ለትምህርት ስኬታማነት

0
78

የ2018 ትምህርት ዘመን ባለፉት ሁለት ዓመታት የባከነውን የትምህርት ጊዜ የሚያካክስ፣ ከትምህርት ውጭ ሆነው የቆዩ ተማሪዎችም መደበኛ ትምህርታቸውን ያለምንም ችግር ካስቀጠሉ ተማሪዎች እኩል የሚያስተካክል የተፋጠነ የትምህርት ሥርዓት ዘርግቶ ወደ ሥራ መግባቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤቶችን ዳጃፍ እንዳልረገጡ የቢሮው መረጃ ያሳያል፡፡ በእነዚህ ሁለት ዓመታት የተፈጠረው የትውልድ ክፍተት ሰፍቶ ክልሉን በሁሉዓቀፍ ዘርፍ ወደ ኋላ እንዳይጎትተው የ2018 የትምህርት ዘመን መውጫ ሊሆን ይገባል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪ ምዝገባ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እያደረገ ይገኛል፡፡ የዓመቱ ትምህርትም መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በዝቅተኛ የትምህርት አፈጻጸም ላይ የቆየው የምዕራብ ጎጃም ዞን የዚህ ዓመትን መማር ማስተማር በተባለው ቀን አስጀምሯል። አሚኮ የትምህርት አጀማመሩን በፍኖተ ሰላም ከተማ 01 እና ባከል የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቶ በቃኘበት ወቅት ተማሪ ሐናማርያም አለነ እና አፀደ መለሰ ትምህርት በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው ትምህርት በመቋረጡ በትምህርት ላይ የነበራቸው ተስፋ ዝቅተኛ ሆኖ እንዲቆይ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

የዳሞት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አቤል መለሰ በበኩሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው የጸጥታ ችግር ትምህርት እንዲቋረጥ በማድረጉ ጓደኞቹ ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌላ አካባቢ እንደተሰደዱ ተናግሯል፡፡

በተያዘው ዓመት በትምህርት ቤታቸው መማር ማስተማሩ ቀድሞ በመጀመሩ የተማሪዎች የመማር  ተስፋ ዳግም ነፍስ እንደዘራበት እና ለእነሱም  ዳግም መነሳሳት እንደፈጠረባቸው አቤል መለሰ ተናግሯል፡፡ አሁንም ቢሆን የተጀመረው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የስጋት ደሴ ባለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀው ግጭት ከ360 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ርቀው እንዲከርሙ ማድረጉን አንስተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም 426 ሺህ 29 ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ እስከ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም የተመዘገቡት ግን 41 ሺህ 366 ተማሪዎች ብቻ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ችግሩ በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ የስጋት፤ አሁንም ወደ ትምህርት ያልተመለሱትን ተማሪዎች ለመመለስ ሁሉም እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ  የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ድጋፍ እየተደረገም ይገኛል፡፡ ለአብነት የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቁሳቁስ የማሟላት ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ከትምህርት ተቋማት ጋር ሆኖ በመለየት ድጋፍ አድርጓል፡፡ “ዛሬ ደብተር የሚሰጣችሁ ተማሪዎች የነገ የሥራ መሪዎች፣ ሀገር ተረካቢ እና ተስፋ ናችሁ!” በማለት አበረታትዋቸዋል። ድጋፍ ለተደረገላቸው ሁለት ሺህ 400 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጠንክረው እንዲማሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባሕር ዳር በጎ አድራጎት ማኅበርም “አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አለመሟላት ምክንያት ከትምህርት መራቅ የለበትም!“ በሚል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡ ማኅበሩ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ 37 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ አንድ ሺህ ሦስት ተማሪዎች ነው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው፡፡ ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር፣ ስክብሪቶ፣ እርሳስ እና ማስመሪያ ድጋፍ ማድረጉን የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ አቶ አህመድ ይማም አስታውቀዋል፡፡ ማኅበሩ ባለፈው ዓመትም በ22 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ አንድ ሺህ 326 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉም ይታወሳል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በትምህርት ዘመኑ ሰባት ሚሊዮን  445 ሺህ 545  ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዕቅድ መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡ እስከ መስከረም 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር ከሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀድሞ የመመዝገብ ልምድ የሌላቸው መሆኑን እና የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ተማሪዎችን ባስቀመጡት ዕቅድ ልክ ለመመዝገብ መቸገራቸው ለዕቅዱ አፈጻጸም ዝቅ ማለት ምክንያት አድርገው አንስተዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የምዝገባ ሂደቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መሻሻል እንዳሳዬ ተናግረዋል፡፡ የትምህርት አጀማመሩም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የታየበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት ትምህርት ባልተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ያሳዩት እንቅስቃሴ ለትምህርት ሥራው ትልቅ ተስፋ እንደሰጠው አስገንዝበዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የታጡ ድሎችን በ2018 ዓ.ም ለማሳካት ሁሉም አካል ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ጠይቀዋል፡፡ የትምህርት ሥራ በደቂቃዎች፣ በሰዓታት እና በወራት የተከፋፈለ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ተማሪዎች በወቅቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው ሳያቆራርጡ እንዲከታተሉ ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት እና አመራሮች በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መምህራንም በተደራጀ መንገድ መማር ማስተማር እንዲሰጡ ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡

ወላጆች ልክ እንደ ተማሪዎች ሁሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ክልል ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ በሥነ ልቦና ተጎጂ ሆነው አልፈዋል ያሉት ኃላፊዋ፤ ነገር ግን በትምህርት ዘመኑ ለመመዝገብ የታቀደውን የተማሪ ቁጥር ለማሳካት የወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ “ወላጆች ባለፉት ሁለት ዓመታት የባከኑ የትምህርት ጊዜያት የሚካካሱበት ጊዜ አሁን ነው፤“ በማለት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት

ወላጆች ያልተፈጠረን ችግር ይፈጠራል ከሚል ስጋት ወጥተው በብሩህ ተስፋ ልጆቻቸውን ቀድመው ከማስመዝገብ ጀምሮ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩም ኃላፊዋ  ጠይቀዋል፡፡ የሚባክን የትምህርት ጊዜ እንዳይኖር ልጆቻቸውን መከታተል፣ የትምህርት ማኅበረሰቡን ማቅረብ እና ከለላ ማድረግ ከወላጆች እንደሚጠበቅም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ቢሮው ከተለያዩ አካላት ያሰባሰበውን የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያበረክትም አረጋግጠዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነሽ የተማሪ ምዝገባ አጀማመርን መሠረት አድርገው ነሐሴ 18 ቀን 2017 ዓ.ም መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ከሦስት ሚሊዮን በላይ የትምህርት ቁሳቁስ (ደብተር፣ እስክርቢቶ) ተሰብስቧል፡፡ ይህም ደጋፊ ለሌላቸው እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማሟላት ለሚቸገሩ ቤተሰቦች ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሰረጋግጠዋል፡፡

የትኛውም አካል ደግሞ ትምህርትን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ አድርጎ ትምህርት ቤቶችን ለትምህርት ዓላማ፣ የትምህርት ሥራውንም ባለማደናቀፍ ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “ልጆቻችን በማያውቁት፣ በማይፈልጉት እና ባልገባቸው አጀንዳ የነገ ሕይወታቸው፣ መንገዳቸው እና ግባቸው እንዳይስተጓጎል ሰው ሆነን እናስብ” በማለት ሁሉም አካል ክልሉ ከገባበት የትውልድ ክፍተት እንዲወጣ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ግዕእዝ በአማርኛ

ትምርት እፎ ውእቱ?

ትምህርት እንዴት ነው?

ሠናይ ውእቱ

ጥሩ ነው

ማዕዜ ውእቱ ዘፈጸምክሙ ፈተናክሙ?

መቼ ነው ፈተናችሁን የጨረሳችሁት?

ዘዮም ወር

የዛሬ ወር

እስፍንቱ አዝማኒከ?

እድሜህ ስንት ነው?

እሥራ ወክልኤቱ

ሀያ ሁለት

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here