ወቅቱ አርሶ አደሩ ፀሐይ፣ ብርድ እና አቧራ ሳይበግረው ለነገ ስንቁ ያለ እረፍት የሚታትርበት፤ ጊዜውን በአግባቡ ለመጠቀም ምሳውን ከቤቱ ሳይሆን ከማሳው ላይ የሚመገብበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ የጅራፍ ጩኸት እና የትራክተር ድምጽ አሁናዊ የገጠሩ መለያዎች ሆነው ይሰማሉ፡፡ እያንዳንዱ ማሳ ከአርሶ አደር እና ከከብት ውጪ የማይታይበት ወቅት ነው፡፡
የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ የመጠቀም መጠንን በመቀነስ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ ከወርሀ መስከረም ጀምሮ ሲያዘጋጅ፣ ሲያገለባብጥ እና ሲያቀላቅል የከረመውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በአህያ፣ ፈረስ፣ ጋሪ እና አለፍ ሲልም ከቤተሰቦቹ አባላት ጋር ተሸክሞ ወደ ማሳው ሲያጓጉዝ እና ሲበትን በዚህ ወቅት ማየት የሚያስገርም አይሆንም፡፡
ማኅበራት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አርሶ አደሮች መገናኛ፣ እርስ በእርስ መተዋወቂያ፣ ዘመድ አዝማድ መጠያየቂያ፣ ምርትን ለማሳደግ አንዱ ከሌላው ተሞክሮ የሚቀሳሰሙባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርን በወቅቱ አሟልቶ ዝናብ ጠብ እናዳለ ማሳን በዘር ለመሸፈን በዚህ ወቅት ማኅበራት በአርሶ አደር ይጨናነቃሉ፤ ከሚኒሥቴር እስከ ቀበሌ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ያለ እረፍት የግብርና ግብዓት ስርጭት የሚያካሂዱበት፣ ስርጭቱም በፍትሐዊነት እንዲሄድ ከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር የሚያደርጉበት ወቅት ነው፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪዉ አበባው ጌቴ ለመግቢያችን ሂደት ማሳያ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለ እረፍት የመኸር እርሻ ሥራቸውን እያስኬዱ መሆናቸውን በስልክ ነግረውናል፡፡
በየዓመቱ የግል መሬታቸውን ጨምሮ ከሦስት ሄክታር ያላነሰ መሬት ተከራይተው በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በርበሬ እና በዳጉሳ ይሸፍኑ ነበር፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን የሚያለሙትን የማሳ መጠን እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ በዚህም ዓመት የግላቸው በሆነው ሦስት ጥማድ ማሳቸው ላይ ብቻ ተወስነው ለማምረት ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዘር የሚሸፍኑትን ማሳ እንዲቀንሱ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩን ነው፡፡ በዓመቱ ለሚያለሙት ማሳም ሦስት ኩንታል ዳፕ እና ዩሪያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እስካሁንም ሁለት ኩንታል ገዝተው ማሳቸውን እያለሰለሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሰሎሞን አበበ በበኩላቸው 13 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት እየሠሩ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በጎርፍ አደጋ ምክንያት የታሰበውን ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ የተናገሩት ባለሐብቱ ዘንድሮ በሚሸፍኗቸው የተለያዩ ሰብሎች 100 ኩንታል ምርት ማግኘትን ታሳቢ አድርገው እየሠሩ ነው፡፡ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያን በስፋት መጠቀምን ለዕቅዳቸው መሳካት ዋነኛ መውጫ መንገድ አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልልም በመኸር ወቅቱ አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ክልሉ ወትሮውንም በሚታወቅባቸው ሰብሎች ይሸፍናል፡፡ 187 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ተጠባቂ ምርቱ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት እርሻን በድግግሞሽ ከማረስ ጀምሮ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን በስፋት ማቅረብ፣ የተለያዩ አይነት የአፈር ማዳበሪያዎችን በሚፈለገው መጠን በወቅቱ ከአርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ማድረግ፣ የሜካናይዜሽን አስተራረስን በሰፊው መተግበር እና አሲዳማ አፈርን ማከም ትኩረት አድርጓል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የክልሉ የሰላም ሁኔታ ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ማድረግ ይገባል።
የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በ2017/18 የምርት ወቅት 407 ሺህ 26 ሄክታር መሬትን በተለያዩ የሰብል አይነቶች ይሸፍናል፡፡ እንደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አዲሱ ስማቸው ገለጻ እርሻን በድግግሞሽ ማረስ ሰብሎችን ከተባይ እና አረም ጠብቆ ምርታማነትን ለማሳደግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ እርሻ 277 ሺህ 745 ሄክታር መሬት መታረሡን ገልጸዋል፡፡
ብሄረሰብ አስተዳደሩ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ለሜካናይዜሽን ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከ22 ሺህ 800 የሚበልጠው ማሳ በትራክተር ይታረሳል ተብሎ በዕቅድ መያዙን ምክትል ኃላፊዉ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ሚያዝያ 9/2017 ዓ.ም ድረስ 12 ሺህ 32 ሄክታሩ መታረሱን ተናግረዋል፡፡
በብሄረሰብ አስተዳደሩ ከአርሶ አደሩ፣ ከአካባቢው እና ከክልሉ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ምርት ለማምረት ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ጀምሮ የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን አቶ አዲሡ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ መጠን፣ ጥራት እና ፍጥነት ደግሞ ለእርሻ ሥራ ወሳኝ አካሄዶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በብሄረሰብ አስተዳደሩ ለሚሸፈነው የማሳ መጠን 816 ሺህ 660 ኩንታል የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ምክትል ኃላፊዉ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 466 ሺህ 399 ኩንታሉ ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ገብቷል፡፡ ይህም ከዓመታዊ ዕቅዱ ውስጥ 54 በመቶ ነው፡፡ እስካሁን ወደ አርሶ አደሩ የተሰራጨው ደግሞ 138 ሺህ ኩንታል ነው፡፡ ይህም ከዓመታዊ ዕቅዱ አኳያ ከ16 በመቶ የማይበልጥ ድርሻ ሲኖረው ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ከገባው ውስጥ መሰራጨት የቻለው ግን 30 በመቶዉ ነው፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ በበቂ መጠን ለማቅረብ እየተሠራ ቢሆንም ዋጋው በዓለም አቀፋዊ ተጽእኖ ምክንያት መጨመሩን ኃላፊው አንስተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በበቂ መጠን እንዳይጠቀም በማገድ የምርት ቅናሽ እንዳይኖር የምርት ዘመኑ ስጋት መሆኑ አይቀርም፡፡
የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በአፈር ማዳበሪያ ላይ የዋጋ መጨመር መኖሩን እንዳወቀ ለአርሶ አደሩ የማሳወቅ እና የማስገንዘብ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ደግሞ የስጋቱ ማምከኛ ሆኖ እየተሠራበት መሆኑን አቶ አዲሡ ገልጸዋል፡፡ አምስት ሚሊዮን 457 ሺህ 91 ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም 159 ሺህ 942 አርሶ አደሮች ተሳትፈውበታል፡፡ ሦስት ሚሊዮን 279 ሺህ 764 ሜትር ኩብ የሚሆነውን አውጥቶ መጠቀም መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም አራት ሺህ 952 ሄክታር መሬትን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡
ከፍተኛ የዝናብ መጠን በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የአፈር አሲዳማነት ከፍ ብሎ ይስተዋላል፡፡ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ለዚህ አብነት ነው፡፡ 40 በመቶ የሚሆነው መሬት የአፈር አሲዳማነት ችግር ያለበት ነው፡፡ ይህንንም በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን አቶ አዲሡ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ አንድ ሺህ 960 ሄክታር መሬትን ለማከም የኖራ ግብዓት ግዢ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ሁለት ሺህ 900 ኩንታል ኖራ ማቅረብ ተችሏል፡፡ ከቀረበው የኖራ ውህድ ውስጥ 27 በመቶ የሚሆነውን በ40 ሄክታር መሬት ላይ መቀላቀል መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የአፈር ጤናማነትን ከማስጠበቅ ባለፈ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ማሻሻል ሌላው የምርታማነት መሠረት ሆኖ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዓመት በብሄረሰብ አስተዳደሩ በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል ከተባለው አጠቃላይ የማሳ መጠን ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፈነው በበቆሎ ነው፡፡ ከ122 ሺህ በላይ የሚሆነው ማሳ በበቆሎ ዘር የሚሸፈን ሲሆን ለዚህም ያስፈልጋል የተባለው እና በክልሉ ግብርና ቢሮ የተመደበው 32 ሺህ 336 ኩንታል ነው፡፡ ምክትል ኃላፊዉ ይህንን ቃለ መጠይቅ በስልክ ለበኵር ጋዜጣ እስካስታወቁበት ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ አሥር ሺህ 82 ኩንታል ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ የደረሰ ሲሆን ከዚህም ስድስት ሺህ 395 ኩንታሉ ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል፡፡
የግብርና ግብዓትን በወቅቱ ማድረስ፣ አርሶ አደሩም ፈጥኖ ወደ ዘር እንዲገባ ማድረግ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ወቅታዊ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ መሆኑን አቶ አዲሡ አስታውቀዋል፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲስ ወልዴ ለአሚኮ እንዳስታወቁት በዚህ ዓመት ከ120 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በዘር በመሸፈን ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
በማሽላ፣ በማሾ፣ በእንቁ ዳጉሳ፣ በስንዴ እና በጤፍ ዘሮች ላይ ከፍተኛ ምርት ለማግኘት ከፍተኛ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 50 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱ ያስታወቁት አቶ አዲስ፣ እስከ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጊዜ ድረስ 32 ሺህ ኩንታል ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ገብቷል፡፡ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ “ወቅታዊ የግብርና መረጃ” ብሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባጋራው ጽሐፍ በ2017/18 የምርት ዓመት ምርታማነትን በሄክታር 34 ኩንታል ለማድረስ ታስቦ እየተሠራ ነው፡፡ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይለማል፡፡ እስካሁን የታረሰው ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በትራክተር የታረሰው 198 ሺህ 555 ሄክታር መሬት ነው፡፡ ጥቅም ላይ የዋለው የትራክተር ብዛትም 497 ነው፡፡
149 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ይሰራጫል፡፡ በቀጣይ ለሚዘሩ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የሩዝ፣ የቦሎቄ… ምርጥ ዘሮችን ለማሠራጨት ድልድል እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም እንዳስታወቁት ለመኸር እርሻው ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሉ መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡ አርሶ አደሮች የቀረበውን የግብርና ግብዓት በወቅቱ በመግዛት እንደ ዝናቡ ሁኔታ ቀድመው የሚዘሩ ሰብሎችን መዝራት፣ የግብርና ባለሙያዎች ደግሞ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የግብዓት ሥርጭቱ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እየተካሄደ ቢሆንም በጎጃም ቀጠና ካለው ፍላጎት አንጻር የበለጠ ሥራ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡ የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦትን ከማሻሻል ባሻገር የአፈር አሲዳማነትን በኖራ ማከም፤ የፀረ ተባይ ኬሚካል እና የቴክኖሎጂ ግብዓትን በስፋት በመተግበር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡
ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ ሁሉም በትኩረት እንዲሠራ ማድረግን ጨምሮ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን እና አሠራሮችን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ በዓመቱ የሚጠበቀውን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ዕውን ማድረግ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በመኸር እርሻ 21 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች ትሸፍናለች። 690 ሚሊዮን ኩንታል ምርትን ለማሳካትም ታቅዷል፡፡ ለዕቅዱ ተግባራዊ መሆንም የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት እና ሌሎች የምርታማነት ማረጋገጫ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል፡፡ እንደ ግብርና ሚኒሥቴር መረጃ በዓመቱ ለሚጠበቀው ምርት መሳካት 24 ሚሊዮን ኩንታልየሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው። ይህም 87 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጎበት የሚቀርብ ሲሆን በኩንታል ሦስት ሺህ 700 እንደማለት ነው፡፡ ከ24 ሚሊዮን ኩንታሉ ውስጥ እስከ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም 11 ሚሊዮኑ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙም ተመላክቷል፡፡
ምርታማነትን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ሌላው በትኩረት እየተሠራበት ያለው የምርጥ ዘር አቅርቦት ነው፡፡ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ዘር ይሠራጫል ተብሏል፡፡ የኩታገጠም አስተራረስ እና የእርሻ ሜካናይዜሽን ትግበራ እንዲሁም አሲዳማነትን ማከም ሌሎች የምርታማነት ማሳደጊያ መንገዶች ሆነው እየተሠራባቸው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ከማሳ ጭማሪው ጋር ተዳምረው በዚህ ዓመት የሚጠበቀው ምርት ከባለፈው ዓመት በ80 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም