ለነገዉ የቀና መንገድ

0
157

የህዳር  9 ቀን 2017 ዓ.ም

የትምህርት ቤቶች  ውስንነት እና  ደረጃቸውን አለመጠበቅ፣ የመማሪያ ክፍል እጥረት እና ጥበት በኢትዮጵያ ላለው የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ፈተና ሆነው ይነሳሉ:: እነዚህን ችግሮች በመፍታት የትምህርት ጥራትን ዕውን ለማድረግ የትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት ማስፋት፣ የመማሪያ ክፍሎችን ለመማር ማስተማር ምቹ ማድረግ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት ሥርዓት ለውጥ እስከ ማድረግ ተደርሷል::

የትምህርት ዘርፉ ግን አሁንም ፈተናዎች አላጡትም:: በተለይ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ መልካቸውን እየቀያየሩ አሁንም ድረስ የቀጠሉ ግጭቶች /ጦርነቶች/ ትምህርት ተቋማት ከተቋቋሙለት አላማ ውጪ ለአገልግሎት እንዲውሉ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ ለጉዳት እና ውድመት በመዳረጋቸው፣ የውስጥ ግብዓታቸው በመዘረፉ፣ ተማሪዎች እና መምህራንም በስጋት አካባቢያቸውን በመልቀቃቸው ሚሊዮኖች አሁንም ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል::

በተለይ ያለፈው የመንግሥት ሥርዓት ለትምህርት የሰጠው ትኩረት አናሳ ሆኖ ሲወቀስ ይሰማል:: የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው በቃፍታ ሁመራ ወረዳ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በብዓከር ቀበሌ የተገነባውን የነገ ተስፋ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መርቀው በከፈቱበት ወቅት ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው:: ህውሓት በሥልጣን ዓመታቱ በነበረበት ጊዜ ትምህርት ቤቶች  እንዳይከፈቱ  እና ትውልዱ ወግ፣ ባሕሉን እና እሴቱን  እንዳያውቅ  ማድረጉን   አንስተዋል::

ሕፃናት የሀገራቸውን ታሪክ አውቀው እና ተረድተው በጥሩ ሥነ ልቦና ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ጎዳና እንዲያሻግሩ ከተፈለገ  በተባበረ ክንድ ትምህርት ላይ መሥራት እንደሚገባ አቶ አሸተ ገልጸዋል::

በአማራ ክልል የተፈጠረውና ከአንድ ዓመት በላይ የተሻገረው ግጭት ግን አሁንም ሚሊዮን ተማሪዎችን ከትምህር ማራቁ ምናልባትም በቀጣይ የትውልድ ቅብብሎሹ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ተሰግቷል:: በቅርቡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተደረጉ በሚገኙ የሰላም ውይይቶች በስፋት መነጋገሪያ የሆነውም ትምህርት በፍጥነት በሁሉም አካባቢ ይጀመር የሚል ነው:: ክልሉ በተማረ ዜጋ ወደ ኋላ እንዳይቀር፣ በምጣኔ ሐብትም እንዳይሽመደመድ፣ በቀጣይ ሀገር ለሚገጥማት ችግር መፍትሄ አመንጪ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬ ላይ ሁሉም ሰላምን በማረጋገጥ ለትምህርት ዘርፉ ዘብ ሊሆን እንደሚገባ ሕዝቡ በውይይቱ አረጋግጧል::

የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትም በክልሉ የተፈጠረው ችግር መፍትሄ አለማግኘቱ አሁንም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመሳብ መቸገራቸውን እየገለጹ ነው:: የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም የሩብ ዓመት ዕቅዱን በገመገመበት ወቅት  የፀጥታ ችግሩ በመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው ላይ መስተጓጎል መፍጠሩን ገልጿል:: የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት ተገቢውን ዕውቀት እንዳያገኙ ማድረጉም በግምገማው  ተነስቷል:: በዓመቱ ከ49 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር የከተማ አስተዳደሩ ዕቅድ ነበረው:: ይሁን እንጂ እስካሁን ማሳካት የተቻለው ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ብቻ ነው::

የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ የሩብ ዓመት ሥራዎችን በገመገሙበት ወቅት እንዳስታወቁት እስካሁን 15 ትምህርት ቤቶች ትምህርት አልጀመሩም:: የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል::

ወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ትምህርት እንዲጀመር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥረት ከማድረግ ባሻገር የመማር ማስተማር ሥራውን የተሳካ ለማድረግ የትምህርት ግብዓት ማሟላት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በተለይ በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት የተቀረጹ የግብረ ገብ፣ የአይ ሲቲ  እና የዜግነት ትምህርት መጻሕፍትን በአጭር ጊዜ ለተማሪዎች እና ለመምህራን ለማቅርብ ከክልሉ ትምህርት  ቢሮ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::

የሰሜን ወሎ ዞን በዓመቱ ትምህርታቸውን መከታተል ከነበረባቸው ተማሪዎች ውስጥ እስከ አንደኛው ሩብ ዓመት ማሳካት የተቻለው 40 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው:: የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ፍሰሃ ደሳለኝ መምህራን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተበተኑ ተማሪዎቻቸውን ሰብስበው በማስተማር ሙያዊ እና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል:: መምህራን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት በትምህርት ቤቶች በመገኘት ሥራቸውን በትኩረት መሥራት፣ ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱ ተማሪዎችንም እንዲመለሱ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል::

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዳስታወቁት በ2017 ዓ.ም 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዕቅድ ቢኖርም እስካሁን ማሳካት የተቻለው 2 ነጥብ 4 ሚሊዮኖችን ብቻ ነው:: ከአራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ግን አሁንም ወደ ትምህርት ቤቶች አልመጡም::

ርእሰ መስተዳደሩ አማራ ክልል በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል:: መማር ማስተማር ላይ የሚደርሰው ጉዳት ዛሬ ጦርነቱ እያደረሰ ካለው ሰብዓዊ ኪሳራ፣ በመንገዶች እና በመኖሪያ ቤቶች እየደረሰ ካለው ጉዳት በላይ እንደሚሆን ያምናሉ:: መዘዙ በትውልዶች መካከል የትውልድ ቅብብሎሽ  እንዳይኖር ክፍተት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል:: በመሆኑም ትምህርት የሁሉም አጀንዳ መሆን እንደሚኖርበት አስታውቀዋል:: ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ፣ መምህራን ወደ ማስተማር እንዲመለሱ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አጽንኦት ሰጥተዋል:: ለዚህም ሕዝቡ ለሚኖርበት አካባቢ ሰላም መሆን ዘብ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል:: የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here