የጦርነት፣ የግጭት፣ የፍረጃ፣ የንፁሃን ሰቆቃ፣ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ገና አሁንም አልቆሙም። ከልማት፣ ከሥራ፣ ከተስፋ ይልቅ የስጋት፣ የሴራ እና የጥርጣሬ ወጎች አየሩን ሞልተውታል። ይህ ሁኔታ ሲታይ አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ ገና ውይይት፣ ንግግር እና ድርድር አስፈላጊ ስለመሆኑ ነው። የተፈጠረው ችግር በመጠኑ የገዘፈ፣ በይዘቱም የተወሳሰበ ነው። ይህን ውስብስብ ችግር እልባት ለማስገኘት በመጀመሪያ መገዳደልን ማቆም ያስፈጋል።
ከዚያም መነጋገር እና መደራደር ይቀጥላል። ማንም በውጊያ ያሸንፍ ያለድርድር እና ውይይት ዘላቂ ሰላምን ማፅናት ይከብዳል። ድርድር ደግሞ የፖለቲካው ዓለም ቁልፉ ጉዳይ ነው። የድርድርን ሃሳብ ሁሉም ወገን በእኩል መደገፍ ያስፈልጋል::
ድርድር የሐሳብ ግብይትን የሚያፋጥን፣ የመሳሪያ አፈሙዝን የሚዘጋ፣ ሁሉንም ወገን ተደማጭ የሚያደርግ ሰጥቶ የመቀበል የ”እንካ በእንካ” አካሄድ ነው። ስለዚህ ተደራዳሪ አካላት ካላቸው ለመስጠት፣ ከሌላቸውም ለመቀበል በመዘጋጀት ዳር ከመቆም ወደ መሃል በመምጣት መነጋገር ይገባቸዋል። መነጋገር እና መደራደር ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ሰቆቃ መግቻ መንገድ ነው። መደራደር ሰፈሩን፣ አየሩን… በሰላም የመክበብ የማሸነፍ ጥበብ ነው። በድርድሩ ሕዝብ ያሸንፋል። በድርድሩ ሕይዎትን መታደግ ይቻላል። በድርድሩ ጥርጣሬ እና ስጋትን መቅበር ይቻላል። በድርድሩ ሐሳብ መሸጥም፣ መግዛትም ይቻላል። በድርድር መደማመጥ ስለሚቻል መደማመጥ፣ መረዳዳትና መናበብ እንዲሁም አብሮነት ስለሚኖር ሀገር እና ሕዝብ በተስፋ ይሞላሉ።
በመሆኑም ማንም በየትም ሁኔታ ለድርድሩ ሳንካ ሳይሆን መደላድል በመሆን ቀጣዩን አዲስ ዓመት የሰላም፣ የሥራ፣ የተስፋ ዓመት አድርጎ ለመጀመር ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ዛሬ በጥላቻ ምክንያት ደመነፍሳዊነት ጉልበት አግኝቶ የአንድ ሀገር ዜጎች በጠላትነት ተፈራርጀው በየፊናቸው ደመሰስን፣ ገደልን፣ ማረክን፣ አቆሰልን፣ አወደምን ብለው የድል የሚመስል ዜና ሲናገሩ ይሰማል። ነገር ግን ተረጋግቶ እና ጉዳዩን ነገ ላይ ሆኖ ማየት ቢቻል የጋራ ሽንፈት እንጂ የጋራ ድል የለም። የአንድ ሀገር ዜጎች በጋራ ካላደጉ፣ በጋራ ካላሸነፉ፣ በጋራ ካላዘኑ፣ በጋራ ካልተደሰቱ አንድነት አይመጣም።
“ለትብብር እና መግባባት ድርድሩን አለመግፋት” ከሁሉም ሀይሎች የሚጠበቅ ጥብቅ ጉዳይ ነው። ድርድር በሰላም የማይገፋ የእርቅ መንገድ ነው። ሁሉም በያለበት ለድርድሩ አወንታዊ ሚናውን መወጣት ከቻለ ድርድሩ ይሳካል፣ ሰላሙም ይመጣል::
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም