በኢትዮጵያ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሀገሪቷ የመሬት ቆዳ ስፋት ውስጥ 60 በመቶው የሚሆነው በደን የተሸፈነ እንደነበር ድርሳናት ያስነብባሉ። በተለይም በዓፄ ዳዊት፣ በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ እና በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር ይነገራል። ከ1960ዎቹ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የተተከሉ ወይም የለሙ ዛፎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዓመታት ትኩረት በመነፈጉ፣ የሕዝቡ ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመር እና በመሰል ምክንያቶች የሀገራችን የደን ሽፋን እየተመናመነ መጥቷል፤ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 3 በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታዲያ የደን ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ይተከላሉ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ የሀገር በቀል እፅዋት ቁጥር እየተመናመነ በመምጣቱም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተመናመኑ እና ጥብቅ ደኖች ልማት እና ጥበቃ ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ በቃሉ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የደን ልማት ሥራ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም የደን ልማት ሥራ ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል። የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ ሥራ መስፋፋት እና የባለቤትነት ስሜት ማጣት ለደን መመናመን ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል። ይህም ለበረሃማነት መስፋፋት፣ ለዝናብ እጥረት መከሰት እና ለዱር እንስሳት መሰደድ ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ፖሊሲዎችን ቀርፃ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። በተለይም ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከናወኑ ተግባራት ለደን ሽፋን መጨመር፣ ለደን ስነ ምህዳር መጎልበት፣ ለብዝኃ ህይወት መጨመር፣ እና ለካርበን ልቀት መቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለፃ የሰው ልጅ የእንጨት ፍላጎቱን (ለማገዶ፣ ለቤት ግንባታ፣ …) ለማሟላት፣ የእርሻ ሥራን ለማስፋፋት እና ከደን ውስጥ የሚገኙ ምርቶችን ለመጠቀም ሲል ደንን በመመንጠር የደን ሽፋኑ እንዲመናመን አድርጎታል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአረንጓዴ አሻራ በተሰጠው ትኩረት አሁን ላይ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሰረት በተደረገ የደን ሽፋን ልኬት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል። በአማራ ክልል ደግሞ የደን ሽፋኑ ወደ 16 ነጥብ ሦስት በመቶ ከፍ ማለቱን የደን ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ አስታውቀዋል።
ጃሬድ ዳይመንድ (Jared Diamond) Collapse (ውድቀት) በተሰኘው መጽሐፉ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን በተገቢው መንገድ የማይዙ እና ጥቅም ላይ የማያውሉ ማሕበረሰቦች ላልተገባ ስርዓተ ምህዳር፣ ለአጥፍቶ መጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ ይላሉ። የደኖች መመናመን፣ የእፅዋት አይነት መቀነስ፣ ሚዛን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት፣ … ለተጠቀሰው አደጋ ምክንያቶች መሆናቸውን ከምድረ ገፅ የጠፉ ማህበረሰቦች ታሪክ ዋቢ መሆኑንም ይጠቅሳል። ስለሆነም ከዚህ አደጋ ለመትረፍ ዛፍ መትከል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ለዚህም ነው ታዋቂው አርቲስት ቴወድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/
“ዛፉ ዛፉ እስትንፋሴ፣
ልጠብቅህ እንደራሴ!
ዛፉ ዛፉ አረንጓዴ፣
አንተ ባትኖር እኛስ አለን እንዴ?” በሚሉ ስንኞቹ ያቀነቀነው።
የደን ልማት ለሰው ልጅ እስትንፋስ እና ሕይወት መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል። የደን ልማት የአየር ንብረትን ከማስጠበቅ ባለፈ ለምግብነት አገልግሎት ይውላል። ደን ንፁህ አየር ለማግኘት እና ወቅቱን የጠበቀ እና ጤናማ ዝናብ እንዲዘንብ መሠረት ነው። ዛፍ የብዙ ተግባራት መፈፀሚያ፣ ለሰው ልጆች የመኖር ህልውና የተፈጥሮ ፀዳልን የምንቀበልበት ገጸ በረከት ነው።
የደን ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ፣ አረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ፣ የውኃ አካላትን ለማጎልበት (ምንጮች እንዲበራከቱ)፣ ለመድኃኒት መቀመሚያ፣ ለዱር እንስሳት መጠለያ፣ ንፁህ አየር ወይም ኦክስጅን ለማግኘት፣ ለማገዶ፣ ለቤት ግንባታ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ለምቱንም ለመጠበቅ፣ ለዱር እንስሳት መጠለያ፣ ለውጭ ምንዛሬ ማስገኛ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።
ለዚህም ነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በደን ልማቱ መነቃቃት እየታየ ያለው።
ቢሆንም ባለን ፀጋ ልክ ግን ተጠቃሚ ለመሆን ገና ብዙ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል የደን ባለሙያው። በመሆኑም በተለይ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ፣ የደን ኢንተርኘራይዝ፣ የምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ቅንጅታዊ አሠራርን በመከተል ዕውቀታቸውን ወደ አንድ በማምጣት በደን ልማቱ ዘርፍ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ባለሙያው አክለውም በትምህርት ሥርዓቱ ተካቶ ስለ ደን ልማት ጠቀሜታ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት አመላክተዋል።
ባለሙያው ለበኲር ጋዜጣ እንደተናሩት ለ2016 ዓ.ም ለአረንጓዴ አሻራ ትኩረት በመስጠት አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ መረጃውን እስከተለዋወጥንበት ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አንድ ነጥብ 37 ቢሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል። ከስድስት መቶ ሺህ በላይ የመትከያ ጉድጓድ ዝግጁ ሆኗል፤ ከ36 ሺህ በላይ የካርታ ልየታ ሥራም ተሠርቷል ነው ያሉት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳን ቢሊዮን ችግኞች በየዓመቱ በዘመቻ ቢተከሉም ከተከላ በኋላ ያለው እንክብካቤ ግን ዝቅተኛ ነው ሲሉ የዘርፉ ባሙያዎች ይተቻሉ፤ ከዚህ በተጨማሪም የሚተከለውን ችግኝ ብዛት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በዓይነት እና በፍሬ ሰጭነታቸው የተለዩ ዛፎችን ማልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሐሳብ የሰጡት ባለሙያው ተቋማት ሰኔ ሲደርስ ችግኝ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ቦታ አዘጋጅተው ችግኝ ገዝተው መትከል እና መንከባከብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ለአረንጓዴ አሻራ ወይንም ለችግኝ ተከላ መደረግ የሚገባቸውን መሠረታዊ ነጥቦችንም አስቀምጠዋል አቶ ዓለማየሁ። ይህም ችግኝ የሚተከልበትን ቦታ መለየት፣ ለቦታው የሚመች ዝርያ መምረጥ፣ የሚስማማውን የአፈር አይነት መለየት፣ ለችግኙ የሚሆን ግብዓት (ፕላስቲክ፣ ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማማ ችግኝ መምረጥ፣ …)፣ ደረጃውን የጠበቀ ጉድጓድ ማዘጋጀት፣ በወቅቱ መትከል፣ ርቀቱን ጠብቆ መትከል፣ ከተከሉ በኋላ ማረም፣ መኮትኮት፣ ግብዓት (ፍግ) መጨመር፣ ውኃ ማጠጣት፣ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ፣ የደረቁ ካሉ ክትትል በማድረግ መተካት እና በአጠቃላይ ዓመቱን ሙሉ ክትትልና ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል።
የችግኝ ተከላ የዘመቻ ሥራ ብቻ ሳይሆን የዓመት ሙሉ ሥራ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። ነገር ግን አሁንም ድረስ በተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ጉድለቶች እየታዩ ነው ብለዋል፤ ባለሙያው አክለውም ሰኔ ወይም ሐምሌ ላይ ተክሎ ከሄደ በኋላ ዘወር ብሎ የማያየው በርካታ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን አጋርተውናል። የዘመቻ ሥራ እንዳይሆን በኘሮግራም መመራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከፍተኛ ወጭ የወጣበት በመሆኑ በትኩረት መታየት ይኖርበታል። ማን ምን ይሠራል በሚል ሰነድ ተዘጋጅቶ ክትትል መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠትም ማግኜት የሚጠበቅብንን አበርክቶ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፤ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የሚተከሉ ዛፎችን ግንዳቸውን ከመሸጥ ይልቅ ዕሴት በመጨመር መሸጥ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል ብለዋል። ለአብነትም ኢትዮጵያ ወረቀት ማምረት መቻል እንዳለባት አመላክተዋል። ከውጭ የሚገቡ የደን ውጤቶችን በመቀነስ የውጭ ምንዛሪን መቀነስ ይገባል። “ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን” ይላሉ አቶ ዓለማየሁ፤ “ባለሀብቶችን ባሳተፈ መልኩ መሥራትን ይጠይቃል” ብለዋል።
ችግኝ ያለ ኘላስቲክ መትከል፣ የተከላ ቦታዎችን በወቅቱ አለማዘጋጀት፣ ጥራቱን የጠበቀ የችግኝ ዘር ቀድሞ አለማዘጋጀት፣ ድህረ ተከላ እንክብካቤ ላይ ስር የሰደደ ችግር መኖር፣ በምርምር ተቋማት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ አለመሥራት (ለአብነት በበሽታ እንዳይጠቁ)፣ የወጡ ሕግና መመሪያዎች በትክክል ተግባራዊ አለመሆን፣ የበጀት ችግር፣ በባለቤትነት የሚመራ ጠንካራ ተቋም አለመኖር፣ የግብይት ሥርዓቱ አለመስተካከል፣ … እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል ለደን ልማት ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል። በመሆኑም የተነሱትን ችግሮች መሠረት በማድረግ መፍትሔም በመስጠት በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ለ2016 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን በማዘጋጀት ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደተቻለ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም