ለሰላም ሁሉም እንዲሠራ ተጠየቀ

0
125

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው እና ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ የተሻገረው ግጭት እንዲያበቃ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ይህ ግጭት የልማት ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ ምክንያት ሆኗል። ሕዝቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ፣ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ እና የሕዝብ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲቋረጥ ማድረጉን መንግሥት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መቋጫ እንዲያገኙ ባመቻቻቸው የውይይት መድረኮች ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። ይሁን እንጂ የሰላም ሁኔታው አሁንም ትኩረትን የሚሻ ሆኖ ይነሳል። ግጭቱ ክፉኛ ከጎዳቸው መካከል ትምህርት አንዱ ነው። በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ከአሚኮ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት በክልሉ የተፈጠረው ችግር ለሁለት ሺህ 833 ትምህርት ቤቶች ጉዳት ምክንያት ሆኗል።

ይህም ቀድሞውኑ ችግር የነበረበትን የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ሆኖ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም ግጭቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አሁንም ከትምህርት እንዲርቁ አድርጓል። ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ጫና የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲገታ፣ በተማረ ዜጋም ክልሉ ሀገራዊ ተወዳዳሪነቱን እንዲያጣ የሚያደርግ በመሆኑ ለሰላማዊ መፍትሄ ሁሉም ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል።

የክልሉን ሰላም ወደ ዘላቂነት ለመለወጥ ሁሉም እንዲረባረብ ሲጠየቅ፣ ግጭቱ ብዙዎችን በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ በሚያደርገው እና ለክልሉ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በሚነገርለት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ በመሆኑም ነው። አማራ ክልል ሰላም በነበረበት ወቅት ከቱሪዝም ዘርፉ በዓመት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኝ የነበረ ቢሆንም ይህ አኃዝ በ2016 ዓ.ም ከ865 ሚሊዮን ብር በላይ ዝቅ ያለ መሆኑን በባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ለበኵር አስታውቀዋል።

ክልሉ ከገባበት የሰላም እጦት ለማውጣት ታዲያ ሕዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው ምዕራብ ጎጃም ዞን እንደ ክልል ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አክትሞ የሕዝቡ ወጥቶ መግባት በተግባር እንዲረጋገጥ፣ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ የልማት ሥራዎች እንዲጀመሩ እና እንዲጠናቀቁ፣ የኑሮ ውድነት ጫና ማቃለልን እንዲሁም የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ የሚቻልበትን ርምጃ በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።

ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተሳተፉበት ውይይት የጸጥታ ችግሩ ሕዝቡን ለማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች እንደዳረገ ተጠቁሟል። የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ማማሩ ሺመልስ የጸጥታ ችግሩ የልማት ሥራዎችን ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጡ፣ ሕዝቡንም ለማኅበራዊ መቃወስ እና ለምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ማድረጉን ገልጸዋል።

ግጭቱ መቋጫ እንዲያገኝ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አቶ ማማሩ አስታውቀዋል። መንግሥት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም ለሚያደርጉት ጥረት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ ለሰላም እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። የታጠቁ ወገኖች ሕዝቡ እያሳለፈ ያለውን ችግር በመረዳት ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የክልሉ የሰላም ሁኔታ ባለፈው ዓመት ከነበረው የጸጥታ ስጋት አሁን ላይ ለውጥ እያሳዬ መምጣቱን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ የደቡብ ወሎ ዞን በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በደሴ ከተማ ባካሄደበት ወቅት አስታውቀዋል። ለዚሀም የጸጥታ መዋቅሩ እና ሕዝቡ በጋራ የሠሩት ሥራ ውጤት መሆኑን አረጋግጠዋል። “አሁንም እየተሻሻለ የመጣውን የጸጥታ ሁኔታ ለማስቀጠል በትኩረት ይሠራል” ብለዋል።

ክልሉ ከገጠመው ግጭት ወጥቶ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻዉን እንዲወጣ ተጠይቋል።

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ 28  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here