ለተሻለ ውጤት – መብቃት

0
149

ከ402 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተና የሚያስፈትነው የአማራ ክልል ለተሻለ ውጤት መመዝገብ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 6/2017 ዓ.ም ይሰጣል፡፡ በሦስት ሺህ 649 ትምህርት ቤቶች   154 ሺህ 260 ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ፡፡ 148 ሺህ 256 ተማሪዎች ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ መግቢያ (ስምንተኛ ክፍል) መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡ ሁለት ሺህ 642 ትምህርት ቤቶች በአስፈታኝነት ተለይተዋል፡፡ ፈተናውም ሰኔ 3 እና  4 / 2017 ዓ.ም ይሰጣል፡፡

 

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች  99 ሺህ 880 እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በአስፈታኝነት የተለዩ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ደግሞ 470 ናቸው፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ተፈታኝ ተማሪዎች እና አስፈታኝ ትምህርት ቤቶችን ከለየ እንዲሁም ፈተናዎች የሚሰጡበትን ቀን ካስታወቀ በኋላ ለተሻለ ውጤት መመዝገብ ይበጃሉ ያላቸው ቅድመ ዝግጅቶች ከተማሪ እስከ ትምህርት ቤት እንዲደረጉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚህም አብዛኛዎቹ ትምህርት መምሪያዎች እና ጽሕፈት ቤቶች በሥራቸው ያሉ ትምህርት ቤቶች ተፈታኝ ተማሪዎችን  ማብቃት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

 

ለአብነት በኵር ጋዜጣ    ዞኖች ለተሻለ ውጤት መመዝገብ ምን ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ነው? ስትል የደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር፣ የምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች፣ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እና የሌሎችንም ትምህርት መምሪያ ኃላፊዎች በመጠየቅ ዘግባለች፡፡ ተፈታኞችን በሥነ ልቦና ማዘጋጀት፣ የማጠናከሪያ እና የማካካሻ ትምህርት መስጠት፣  መጻሕፍት ቤቶችን ሙሉ ቀናት ክፍት ማድረግ፣ ለኦንላይን ተፈታኞች መሠረታዊ የቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ አተኩረው እየሠሩ መሆናቸውን በመምሪያ ኃላፊዎቻቸው በኩል መገለጹ  ይታወሳል፡፡

 

እኛም በዚህ እትም  ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ አድርገው ከሚሠሩ የተለያዩ የመረጃ ቋቶች ያገኘናቸውን ተማሪዎችን የማብቂያ ስልቶች ልንጠቁማችሁ ወደድን፡፡ ፈተና በጣም የተረጋጉ ናቸው በሚባሉ ተማሪዎች ላይም ሳይቀር መጠነኛ መረበሽን ይፈጥራል፡፡ ለዚህ መፍትሔው በደንብ መዘጋጀት፣ የፈተና ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ ጠንካራ ክለሳ ማድረግ እንደሚገባ ብሪትሽ ካውንስል በድረ ገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ ያስገነዝባል፡፡

ሁሉም ፈተናዎች ከአንድ ወር ያነሰ በቀሩበት በዚህ ጊዜ ለእያንዳንዷ ደቂቃ ትኩረት ሰጥተው እንዲያጠኑ፤  በደንብ ሲዘጋጁ የቆዩትም ክለሳ እንዲያደርጉ  ይመከራል፡፡

ብሪትሽ ካውንስል በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ የፈተና ሰዓቱ እየተቃረበ በሚሄድበት ወቅት ተማሪዎች የክለሳ መርሀ ግብር በማውጣት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ካውንስሉ ለክለሳ የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችንም ለተፈታኝ ተማሪዎች በድረ ገጹ አስፍሯል፦

ፈተናዎች በምርጫ እና በዝርዝር በተጻፉ ነገሮች ላይ ተመስርተው ሊዘጋጁ እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ ጥናት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ያግዛችሁ ዘንድ ያለፉ የፈተና ወረቀቶችን መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ያለፉ ፈተናዎችን መመልከት የጥያቄዎቹን ዓይነት እና የሚመደበውን ሰዓት እንድታውቁ እና በዚያ ግንዛቤ ውስጥ ሆናችሁ ለፈተና እንድትዘጋጁ ያግዛችኋል፡፡

 

የተማራችሁትን ለመከለስ መርሀ ግብር ስታወጡ ከቀኑ ውስጥ ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጋችሁን ጊዜ መምረጥ ይኖርባችኋል፡፡ ለምሳሌ ጠዋት ላይ ቀለል የሚላችሁ እና ነቃ የምትሉ ተማሪዎች በዚህ ሰዓት ሰፊ ጊዜ መድባችሁ  ልታጠኑ  እንደሚገባ ይመከራል፡፡ ሌሎቻችሁም በተመሳሳይ የሚመቻችሁን ጊዜ መርጣችሁ እንድታጠኑ በድረ ገጹ ሰፍሯል፡፡

 

በአንድ የትምህርት ዓይነት ብዙ ነጥብ ለሚይዙ የፈተና ዓይነቶች ቅድሚያ መስጠትም ለውጤታማነት ያበቃል፡፡ በጥናት ጊዜ ቁልፍ ነጥቦች የማቅለም ልምድን ማዳበር እና አጫጭር ማስታወሻዎችን በቁራጭ ወረቀት መያዝም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን  ያጠናችሁት የትምህርት ዓይነት በየትኛውም ቦታ ላይ ሆናችሁ በቀላሉ እንድታስታውሱት ይረዳችኋል፡፡

መጻሕፍትን፣ በድምፅ የተቀዱ ይዘቶችን እና ኢንተርኔት ላይ የሚገኙ በቪዲዮ የቀረቡ ዋና ዋና ሐሳቦችን ጨምሮ ለማጥናት የሚረዱ የተለያዩ ዝግጅቶችን ተጠቅማችሁ   መከለስም ለውጤማነት የሚመከር ዘዴ ነው፡፡

 

ከእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ የሆነ ሰው ጥያቄዎች እንዲጠይቋችሁ በማድረግ የዝግጅታችሁን ሁኔታ መገምገም እንደሚኖርባችሁም ከብሪቲሽ ካውንስል ገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

አዕምሮን ለማደስ አዘውትሮ እረፍት ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ፈተና በሚደርስበት ወቅት አዕምሮ ይበልጥ ውጥረት ውስጥ መግባት አይገባውም፡፡

 

ጥናት እና ዝግጅታችሁን አጠናቃችሁ ለዋናው ፈተና ለሚሰጥበት ቀን ስትቀመጡ ምን ማድረግ እንደሚገባችሁም ከብሪቲሽ ካውንስል ያገኘንውን ሐሳብ እናካፍላችሁ፡፡ በዕለቱ በተቻለ መጠን ከመረበሽ እና ግራ ከመጋባት ስሜት ለመውጣት መሞከር ይኖርባችኋል፡፡  በዝግጅታችሁ  ልክ ጥሩ ውጤት ለማምጣትም መረጋጋት ይኖርባችኋል፡፡ ለዚህም ደጋግሞ በደንብ መተንፈስ ይመከራል፡፡ አልፎ አልፎ ውኃ መጎንጨትም ተገቢ ይሆናል፡፡

 

ፈተናውን መሥራት ከመጀመራችሁ በፊት የጥያቄ ወረቀቱን ከመጀመሪያ ገጽ እስከ መጨረሻው መመልከት፣ የተመደበውን ጊዜ ማየት፣ መመሪያውን እና የጥያቄውን ስብጥር ቀድሞ መረዳትን ማስቀደም ለጥሩ ውጤት ያበቃችኋልና ትኩረት ልትሰጡ ይገባል፡፡ ቀጥሎ የተመደበውን ጊዜ ማከፋፈል ይመከራል፡፡ ከባድ ጥያቄ ሲያጋጥም ምልክት አድርጎ ወደ ሚቀጥለው ጥያቄ ማለፍ የተመደበውን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያግዝ መረጃው ይጠቁማል፡፡

 

ጥያቄዎቹ የመረዳት አቅምን ታሳቢ አድርገው የወጡ ሊሆኑ ስለሚችሉ በጥሞና ደጋግሞ በማንበብ ተገቢውን መልስ መስጠት ይገባል፡፡ ፈተናውን ከተመደበው ጊዜ ቀደም ብላችሁ ማጠናቀቅ ከቻላችሁ የተሰጡ መልሶችን ተመልሶ መመልከት፣ ከብደዋችሁ ያለፋችኋቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ በመመርመር መልስ መስጠታችሁን ማረጋገጥ ዓመቱን በመልካም ውጤት ለመሻገር ያስችላል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here