ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን መረጋገጥ በትኩረት እንሥራ!

0
5

ሃገራት በአለም ዘንድ ዝነኛ ፣ የተከበሩ፣ ስማቸዉ   ተጠቃሽ ፣   የተፈሩ  እና ተፈላጊ ሆነዉ እንዲታዩ  ትኩረት  ያደርጋሉ። ይህን ፍላጎታቸዉን ለማሳካት ደግሞ በዋና  መሳሪነት የሚጠቀሙበት ብሄራዊ ጥቅማቸዉን በማስጠበቅ ነዉ። ብሄራዊ ጥቅም ለአንድ ሃገር የሚያስገኘዉን ጠቀሜታ  ዘርፈ ብዙ እንደሆን በርካታ የፖለቲካ ሙሁራን የሚያወሱት ሲሆን ለምሳሌም ብሄራዊ ጥቅም   የሃገርን ህልዉና እና   ደህንነት ለማስጠበቅ፣የበለጸገና  ተጽእኖ ፈጣሪ ሃገር እንዲሆን የማድረግ አቅም ፣የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት እንዲሁም የነጻነት መረጋገጥ እንዲኖረዉ፣ምጣኔ ሃብታዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ራስን ለመቻል፣ ከድህነት ለመዉጣት፣ሃገራት ፖለቲካዊ አቅም እና ተጽእኖ ፈጣሪነት እንዲኖራቸዉ ለማስቻል ፣የህዝቦችን ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ ፣የባህል ነጻነት፣እና  መሰል ጉዳዮች የብሄራዊ ጥቅም መሰረታዊ ገጸ በረከቶች እንደሆኑ ይጠቀሳሉ፤

ሀገራት  ብሄራዊ ጥቅማቸዉን ለማስከበርም የተለያዩ መንገዶችን ይከተላሉ። ከነዚያ በርካታ መንገዶች መካከልም  ስርኣቶቻቸዉን ፣  የሃገራቸዉ ጅኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥን ፣አለማቀፋዊ ሁኔታወችን ፣ በራስ ሃይል መጠቀምን ፣ከሌሎች ሃገራት ጋር መተባበርን፣መተጋገዝን፣መደመርን፣ ሰጥቶ መቀበልን ጨምሮ ሃገራዊ ጥቅሞቻቸዉን ለማስከበር   በእጅጉ ይጠቀሙበታል።

እነዚህንና መሰል መርሆወችን በመተግበርም ሃገራት  ታፍረዉና ተከብረዉ ይኖሩ ዘንድ የየራሳቸዉን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ያስችለኛል የሚሏቸዉን ተግባራት  በየወቅቱ ከሚለዋወጠዉ ነባራዊ የአለም ሁኔታ ጋር በመከለስ ተቋቁመዉና ተፎካክረዉ እንዲኖሩ ብሎም በአሸናፊነት ለመቀጠል የየራሳቸዉን ብሄራዊ ጥቅሜ ናቸዉ ብለዉ ያመኑባቸዉን ተግባራት   ከሃገራቸዉ ፣ከድንበራቸዉ ፣ ከጎረቤቶቻቸዉ ፣ እንዲሁም ከአለም ነባራዊ ሁኔታወች ጋር የተስማማ ለብሄራዊ ጥቅም ማስተግበሪያ የሚሆኑትን መተግበሪያ መሳሪወች  በየጊዜዉ ይነድፋሉ  ብሎም ይተገብራሉ።

ይህን በማድረጋቸዉ እና ብሄራዊ ጥቅሞቻቸዉን በማስከበራቸዉም  ዜጎቻቸዉ  በነጻነት የሚኖሩባት ሃገር ፣ የተሟላ የመሰረተ ልማት ያላት ሃገር  ፣ዜጎችም ብቁ እና ተወዳዳሪ፣ የተማሩ  ፣ ጤናማ እና አምራች ዜጋወች እንዲሆኑ   የሚያስችል  ሁኔታ ይፈጥራሉ

ሉኣላዊነቱን ያስከበረ ሃገር ብሄራዊ ጥቅሙንም ለማስከበር አይቸገርም:: ሃገራችን ኢትዮጵያም በብሄራዊ ጥቅሞ እና በሉዓላዊ ክብሯ ድርድር የማታዉቅ ሃገር  በመሆኗ ብሄራዊ ጥቅሞቻን አዉቃ እና አስከብራ ለማስቀጠል በብሄራዊ ጥቅሞቿ ዙሪያ ሰፋ ያለ እቅድ በመንደፍ ስራወችን ጀምራለች።  ስለ ብሄራዊ ጥቅም ምንነትን  እና አስፈላጊነቱን ያብራሩት የብልጽግና ፓርቲ ህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንዳሉት ብሄራዊ ጥቅም የሃገርን ሉአላዊነት ለማስከበር፣ባህል እና እሴቱን የጠበቀ ማህበረሰብ እንዲሁም ማንነቱ ተከብሮ እንዲኖር እና ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ ማስቻል ማለት ሲሆን ብሄራዊ ጥቅም ሲባል  የፓርቲ ወይም  የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የአንድ ሀገር  ህዝብ እና ትዉልድ አጀንዳ በመሆኑ ሁሉም ግንዛቤ ይዉሰድ በማለት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞች ባለፉት ዘመናት ጉዳት ሲደርስባቸዉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ጂኦ ስትራቴጅካዊ ተፈላጊነት፣ የሃገረ መንግስት ግንባታ አለመጠናቀቅ፣ድህነት፣ ሃላቀርነት፣የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፣ለብሄራዊ ጥቅሞቻችን ዋነኛ ፈተናወች እንደነበሩ ሚንስትሩ አዉስተዉ  አሁን ያለዉ ትዉልድ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ፈተና የሆኑት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለመፍትሄወቹ መስራት እንደሚገባዉ አሳስበዋል፣

ብሄራዊ ጥቅም  ሃገር በባህሏ ፣በወጓ ፣፣ በታሪኳ፣ በኪነ  ጥበቧ  በአለም ዘንድ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል እቅድ በብሄራዊ ጥቅም እቅድ ዉስጥ በመካተቱ  የህዝብ ማህበራዊ ልማትን ማለትም የተማረ ፣ጤናዉ የተጠበቀ፣ ማህበራዊ ዋስትና  ያለዉ እና አንድነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመገንባት በእቅዱ ዉስጥ በዋናነት የተቀመጡ በመሆኑ እነዚህ እቅዶች እንዲሳኩ እና ተግባራዊ ሆነዉ ተጠቃሚወች እንሆን ዘንድ  ለብሄራዊ ጥቅሞቻችን እንቅፋት የሆኑትን  ጉዳዮች በመታገል እና በማስወገድ በምትኩም ዛሬ ላይ ሃገራችን የምትፈልገዉንና ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር እንችል ዘንድ ከሚረዱን ተግባራት መካከል  ዉስጣዊ አንድነታችንን ማጽናት ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ባህልን ማዘመን ላይ ሰፊ ስራ በመስራት  የመፍትሄዉ አካል  ልንሆን  ይገባል፡፡

 

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here