ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ቀዳሚ ፍላጎት ሰላም ነው፡፡ ስለ ሰላም ከመዘመር፣ ከማዜም፣ በመጻሕፍት ከመሰነድ ባለፈ ሰላም በተግባር አልተገለጠም፡፡
ሀገራት ሰላምን በማጽናት የሕዝባቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሰላም ስምምነት ሰነድ ሲፈራረሙ ይታያሉ፤ ይሰማልም፡፡ ለመደራደር የተቀመጡትም በርካቶች ናቸው፡፡ በየሀገራቸው በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ችግሮቻቸውን ለመፍታትም ጥረት ያደረጉ ውስኖች አይደሉም፡፡ የሰላም ዘብ የሚሆን ሚኒሥቴር እስከማቋቋም የደረሱት ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የሰላም መንገዶች በአብዛኛው ግጭቱን ሲያበርዱ አልተስተዋለም፡፡
በአሁኑ ወቅት 92 ሀገራት የሕዝባቸውን ሰላም እና ደኅንነት ባሳጡ ግጭቶች ውስጥ እያለፉ ይገኛሉ፡፡ የእኛዋ ሀገር ኢትዮጵያም ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ በአማራ እና በሌሎችም ክልሎች በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች እያለፈች ትገኛለች፡፡ የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም የፕሪቶሪያ ስምምነት እንደ መሠረት ቢነሳም በጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የነበረው የአማራ ክልል ዛሬም ድረስ በግጭት ውስጥ ይገኛል፡፡
የክልሉ ግጭት መነሻውን ያደረገው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ነው፡፡ የችግሩ መነሻ ምክንያት እንደነበሩ የሚነሱት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች አለመመለስ፤ የክልሉ ልዩ ኅይል መዋቅር ፈርሶ በክልል እና በፌዴራል የጸጥታ ተቋማት እንዲካተቱ የተደረገውን ሂደት መንቀፍ…ነበሩ፡፡
በክልሉ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኅይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች መካከል የተጀመረውን ጦርነት የክልሉ መንግሥት በመደበኛ ሕግ መቆጣጠር ባለመቻሉ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተደረገ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታወጇል፡፡ አዋጁም ሁለት ጊዜ ተራዝሟል፡፡ የክልሉ ይፋዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሥር ወራትን አልፏል፡፡
መንግሥት የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ በሕግ የማስከበር ርምጃ ለመቀልበስ እየሠራ ከነበረው ሥራ ጎን ለጎን ሰላማዊ የሰላም አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ሕዝባዊ ውይይቶች፣ የሰላም ጥሪዎች፣ የሰላም ካውንስል በማቋቋም ችግሩን በድርድር በመፍታት ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከናወኑ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ሥራዎች የክልሉ የሰላም ሁኔታ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ እንዲመጣ እንዳደረገው የክልሉ መንግሥት ተደጋጋሚ መግለጫ ያስረዳል፡፡
ሁለት ዓመታትን የተሻገረው ግጭቱ በክልሉ ሕዝብ፣ የልማት ሥራዎች፣ የመልካም አስተዳደር እና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ማድረሱ ግን አይዘነጋም፡፡ የክልሉን የሰላም ሁኔታ በዘላቂነት ለመመለስ የመንግሥት ቀዳሚ ፍላጎት ሰላማዊ ንግግር መሆኑን የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ይህም ዕውን እንዲሆን የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል ጥረት እንዳለበት ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም አባላት በየጊዜው ሲገናኙ ሀገራዊ ሰላምን በመመለስ እና ማጽናት ላይ በስፋት ተነጋግረዋል፡፡ በዘመናት መካከል ያጋጠሙ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፈው ዛሬ ላይ የደረሱ አረጋውያንም በትጥቅ ትግል የመጣ ለውጥ ባለመኖሩ ሰላማዊ አማራጮች ትኩረት እንዲያገኙ በተሰሚነታቸው ልክ መንገዶችን እያመላከቱ ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶችም ለአሁናዊ የሰላም ቀውሱ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳበዋል፡፡ የኢትዮጵያ እና የአማራ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔያት በወርሀ ሰኔ በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የሰላም መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ሆና ግጭቱ ከሃይማኖት አባት በላይ ሊሆን እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሰላም መድረኩ ተሳታፊ የነበሩ የሃይማኖት አባቶችም “ልጆቻችንን በመምከር ወደ ሰላም ማምጣት አሁናዊ ዓላማችን ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
በግጭት ወቅት ግጭቱን ለማርገብ የሃይማኖት አባቶች ከፊት ሊሰለፉ እንደሚገባ እና ሁሉንም አካላት በእውነት ላይ ተመሥርቶ በድፍረት መገሰጽ ግድ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ ‘‘የሃይማኖት ሰው ነኝ” ማለት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት አባቶችን ምክር መቀበል እና መተግበር ሰላሙ እንዲመለስለት ለሚጠበቀው ሕዝብ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡
ያልተጠቀምንባቸው እና ቸል ያልናቸውን ባሕላዊ የእርቅ መንገዶች በከፍተኛ ደረጃ አሟጦ መጠቀም የወቅቱ ሌላኛው መፍትሔ እንደሚሆንም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
”ሰማይ ተቀደደ ቢባል ሽማግሌ ይሰፋዋል” ብሎ የሚያምን ሕዝብ ባለበት ሀገር የሰላም እጦቱ ሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለው ችግር እንዲያበቃ የሀገር ሽማግሌዎች በከፍተኛ ኃላፊነት መሥራት እንደሚገባቸው የተናገሩት ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀገር ሽማግሌ አቶ ብርሐኔ የሻነው ናቸው፡፡ ሀገር ወደቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ተናገግረዋል፡፡ በተለይ “የአማራ ክልል ወደ ቀደመ ሰላሙ ተመልሶ አሁን ያለው ወጣት የእኛ ዕድሜ ላይ እንዲደርስ፣ ሕጻናት ትምህርታቸውን አስቀጥለው የነገ ሀገር ተረካቢነታቸውን እንዲያሳኩ እየሠራን ነው” ብለዋል:: በየመድረኩ ስለሰላም አስፈላጊነት ማሳወቅ ለክልሉ ሰላም መሆን ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጎንደር ሰላም እና ፀጥታ ሸንጎ ምክር ቤት እየሠሩ ያሉት የሀገር ሽማግሌው አቶ ባዩ በዛብህ ለበኵር በስልክ እንደገለጹት የትጥቅ ትግል ዜጎችን ለከፋ ጉዳት ከመዳረግ የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 80 ዓመታቸው ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት የሀገር ሽማግሌው፣ በኖሩባቸው ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶች ሀገሪቱ የተማሩ እና ችግር ፈቺ ምሁራኖቿ ከሀገር እንዲወጡ የተገደዱበትን ወቅት እንደማይረሱት ተናግረዋል፡፡
አሁንም በአማራ ክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ግጭቶች ተማሪዎችን ከትምህርት ከማራቅ፣ የዜጎችን እንቅስቃሴ ከመገደብ፣ የኑሮ ውድነትን ከማባባስ የዘለለ ትርጉም እንደሌለው ያለፉትን ዓመታት ክስተቶች እማኝ አድርገዋል፡፡ ብሔርን፣ ጎሳን፣ ሃይማኖትን… መሠረት አድርገው እየተቀሰቀሱ ያሉ ግጭቶች በሕዝቡ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እና መስተጋብር ላይ ውስብስብ ችግር በመፍጠር ለተባባሰ ቀውስ እንደሚዳርግም የሀገር ሽማግሌው አቶ ባዩ አስገንዝበዋል፡፡
”በዘመናት መካከል የትኛውም ችግር ሊያጋጥም ይችላል” የሚሉት አቶ ባዩ፣ ችግሮች ይዘውት ከሚመጡት ሕይወት ተገዳዳሪ ፈተና በመውጣት ሀገርን በትብብር ወደ ተሻለው መንገድ ለመምራት መነጋገር፣ መወያየት እና መደራደር እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ በዓለም ላይ የሰላም እና ደኅንነት መናጋት የገጠማቸው ሀገራት ችግሮቻቸውን ቁጭ ብለው በመለየት ለመፍትሔው በሰጡት ትኩረት ዛሬ ላይ ሰላማቸውን እንዳሳኩ ተናግረዋል፡፡
የእኛዋ ሀገር ኢትዮጵያም ከተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት ለመውጣት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሟን ገልጸዋል፡፡ የኮሚሽኑ አባል እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ባዩ ሕዝቡ በርካታ ችግሮችን መለየቱን እና ይህም ሀገርን ከቀውስ ለማውጣት ዋና መፍትሔ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ችግሮችን በመነጋገር መፍታትም የሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሀገርን ለቀውስ እየዳረጉ ያሉትን የሰላም እና ደኅንነት ችግሮች ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ከመጠቀም በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም ”ስለ ሕዝቤ ደኅንነት ይመለከተኛል” የሚሉ ሁሉ ኃላፊነት እንዳለባቸው አቶ ባዩ አሳስበዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች ግጭትን በማርገብ ረገድ ትልቅ አቅም እንዳላቸው አቶ ባዩ ማሳያዎችን ያነሳሉ፤ ከቅማንት ጋር በተገናኘ ለዓመታት ሲፈጠር የነበረውን ችግር እርሳቸው በተሳተፉበት የሰላም ሥራ ችግሩን መፍታት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ ይህም ችግሩ በዝምታ ቢታለፍ ኖሮ ሊያጋጥም ከሚችለው የከፋ ጉዳት ማዳን እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ባዩ ”አሁንም ያለው ችግር በንግግር መፈታት አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለኝ፡፡ ‘የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ገቡ‘ የሚል ዜና ሳይ በጣም እደሰታለሁ! ይህም ከሰላም ውጭ አትራፊ መንገድ እንደሌለ ማሳያ በመሆኑ ነው፡፡ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ግን የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል” ይላሉ፡፡
በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ስለ ሰላም አስፈላጊነት ማስተማር እንደሚገባቸውም አቶ ባዩ በዛብህ አሳስበዋል፡፡ ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጀምሮ የነበረው እና አወንታዊ ተጽእኖ ፈጥሮ የነበረው የ”በቃ! / No More!” እንቅስቃሴ አሁን ላይ መደገም እንደሚኖርበት ጠይቀዋል፡፡ የሰላም እጦቱ እያደረሰ ያለው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ችግሩ በስፋት ባለባቸው አካባቢዎች ይታያል ያሉት አቶ ባዩ፤ ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ ያሉ አካሄዶችን መንቀፍ የዚህ ዘመን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ክልሉ የገጠመውን የሰላም ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የክልሉ መንግሥት አቋም መሆኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን መብት እና ጥቅም ከማስከበር፣ የክልሉን ሕዝብ የጸና አንድነት ከመጠበቅ ያለፈ ጉዳይ እንደሌለውም ጠቁመዋል፡፡ የሰላም እጦቱ በእስካሁን ሂደቱ ካደረሰበት በላይ ጉዳት እንዳያደርስ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሌሎችም አካላት የተደረገው ጥረት መልካም ውጤት ማምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ አሁንም ችግሩ መንግሥት በያዘው የድርድር መርህ መቋጫውን እንዲያገኝ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም