጠቀሙ ነገር እንደወረርሽኝ ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ እስኪ በየንግድ ድርጅቱ፣ በየተቋማቱ… ደጃፍ የተጻፈውን ስያሜ ላፍታ ባይነ ህሊናችሁ ተመልከቱ፤ “ሱፐር ዳቦ፣ ፎር ኤቨር አትክልትና ፍራፍሬ፣ ኦዞን ጁስ፣ መገናኛ ፉድ ዞን…” የጉራማይሌው ነገር ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ አንዳንዱ የባሰበት ደግሞ እንግሊዝኛውን ከላይ፣ የራሱን ልሳን ከታች ጽፎ ታዩታላችሁ፤ አንዳንዱ ጭልጥ ብሎ የጠፋው ደግሞ የራሱን ልሳን አልይ ብሎ የድርጅቱን ስም በባዕድ ልሳን ጽፎ ከፍ አድርጎ ሰቅሎት ትመለከታላችሁ፡፡
“ባለባበሱ፣ ባጊያጊያጡ፣ ባኗኗሩ.፣ ባስተሳሰቡ፣ በምግቡ፣ በመጠጡ… ልቡ ያልሸፈተ እና ባዕዳንን ለመሆን የማይታገል ማን አለ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ “ማንም” የሚል ነው የሚሆነው፡፡
ከማንነታችን ለመፋታት ይህን ያህል ቆርጠን መነሳታችን ያስገርማል፤ ከማስገረም አልፎም ውስጥን ያሳምማል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አሳዛኝ ነገር ስመለከት አያት ቅድመ አያቶቻችን በደም ባጥንታቸው ያስረከቡንን ነጻነት በፈቃደኝነት ከላያችን ላይ ገፍፈን ጥለን ወዶ ገብ ቅኝ ተገዥዎች ሆነናል ብየ እስከማሰብ እደርሳለሁ፡፡ ከማንነት እየተፋቱ፣ ከሌላው በታች ነኝ እያሉ ራስን እያዋረዱ “ነጻ ሕዝብ ነኝ”፤ “ነጻ ሀገር ነኝ” የማለት ፋይዳው ወይም ትርጉሙ ብዙም አይታየኝም፡፡
ራሳችንን መሆን ተስኖን ሌሎችን ለመምሰልም ሆነ ለመሆን ስንወድቅ ስንነሳ የሚያዩን ባዕዳንም ቢሆኑ እኮ ነጻ ሕዝብ ነን ብንላቸው “ድንቄም ነጻ ሕዝብነት!” በማለት በእኛ ላይ ላለመሳለቃቸው፣ እኛን ላለመናቃቸው ወይም ዝቅ አድርገው ላለመመልከታቸው ምንም ዋስትና የለንም፡፡ ራስን ያለመሆንን ችግር በግለሰብም ይሁን በሀገር ደረጃ ስመለከተው አእምሮየ፣ ‘ለምን ይህን ያህል ራሳችንን መሆን አስጠላን? ለምን ይህን ያህል ከራሳችን ለመፋታት ፈለግን? ለምን ታገሱ ተመለሱ የሚል ጠፋ?…’ በሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች ይጨናነቃል፤ መጨናነቁ መፍትሄ ባይሆንም፡፡
አእምሮየ ሌላም ጥያቄ ይመዝዛል፤ ‘ራሳችንን ሆነን፣ ሰው ሆነን መፈጠራችንም ሆነ ቅኝ ሳንገዛ መኖራችን ባጎናጸፈን ማንነታችን ኮርተን… የምንኖርበት ዘመን ይመጣ ይሆን?’ በማለት፡፡ ይህ ሊመለስ የሚችል ወይም መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ እያንዳንዳችን የራሳችን ማንነት እንዳለን፣ ሀገራችንም የእኛ የልጆቿ ማንነት ድምር ውጤት መሆኗን ተረድተን በግላችንም ሆነ በሀገር ደረጃ ራሳችንን ሆነን መኖር መጀመር አለብን።
ራሳችንን ሆነን መኖር ስንጀምር ራስን መሆን ባለመቻል ሊመጣ ከሚችል ግራ መጋባት፤ በሌሎች ሰዎች ወይም ሀገር ውስጥ የራስን ማንነት በመፈለግ ከሚከሰት የጊዜ ብክነት፣ ዝቅ ተደርጎ ከመታየትም ሆነ ውርደት ወይም ራስን ካለመሆን ዳፋ እንድናለን፤ በነጻነት ኮርተን፣ ነጻ ሕዝብ ሆነን፣ ታፍረን፣ ተከብረን… ኖረናል ብንልም ያምርብናል፤ ዛሬም፣ ነገም፣ መቼም… ታፍረን ተከብረን እንኖራለን፡፡ እናም ራስን የመሆን ፋይዳ በምንም ነገር የማይተመን መሆኑን ተረድተን ራሳችንን እንሁን በማለት ሀሳቤን በዚሁ ቋጨሁ፡፡
(ቦረቦር ዘዳር አገር )
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም