ለሰላም መሸነፍ አሸናፊነትም፤ አትራፊነትም ነው!

0
66

ሽማግሌ ማለት በዕድሜው፣ በልምዱ፣ በጥበብና በተግባራዊ  ብልህነትን ያረጋገጠ ሰው ሲሆን በማህበረሰብ ውስጥ የሚፈጠርን ግጭት የሚፈታ፣ የሚያስታርቅና የሚያስማማ ሰው ማለት ነው። ለሽምግልና የሚመረጥ ሰውም የሚታፈር፣ የሚከበር፣ የማያዳላና እኩል የሚያይ እንዲሁም የሚደመጥ ስለሆነ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሽማግሌዎችም ይህንን በመጠቀም ጸብን ለማብረድ ገለልተኛ መድረክን በመፍጠር አለመተማመን በሚኖርበት ጊዜ ሁለቱን ወገኖች ወደ ውይይት በማምጣት ሲያስማሙ ይኖራሉ።

ሽምግልና በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ በጣም ጥንታዊና የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓት እንዲሁም የይቅርታ፣ የእርቅና የሰላም ድልድይ እንዲሁም ማስፈጸሚያ ሂደት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።

በተለይም በሀገራችን በማህበረሰቡ ውስጥ ሽማግልና የጥበብ፣ የፍትህና የእርቅ ምልክት ነውን በጦርነት፣ በግጭትና በጥላቻ የተበላሸውን የሕዝብ ግንኙነት መልሶ በማቋቋም፣ እምነትን የመመለስና የጋራ መተማመንና ዳግም አብሮ የመኖርን እድል መልሶ የሚሰጥ ፍትሀዊ ሂደት ነው።

ብዙውን ጊዜ በሽምግልና “አሸናፊና ተሸናፊ” የሌለበት፤ ሁለቱንም ወገኖች አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት ስለሆነ ቅራኔን ለመፍታት የሚታመንና አማራጭ የችግር መፍቻ መንገድ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

በግጭትና በጥላቻ የተበላሸውን የሕዝብ ግንኙነት መልሶ በማቋቋም፣ እምነትን በመመለስና የጋራ እውነትን በመስራት ሀገርን ያጸናል። ሽምግልና በኢትዮጵያ ማህበራዊ ተሞክሮ ውስጥ ሀገርን ለማጽናት ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ  እሴቶች አንዱ ነው። በተለይ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና በወሰን ችግሮች ላይ ሽምግልና ብዙ ጊዜ የመጀመሪያውና የተሳካ መፍትሄ ሆኖ አገልግሎት ይሰጣል።

ሽምግልና የተቃራኒ ሃሳብን  ወደ ጋራ መግባባት ይቀይራል። በሽምግልናም ታሪኩን እንደገና በማዳመጥ፣ የከረሩ ስሜቶችንና ጫፍ የያዙ ፍላጎቶችን በጽሞና በማዳመጥና በመቀበል የጋራ መፍትሔ ይሰጣሉ፤ ጥላቻን ያስታግሳሉ። በሀገራችንም በተለያዩ ቦታዎች የተካሄዱ ብዙ የሽምግልና ሂደቶች በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሞት እንዲቆሙ፣ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዲመለሱና የተበላሹ ግንኙነቶች እንዲጠገኑ አድርገዋል።

በሽምግልና የሚሳተፉ ሰዎች ገለልተኛ መድረክ መፍጠር ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታመኑና የሚከበሩ፣ ሁለቱንም ወገን በእኩል ዓይን በማየት  ከሁሉም ወገን የሚታመኑ፣ የተለያዩ ቡድኖችን የሚያውቁና የሚያከብሩ ሰዎች ስለሆኑ ሁሉንም ወገኖች ወደ ውይይት ለማምጣትና ለማስማማት ትልቅ ሚና ስላለቸው ብዙ ችግሮችን ፈተዋል።

ይህን የመሰለ ሀገር በቀል የችግር መፍቻ ነባር እሴት ያላት ሀገራችን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ስታልፍ ነገርን ለማብረድ የሽምግልና ዋጋ ቀላል ባይሆንም የበለጠ አጠንክሮ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ሀገራችንም በተለይም በውስጥ ችግሮቿ የራሷን የችግር መፍቻ መንገድ በመጠቀም ስትፈታ እንደቆየችው አሁንም ይህንን እሴት በመጠቀም አሁን ያለውን ቅራኔን ለመፍታት በየቦታው ባሉ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶችን በመጠቀም ችግርን መፍታት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡

መደማመጥ፣ ወደጋራ አሸናፊ ወደሚያደርግ ሃሳብ መምጣት፣ ሕዝብን እስከጠቀመ ድረስ ለማሸነፍ እና መሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መቀራረብና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ እና ከዚህ በመሆን ድንጋይ መወራወር ሁሉንም ተጠቂ ያደርጋል፡፡ መቀራረብ ግን ለመነጋገር፣  ለመሰማትና ለመረዳዳት ያግዛል፡፡ ለሰላም መሸነፍ አሸናፊነትም፤ አትራፊነትም ነው፤ ነባር እሴታችን የሆነውን ሽምግልናን የችግር መፍቻ በማድረግ ሀገርን ለማጽናት እንጠቀምበት፡፡ በጦርነትና በሰለጠነ ዘመን “ደም ደምን አይመልስም። ቂም ቂምን አያጠፋም“ በሽምግልና ተቀራርቦ እውነትን በመናገር፣ ይቅርታ በማሰጠት፣ እርቅና ሰላም ማስፈን ዋናው መውጫ መንገድ ነው።

 

በኲር የታህሣስ  20ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here