የብዙኃን መገናኛ ለአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማሕበራዊ እድገት ወሳኝ ሚና ይጫዎታል፡፡ የተፋጠነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እውን ይሁን ከተባለ ጠንካራ የብዙኃን መገናኛ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ መልካም አስተዳደርን በማስፈን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የብዙኃን መገናኛ አውታር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ የብዙኃን መገናኛ ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት እና ከመንግሥት ጋር እንዲሁም ርስ በርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩበት ድልድይ ሆኖም ያገለግላል፡፡ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠርና ሁለንተናዊ እድገት እውን ይሆን ዘንድ የብዙኃን መገናኛ ቁልፍ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
የብዙኃን መገናኛ አውታርን ጠቀሜታ የተገነዘበው የያኔው የክልል ሦስት ያሁኑ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ላለፉት 30 ዓመታት ለዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ ሢሠራ ኖሯል፡፡ ሐምሌ 1986 ዓ.ም. አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ በወቅቱ ክልሉ ስለጉባኤው መካሄድ የሚዘግብ የራሴ የሚለው የብዙኃን መገናኛ አውታር ስላልነበረ ሐምሌ 19 ቀን 1986 ዓ.ም. በኲር ጋዜጣን በልዩ እትምነት እንድትዘጋጅ አድርጓል፡፡ በኲር በልዩ እትምነት እየወጣች የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ስትዘግብ ከቆየች በኋላ ከታህሣሥ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ በየሳምንቱ እየታተመች እንድትወጣ አድርጓል፡፡
በኲር በመደበኛነት ታትማ መውጣት ስትጀምር በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ የተሟላ የሥራ መሣሪያም ሆነ መሥሪያ አልነበረም፡፡ ሆኖም ችግርን ተቋቁመው በጽናት ለመሥራት ቁርጠኛ የሆኑ ሠራተኞች እንዲሁም ችግሮችን እያቃለለ፣ የብዙኃን መገናኛ አውታሩን እያጠናከረ ለመሄድ ቆርጠው የተነሱ መሪዎች ነበሩ፡፡ እናም ጋዜጠኞች እንዲሁም መሪዎች አንድ ሆነው በመሥራት ችግሮችን እየፈቱ፣ ዘርፉን በሚያስደምም ሁኔታ ሲያጠናክሩ ኖረዋል፡፡ በዚህ ጥረታቸውም በኲር ጋዜጣን በየሳምንቱ ከማሳተም ጎን ለጎንም የሬድዮ እንዲሁም የቴሌቪዥን ዜናዎችን እና ፕሮግራሞችን እያዘጋጁ ለኢትዮጵያ ሬድዮ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየላኩ ለሥርጭት እንዲበቁ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
“ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል” እንዲሉ ቀስ በቀስም የአማራ ክልል “ሬድዮን በመመስረት በሳምንት አንድ ቀን ለአንድ ሰዓት ያህል ዜናዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች ከዚሁ ከባሕር ዳር እየተሠራጩ እንዲተላለፉ ወደ ማድረግ ከፍታ ተሸጋግረዋል፡፡ ለቴሌቪዥን የሚሆኑ ዜናዎችን እና ፕሮግራሞችን በቀጥታ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከመላክም እያቀናበሩ ካሴት በመላክ በሳምንታዊ የሠላሳ ደቂቃ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማስተላለፍ ጀምሯል፡፡
በወቅቱ የክልሉ መንግሥት የክልሉ የብዙኃን መገናኛ አውታር የራሱ የሬድዮ ስቱዲዮ እንዲሁም ቢሮ ገንብቶ ስለነበር በኲርን ጨምሮ የዘገባ ሥራዎች የሚዘጋጁትም ሆነ የሚተላለፉት ከኪራይ ቤት ነጻ ሆኖ በራስ ስቱዲዮ እንዲሁም ቢሮ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ከፍተኛ የቢሮ መጣበብ ስለነበር ስብሰባዎች ይደረጉ የነበረው በየዛፉ ስር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ በቀደምት ጋዜጠኞች እንዲሁም በመሪዎች ያልተቋረጠ ጥረት በ12 ቋንቋዎች/የምልክት ቋንቋን ጨምሮ / መረጃዎችን እና ማስታወቂያዎችን በመላው ዓለም ለሚገኙ አንባቢያን፣ አድማጮች እንዲሁም አድማጭ ተመልካቾች ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ የሚያስተላልፈው ባለ ብዝኀ ልሣኑ ግዙፉ ተቋም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሊመሠረት ችሏል፡፡ አሚኮ በሰባት የሬዲዮ እንዲሁም በሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በአዲስ አበባ እና ደሴ ከተማም በማሠራጨት በመላው ዓለም ተደራሽ ኾኗል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በየትኛውም ቦታ ኾኖ መረጃ ማድረስ የሚችልበት ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ሥርጭት ማስተላለፊያ የቴሌቪዥን ስቱዲዮ ባለቤት ሆኗል፡፡ አሚኮ ይህን ስቱዲዮ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም የአሚኮ ቤተሰቦች በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ዋናው የአሚኮ ግቢ አስመርቋል፡፡ የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥየ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ተጨማሪ የሬድዮ ጣቢያዎችም እንደሚገነቡ፣ የሰቆጣ ኤፍ ኤምም በዚህ ዓመት ወደ ስርጭት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ገንዳ ውኃ ከተማ ላይም ወደ ጎረቤት ሀገር የሚደርስ የራዲዮ ጣቢያ እንዲኖር እየተሠራ ስለመሆኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ አሚኮ የሕዝብ ድምጽ ስለመሆኑ ያወሱት አቶ ሙሉቀን የአማራ ሕዝብ ወረራ ሲፈጸምበት ቀድሞ በመድረስ በየግንባሮቹ ዘገባዎችን እንዳደረሰም አውስተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አሚኮ ገዥ ትርክትን ለማስረጽ እየሠራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም አሚኮ አብሮነትን እንደ ሀገር እያስተማረ የሚገኝ የሕዝብ ሚዲያ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
የብዙኃን መገናኛ አውታሮች እንደ አሸን የፈሉበት፣ ዘመናዊ አሠራርን በመጠቀም ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚጥሩበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ በ2022 በኢትዮጵያ ተደራሽ ከሆኑ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ማየትን ራዕዩ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው አሚኮም እጅን እጅን በአፍ በሚያስጭን የለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛል፡፡ ራዕዩ ተሳክቶ ለማየት ይቻል ዘንድ የተጀማመሩ የብዙኃን መገናኛ ዘርፎቹን የማጠናከር ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም