ለሰላም ጊዜው ረፍዶ አያውቅም!

0
206

አንድ ወር ሁለት ወር እያለ ሰባተኛ ወሩን ያገባደደው አማራ ክልል የተከሰተው ግጭት  ዛሬም ሁነኛ እልባት አላገኘም።   ውሎ ማደር፣ አምሽቶ ማንጋት፣ ደርሶ መመለስ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል። የጥይት ድምፅ ሕፃናትን ከትምህርት አርቋል። አባዎራዎችን አሳዷል። የሞቀውን መንደር አፍዝዟል።

ጦርን በጦር፣ ጠብመንጃን በጠብመንጃ በመመለስ  ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ከባድ ነው። የፖለቲካ ሥብራቱ ለአለመተማመን፣ ለመፈራረጅ፣ ለኩርፊያ፣ ለአመፅ መገፋፋቱ ግልፅ ነው።  ችግሩ ፖለቲካዊ ከሆነ መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆን አለበት።   ለዚህ ደግሞ አሁንም ውይይት፣ ንግግር፣ ድርድር አስፈላጊ ነው።  ወንድም በወንድሙ ላይ ተኩሶ ታናሹ ሟች ሆኖ ታላቁ አሸናፊ የሚሆንበት ሞራላዊ ድል የለም። በፖለቲካዊ አሰላለፍ ወይም አቦዳደን ብቻ መገዳደል ዛሬ በጥላቻ ነገሩ ከሮ ባይጤንም፣ ለነገ ግን ታላቅ ሀዘንን እና ፀፀትን   ያሳድራል።

ይህ ከመሆኑ በፊት ሁሉም ወገን ለእውነት እና ለምክንያት ተገዝቶ እየሆነ ያለውን ነገር በትክክል ተረድቶ ለሰላም መሥራት ይገባል። ሠላም በማታለል፣ በማስመሰል፣ በእብሪት፣ በእልህ ስለማይመጣ ጥበብ፣ ጥልቅ ትንታኔ እና የሰከነ አዕምሮን ይጠይቃል።

አሁን በዚህ ወቅት ሙስሊም ክርስቲያኑ በፆም እና በፀሎት ወደ አምላካቸው በሚገናኙበት ጊዜ  ፅሞና ያስፈልጋል፡፡ የጥይት ድምፅ ጠፍቶ  የሰላም፣ የአንድነት እና የተስፋ ዜማ እንዲታወጅ  ሁሉም አካል ለሰላም  ቢወግን  ትውልድን የመጠበቅ ታላቅ ሀላፊነት ነው።

የፖለቲካ ታሪካችን ከመገዳደል፣ ከመፈራረጅ እና ከመጠላለፍ ወጥቶ በሐሳብ፣ በሳይንስ እና በጥበብ ይዋጅ ዘንድ  ለትክክለኛ ተቋማዊ ግንባታ፣ ለፍትሕ እና ለሕግ የበላይነት መገዛት ተገቢነት አለው። ይህ እንዲሆን በመጀመሪያ ሁሉም ወገን እንዲያሸንፍ ድርድር እና ንግግር ያስፈልጋል።  በውይይት የማይፈታ ችግር ስለሌለ   ሁሉም ወገን ለሀቀኛ ውይይት ራሱን ሊያዘጋጅ የሚገባበት ጊዜ  ነው።  ጦርነት ባደረ ቁጥር ሰው እና ሐብት ይበላል። በመሆኑም ከተሳሳተ ትንታኔ በመውጣት ሁሉን አሸናፊ ወደ ሚያደርገው የውይይት መድረክ መቅረብ ያስፈልጋል።

ውይይት እንኳንስ ለፖለቲካ ቀርቶ ለቤተሰብ ግንባታ ተመራጭ የሐሳብ ገበታ ነው። በምድጃ ዳር ተረት፣ ሙግት፣ ውይይት፣ ንግግር፣ እርቅ እና ድርድር ያደግን ልጆች ለምን ዛሬ ንግግርን ፈራነው? ለምን ድርድርን ራቅነው? ለምን ከሐሳብ ይልቅ ጦርን መረጥነው?

ሰላም ያሸንፍ ዘንድ የንግግር በሩ አሁንም፣ አሁንም ከልብ እንዲከፈት  መጠየቅ ሰዋዊ ግዴታ ነው። ግጭት ውሎ አይደር! ሰላም በደጃችን ትግባ። ሰላምን ለናፈቀው ሕዝባችን ሰላምን ከሚነፍጉ ተግባራት ሁሉም ወገኖች ይራቁ!

(የሺሃሳብ አበራ)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here