ለትውልድ ቀጣይነት ዋጋ ከፋይዋ

0
90

በቻይና ዩናን ክፍለ ሀገር ኩንሚንግ ከተማ ኗሪዋ ሊ ዋይ  ለመጀመያ ጊዜ ነፍሰጡር መሆኗን ባወቀችብት ሰሞን ብትደሰትም አምስተኛ ወሯ ከገባ ጀምሮ በፊቷ ገጽታ ላይ  የተከሰቱት ለውጦች በመስታዉት የራሷን ምስል መለየት እስኪያቅታት ያስደነገጣት መሆኑን ኦዲቲ  ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ሳምንታት የፊቷ ቆዳዋ ጥርት ብሎ ብርታት ጥንካሬ ቢሰማትም ከአምስተኛው የእርግዝና ወራት በኋላ ግን ያልተለመዱ ለውጦች ማስተዋሏን ተናግራለች- ለሀኪሞች፡፡ ከለውጦቹ መካከል የፊት ቆዳዋ መታጠፊያዎች መጐድጐድ፣ የአፍንጫዋ መጠን መጨመር፣ በጉንጮቿ ላይ የእርግዝና ምልክት ነጠብጣቦች መታየት እና እግሯቿም እብጠት ተሰተውሎባቸዋል፡፡

ሊ ዋይን የሚከታተሏት ሀኪሞች የታዩባት ለውጦች የሚጠበቁ ተፈጥሯዊ መሆናቸውን ነው ያስረዷት፡፡ ሊ ዋይ ግን በታዩባት ለውጦች ተደናግጣ አመጋገቧን በማስተካከል ስኳር እና የስብ መጠንን በመቀነስ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሯን ተናግራለች- ለውጦቹን ለመግታት በማሰብ፡፡

ሊ ዋይ በሰላም ከተገላገለች በኋላ ፀጉሯ መሳሳቱን እና ቆዳዋም ከቅባታማነት ወደ ደረቅነት መቀየሩን በመገንዘቧ ሀኪሞችን ስታማክር ሁነቱ ተፈጥሯዊ  “ድህረ ወሊድ የፀጉር መርገፍ” በሚል የሚታወቅ ክስተት መሆኑን ነው ያስረዷት፡፡

ሊ ዋይን የተመለከቷት እሷም ስለ አስደንጋጭ ለውጦችዋ ያዋየቻቸው ሰዎች ሁሉም ሁነቱ ሊከሰት የሚችል የተለመደ መሆኑን ነው ያረጋገጡላት፡፡

ወጣቷ የሚሰጣትን ምክር እና አስተያየት በመቀበልም ከወሊድ በኋላ ጥሩ ጥሩ ለወላድ የሚመከሩ የተለያዩ ምግቦችን በመመገብ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጓን በማስቀጠሏ ቀደም ብሎ የነበራትን አካል እና ቁመና  መመለስ ችላለች፡፡ በመጨረሻም ወጣቷ እናት ሊ ዋይ በእርግዝናዋ ወቅት የታዩባትን ለውጦች፣ ዋጋ ከተከፈለበት ልጇ ጋር  የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎችን በማህበራዊ  ድረ ገጽ ለተመልካች አጋርታለች፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here