ለሰላም መስፈን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!

0
30

ሰላም የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ፣ሰላም ማለት ፍፁም ጤና፣ እረፍት፣ ዕርቅ ፣ፍቅር፣ አንድነት ማለት ነው’’ በማለት በይነውታል። ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ነው። የሰው ልጅ የመኖር ተፈጥሯዊ መብቱ እንዲከበር፣ ያለ ስጋት ወጥቶ እንዲገባ፣ ሰርቶ እንዲበለጽግ እና ነግዶ እንዲያተርፍ፣የተሻለ ምርት ለማግኘት ይችል ዘንድ የሥራ እድል ለመፍጠር የሰላም ዋጋው የትየለሌ ነው። ሰላም ከሌለ ያሰቡትን ማከናወን ይቅርና  ማቀድ፣ ነገን ማለም ወይም ተስፋ ማድረግ እንኳ አይታሰብም።

የሰላም ዋጋ ተመን የለውም   ለመላው የዱር እንስሳት እና  አእዋፍም ሳይቀር  በእጅጉ አስፈላጊ  መሆኑን ለማየት ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ እንስሳት ሲረበሹ፣ የተለየ ድምጽ ሲያሰሙ፣ ቀየውን   ለቀው ሲሰደዱ ማየቱ ብቻ በቂ ነው።

በመሆኑም ለሰላም መስፈን ሁሉም የሰው ልጅ   ሊያስብበት እና  ሊጠብቀው ብሎም ሊንከባከበው ግድ ይለዋል። ሰላምን እንዳናጣው ሁላችንም በጥንቃቄ ልንጠብቀው እና ልናስብበት ይገባል።

ከቅርብ አመት ጀምሮ በክልላችን በተከሠተው ግጭት  ሰላም በደፈረሰባቸው አካባቢዎች በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፣ ክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት ጠፍቷል ከኖረበት ቀየው ተፈናቅሏል፤ ሐብት ንብረቱን አጥቷል፣ ልጆቹ ከትምህርት እና ከስራ ተፈናቅለዋል። በዚህም ለአእምሮ እና ለአካላዊ ጤና ችግር ተጋልጧል።

በመሆኑም ሰላምን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ከየትኛውም ስራ በላቀ ርቀት እና ከፍታ ሊከናወን ይገባል። ሰላም ከምንም በላይ አስፈላጊ ስለሆነ ለሰላም ፍለጋ የማይጓዙት ርቀት የማይወጡት ዳገት መኖር የለበትም።

ለሰላም መደፍረስ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የሰላምን ጥቅም በማስቀደም ግጭቶች እንዲወገዱ  በአንፃሩም ሰላም እንዲሰፍን  እና ሰላምን  የማስከበር ሐላፊነት የሁላችንም መሆን  አለበት።

በክልላችን ዘላቂ  ሰላም ለማምጣት የተጀመሩ የሰላም ግንባታ ስራወች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁላችንም  ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ተጋግዘን መስራት ይኖርብናል።

ሰላምን ማስፈን የመንግስት ሐላፊነት ብቻ አለመሆኑን ማሕበረሰቡ ተገንዝቦ ይልቁንም ሰላም ባለመስፈኑ የደረሰብንን ጉዳት እና የገጠመንን ችግር ግምት ውስጥ አስገብተን ሰላም ሲሆን ደግም ስለምናገኛቸው በርካታ በረከቶችን በማጤን ከመንግስት ጎን ለጎን በጋራ መስራት፣በ ትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ  ላይ ምሁራን እና ሌሎች ተወላጆች ስራወችን እንዲሠሩ ማበረታታት እና የየድርሻችን መወጣት ይገባል። መንግስትም ዘላቂ ሰላም ይሠፍን ዘንድ የፍትሕ ስርዓቱን ማሻሻል፣የስራ እድልን ማስፋፋት ሙስናን መቆጣጠር እንዲሁም ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ አጠናክሮ መቀጠል ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

 ለሰላም መስፈን የሚያግዙ መንገዶችን በመጠቀም የክልላችን ሰላም ለማስፈን ይረዳ ዘንድ የተጀመሩ የእርቅ እና የውይይት ሂደቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ስለ ሰላም  መስበክ እና መስራት አዋቂነት እና አትራፊነት ነውና ይህ እንቅስቃሴ መበረታታት ይገባዋል።

የክልሉን ሁለንተናዊ ሰላም ለማስፈን እና ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣  ባለሐብቶች የሐገር ሽማግሌወች፣ ሴቶች እና ወጣቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

 

በኲር የጥር 18  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here